በማግስቱ…! አዝናኝ ጨዋታ | Ethio Teyim | Episode 46

“ዐይኔ ዓለም አየ”፤ የላሊበላ ልጅነት እና የቦታ ፍልስፍና (አጭር ቆይታ ከዶ/ር ይርጋ ገላው ጋር) | Ethio Teyim | Episode 14

ወይ ጉድ…

ከዓመት ከምናምን በፊት…
 
“አብሬያቸው ብሰራ” ከምላቸው፣ ጥሩ ስሜት ካሉኝ መሥሪያ ቤቶች መካከል በአንዱ የሥራ ማስታወቂያ መውጣቱን ጋዜጣ ላይ ተመልክቼ ለማመልከት አሰብኩና የትምህርት እና የሥራ ማስረጃዎቼን አደራጅቼ ሄድኩ። (መቼም አብዛኛው ቅጥር በፖለቲካ አቋም፣ በትውውቅና በዝምድና እንደሆነ ባላጣውም፥ በምናልባት ነበር ሙከራው።)
 
ከወጡት ሶስት የሥራ መደቦች እኔ ለማመልከት የፈለግኩት “managing director” ይል የነበረውን የሥራ መደብ ነበር። (ቀሪዎቹ ሁለቱ Data Encoder እና Secretary ነበሩ።) መስፈርቱን በበቂ ሁኔታ ስለማሟላ “ለቃለ መጠይቅ ፈተና ቢጠሩኝ እንኳን…” የሚል ጉጉት ነበረኝ።
 
ቢሮው ደረስኩኝና የሰው ሀብት አስተዳደሯን (መሰለችኝ) “ጤና ይስጥልኝ፣ የሥራ ማስታወቂያ አይቼ ለማመልከት ነበር።” አልኳት።
 
“Data encoder ነው?” አለችኝ። (ሶስተኛው መደብ ‘secretary’ ስለነበረ ሴቶችን ብቻ መጠበቋም አብሽቆኝ ነበር።)
 
“አይ ለማኔጂንግ ዳይሬክተር መደብ ነው።” አልኳት።
 
ገለማመጠችኝ አይገልጸውም።
 
“ማስታወቂያውን በደንብ አይተኸዋል? መስፈርቱ ብዙ ነው።” አለችኝ።
 
“አዎ! ስለማሟላ ነው የመጣሁት። ዶክመንቶቼን ይዣቸዋለሁ።” አልኳት።
 
“ማስተርስ ዲግሪ ነው የሚጠይቀው።” አለች።
 
“Sure, አለኝ” አልኩ።
 
“በአስተዳደር መደብ የሰራም ይላል…” አለች
 
“አዎ ሰርቻለሁ። እንደውም አሁን የምሰራውም በአስተዳደር መደብ ነው።”
 
አልተዋጠላትም። ዶክመንቶቼን እየተቀበለችኝ፣ “ብዙ ሰው አመልክቷል። ባትደክም ግን ጥሩ ነበር” ብላ አጉተመተመች። ማኅተሞቹን አፍጥጣ መመርመር ያዘች።
 
“ቆይ ግን ምን ዓይነት ሰው ጠብቀሽ ነበር?… ለማኔጂንግ ዳይሬክተርነት የሚያመለክተው ሰው እንዴት መሆን አለበት ብለሽ ነው?” አልኳት።
 
መልስም አልሰጠችኝም።
 
ተናድጄ ቀጠልኩ። “ሁኔታሽ ደስ አይልም። ብቀጠር እኮ ምናልባት አለቃሽ ነው የምሆነው።” አልኩ።
 
እርሷ እቴ ምንም አልመሰላት። (በልቧ “ኡኡቴ” ሳትልም አይቀር)
 
‘ስወጣ የቅርጫት ሲሳይ ታደርገዋለች።’ ብዬ ባስብም የተቀበለቻቸውን ዶክመንቶች ዝርዝር መመዝገቢያዋ ላይ መዘገበችኝ እና ፈረምኩ።
 
“ሳስበው ስራውን ብዙም አልፈልገውም። ለፈተና መጠራቴን ግን እፈልገዋለሁና ዶክመንቴ ቅጥር ኮሚቴው እጅ መድረስ አለመድረሱን እከታተላለሁ። ደህና ይዋሉ።” ብያት ሄድኩኝ።
 
* * *
 
ከወራት በፊት ደግሞ…
 
ለአንድ የአደራ መልእክት… የቤትና የቢሮ እቃዎች ሱቅ ሳይ፥ ተልኬ የነበረውን መግዛት የነበረብኝ እቃ ትዝ ብሎኝ ገባሁና ዞር ዞር ብዬ አይቼ፥
 
“ይሄ ስንት ነው?” አልኳት።
 
“ለቤት ነው የሚሆነው” አለችኝ።
 
በልቤ “ሆ” ብዬ… “አዎ እኔም ለቤት ነው የፈለግኩት።”
 
“ማለቴ ለመኖሪያ…”
 
“አዎ እኮ ለመኖሪያ። ቤት ያለውና የሌለው በድምጽ ይለያል እንዴ?” እንደጨዋታ ነበር ያሰብኩትና ያልኩት።
 
የተጋነነ ብር ነግራኝ… አያይዛ፥ “ግን ከዚህ ወረድ ብሎ አንድ ቤት አለ። ጠይቀሃል እዛ። ይረክስልሃል።” ብላኝ እርፍ።
 
* * *
 
በዚህ ሰሞን…
 
የሰው አገር ጠብ እርግፍ ሲታይ ደግሞ፥ የሚገዛውን እና የማይገዛውን፣ የሚመጥነውን እና የማይመጥነውን ሰው በዐይን አይተው የሚለዩት የአገሬ ልጆች በዐይኔ ዞሩ። የአገር እና የአገር ልጅ ነገር እንደው ባሰቡት ቁጥር ግርም ይላል፤ …ይኼ ይኼም እንደ ደህና ቁምነገር ይናፍቃል!
 
አልኩኝም… ወይ ጉድ!!!

የጉዞ ማስታወሻ

“የአገር ልጅ የማር እጅ”

ባልተለጠጠ የጉዞ እቅድ፥ ብድግ ብዬ ነበር የሄድኩት። እንደነገ ልነሳ፥ አመሻሹ ላይ፥ የቀድሞውን የአውሮፓ ጉዞዬን እና፤ ነገሮች እንዳላሰብኳቸው ሄደው አስደስተውኝ እንደነበር ሳስታውስና፣ ይኽኛው እንዴት ሊሆን እንደሚችል በምናቤ ስስል ነበር። መቼም ርቀው ሄደው የራስን ሰው ሳያገኙ መቅረት የሚያጎድለው የማይታወቅ ነገር ይኖራልና፥ ያኔ መዳረሻ ቦታዬ ስደርስ፥ ያለሁበትን ከተማ ጠቅሼ ‘Any friend here? Coffee?’ ብዬ ነበር የፌስቡክ ገጼ ላይ እለጥፍ የነበረው።

ያ ‘የቡና እንጠጣ’ ጥሪዬ በጎ ምላሽ አግኝቶ፥ እጅግ ከሚገራርሙ ሰዎች ጋር እንዳገናኘኝ፣ በእንክብካቤ እንዳረሰረሰኝና፣ ባይሆን ኖሮ በቀላሉ ላላስብ የምችላቸውን ብዙ ነገሮች አሳስቦኝ እንደነበር ሳስታውስ፥ ድንገት ላፕቶፔን ከፍቼ አቴንስ እንደነበሩ ለማውቃቸው ሁለት የፌስቡክ ወዳጆቼ ‘Hi! If you’re still in Athens, and if convenient, may we grab coffee.’ የሚል የውስጥ መልእክት ላኩላቸው። አንደኛዋ ወዳጄ (ራሄል) በሞቅታ እና በአሉታ (በስራ ምክንያት ከከተማው ትንሽ ራቅ ብላ ነበር)፤ ሌላኛዋ (ቤቲ) ደግሞ፥ በተመሳሳይ ሞቅታ እና በአዎንታ መለሱልኝ።

ቢያንስ ቤቲን እንደማገኝ ሳውቅ ደስ አለኝ። ከሁለቱም ጋር ስልክ ተለዋወጥን። ከተማው ውስጥ የሌለችው ወዳጄን ቀድሜ ስላወራኋት ስለማረፊያዬ እና የሚቀበለኝ ሰው እንዳለ አጥብቃ ጠየቀችኝ። ለማረፊያው ሆቴል ቡክ እንዳደረግኩ፣ የሚቀበለኝ ሰው እንደሌለና፣ መደናበሩም የጉዞው አካል ነው ብዬ ስለማምን፥ የተቀባዩ ሰው ጉዳይ እንደማያሳስብ ገለጽኩላት። ሆቴል ማደሬን አልተስማማችምና ብዙ ተጨቃጨቅን። – እኔ ስግደረደር፣ እሷ ደግሞ በደግነትና በፍቅር ስትጋብዝ። (ከተማም ውስጥ ስለሌለች ‘oh, I am sorry’ ብላ ብታልፍም፥ ለኅሊናዋም በቂ ምህረት (excuse) ነበራት።)

“አመሰግናለሁ! ግን ስለሌሽም እኮ ብዙ አያስጨንቅም። ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን ሆቴል ስለሆነ የያዝኩት ያን ያህል የሚያሳስብ አይሆንም።” አልኳት።

“እኔ ባልኖርም ቁልፍ ጓደኛዬ ጋር ስላለ እሷ ከፍታ ትጠብቅሃለች። ችግር የለውም። …ምንም ቢሆን ቤት ነው የሚሻልህ።” አለችኝ።

“ኧረ ባክሽ ችግር የለውም። እኔ እኮ just ቡና እንጠጣለን፣ ሰው አገኛለሁ ብዬ አስቤ ነው መንገሬ እንጂ ላጨናንቅ አይደለም።”

“ካኔና! አልተጨነቅኩም። ባላገኝህ እንኳን ደስ ይበለኝ…” አለች።

ያው ፍቅርና ቅንነት ያሸንፋሉና እጅ ሰጥቼ ተስማማሁ።

“ኢንዳክሲ!” አለች ከነሞቅታው። – ባለመኖሯ የተሰማትን ቅሬታ እየገለጸች።

የቤቷን አድራሻ እና የመጓጓዣዬን ነገር አስረዳችኝና ተሰነባበትን።

ቀጥሎ ከሌላኛዋ ወዳጄ (ቤቲ) ጋር አወራን። እሷም ስለማደሪያዬ ጉዳይ እና የሚቀበለኝ ሰው እንዳለ ጠየቀችኝ። ከራሄል ጋር የነበረንን ቃለ ምልልስ ዘከዘኩላት። በሁለተኛው ቀን ስራ አስፈቅዳ ቀርታ፥ ከተማውን አብረን ዞረን እንደምናይ ነገረችኝ። ፈጣሪን አመስግኜ ተኛሁና በቀጣዩ ቀን ለጉዞ ተነሳሁ።

የ’ስላሴዎች’ አገር
አቴንስ አየር ማረፊያ እንደደረስን፥ ስልኬን አብርቼ ከዋይ-ፋይ ጋር ተገናኘሁ። ወዲያው ራሄል ደውላ፥ የምይዘውን አውቶቢስ ቁጥር አስታውሳኝ መንገዴን ቀጠልኩ። በነገረችኝ መሰረት ለ1 ሰዓት ገደማ በአውቶቢስ ተጉዤ፥ ታክሲዎች ወደቆሙበት ልሻገር ስል፥ ሸምገል ያሉ ሰው “Hi! Welcome Ethiopian” ብለውኝ እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉልኝ።

ከአንድ አንድ ከየት መሆኔን ስላወቁ ግርምም ደስም እያለኝ፥ እንደኢትዮጵያዊነቴ ከአንገቴ ደፋ ቀና ብዬ አጸፋውን መለስኩላቸው። በወፍ በረር ስለኢትዮጵያውያን ሰላማዊነት አወሩኝ። አባይንና አክሱምን ጠቃቀሱልኝ። “Haileselassie was a good politician” አሉኝ። ሌላም ሌላም የሚያውቋቸውን (እና ሳስበው፥ እኔን ሊማርኩ የሚችሉባቸውን) ነገሮች ጨራረፉልኝና ተሰነባበትን።

ከተደረደሩት ቢጫ ታክሲዎች ፊት ላለው ሾፌር፥ የቤቱን አድራሻ ሳሳየው “ግባ” ብሎኝ መንገዳችንን ቀጠልን። እሱም እንግዳነቴን አውቋልና “Where are you from?” ብሎ ጠየቀኝ። “Ethiopia” መለስኩለት። “Oh, country of Selassies” አለኝ። ተገርሜ፥ ማብራሪያ ጠየቅኩ… “I know Haileselassie, and Haile Gebresellasie. Nai?” ብሎኝ ሳቀና… “country of Haile Selassies” ብሎ እንደማስተካከል አደረገ። ተሳስቀን እየተጫወትን አድርሶኝ የቆጠረውን ብር ከፍዬ ወረድኩ።

‘Feel Like a Star’

ራሄል እንዳጠቆመችኝ ሽቅብ ወደ 2ኛ ፎቅ ቀና ስል፥ ፍልቅልቅ ኢጦቢኛ ፊት ታየኝ። እጇን እያውለበለበች “Welcome ጆኒ! በሰላም ነው? አረፈድክና ተጨነቅኩ እኮ” ብላኝ መግቢያውን ጠቆመችኝና፣ እኔ ስወጣ እሷ ስትወርድ አሳንሰር ጋር ተገጣጠምን። ቤት ስገባ የምግብ ጣዕም አፍንጫዬን አለው።ቁጭ ከማለቴ፥ “እንግዲህ እንዳገርቤት ማስታጠቢያ የለንም። ከይቅርታ ጋር ና እዚህ ታጠብ።” ብላ እየተፍለቀለቀች መታጠቢያ ቤቱን አሳየችኝ። “ወይኔ! ሪች ግን ምን ማድረጓ ነው? ለምን ታደክምሻለች? …ቆይ እሺ ትንሽ አርፌ እንበላለን።” አልኳት። “አይ ሳይቀዘቅዝ ነው እንጂ። ደግሞ ቡናም እንደምትወድ ነግራኛለች… ብላና ቡና ትጠጣለህ።” ብላኝ ሳቀች። (የራሴው ነገር እየገረመኝ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ትዝ አለችኝ። “እቺን ሽሮ ምሳህን ብላና፥ ራት ዶሮ ነው” ዓይነት። የቡና ስም ተጠርቶማ ለምግብ መቸገር ግድ ነው። 🙂 )

ተበላ። ተጠጣ። ተጠገበ። በቡና ታጅበን ተጨዋወትን።

“ካርድ የለውም ግን ይህኔ ትሞላበታለች። እንግዲህ የሚቸግርህ ነገር ካለ፣ ቦታም ቢጠፋህ ደውልልን። ልጆቼም ስለሚያስቸግሩኝ እንግዲህ አላማሸሁህም። አንድ ጓደኛችንን በኋላ ይመጣል፥ እሱ ይዞህ ይወጣል። ቡና ማፍላት ከፈለግክ፣ ሌላም የምትፈልጋቸው ነገሮች ካሉ….” ብላ ቦታ ቦታ ጠቋቁማኝ፥ ሲም ካርድ ያለበትን ስልክ ሰጥታኝ ተሰናብታኝ ሄደች። ወዲያው ራሄል ደውላ ሰው እንደሚመጣልኝ ነገረችኝ። ብዙም ሳይቆይ፥ ሳሚና ሪታ ከሚባሉ ወዳጆች ጋር ስንቀባረር፣ ቢራዎቹን ስቀማምስ፣ ከተማ ለከተማ ስዞር አመሸሁ። የእነሱም እንክብካቤ ወደር አልነበረውም።

የራሄል ነገር እንዲህ ተተርኮ የሚያልቅ አይደለም። ለምሳሌ፥ “ይሄን ባስ ያዝ… እዚህ ውረድ… በዚህ ግባ… በል እዚህ ዞር ዞር በልና ሲደብርህ ወይ ደግሞ ሌላ ቦታ መሄድ ከፈለግክ መልሰህ ደውልልኝ።” ብላ ከተማውን በስልክ ሸኝታ አስጎብኝታኛለች። ቤቲም ባለችው ዕለት ስራ ፈቃድ ጠይቃ ያለሁበት መጥታ ይዛኝ ሄዳ ከተማውን ስታስጎበኘኝና ስትንከባከበኝ ውላ አመሻሹን ተለያየን።

የእንክብካቤዋን ነገር ሳስብ ወደፌስቡክ ጎራ ብዬ “Some people make you feel that you’re more important than what you actually are (or than that you thought you could be). I’ve seen the hospitalit-iest in Athens. Richo, you have left me speechless! You’re amazing that you’ve remote controlled my joy” ለጥፌ ዞር ስል የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ‘feel like a star’ በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ይሄድ የነበረ የቱርክ አየር መንገድ ማስታወቂያ ትዝ አለኝ።

ማስታወቂያው. . .

ተሳፋሪው ከሚደረግለት የላቀ መስተንግዶ የተነሳ የሆነ ዓይነት ቅዠት ውስጥ ገብቶ፥ ‘ታዋቂውን የፊልምና የሙዚቃ ባለሞያ ኬቨን ኮስትነር ብሆን እንጂ… ይሄ ሁሉ እጥፍ ዘርጋማ ለመደበኛ ሰው አይሆንም።’ ብሎ አሰበ። ምስሉ ላይም – አውሮፕላን ውስጥ ቁጭ ብሎ፣ መጽሐፍ እያነበበ እንቅልፍ ሲያዳፋውና አስተናጋጇ መጥታ bookmark (ማለቢያ) ስትከትለት፣ ብዕር ወድቆበት ስታነሳለት፣ እንዲህና እንዲያ ሲሆን… ደግሞ ወርዶ ተርሚናሉ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር እንደ surprise ገባ ብሎ ፎቶ ሲነሳ – ራሱን እንደ ኮስትነር እየቆጠረ፣ የሚታየውም ምስል የኮስትነር ሆኖ ነበር። ከነፈንጠዝያውና ቅዠቱ መስታወት ፊት ቆሞ መልኩን አይቶ በሁኔታው ፈገግ እስኪል ድረስ።ታዲያ እኔስ አቴንስ ውስጥ እንዲህ ቢሰማኝ ይፈረድብኛል?! As the famous Turkish ad goes, ‘it is easy to feel like a star’, but ‘to let someone random feel so’.

ራሄል ግን አትገርምም!?

አቴንስimages

አቴንስ ሁለነገሯ ደስ ይላል። ሰዉ ነፍስ ነው። – በተለይ የሀበሻው ሁኔታ ያባባል። ምሽቷም ደማቅ ነው። ጥቂት መስራት፣ ብዙ ማረፍ። ጥቂት መንቀሳቀስ፣ ብዙ መዝናናት፥ የአቴንስ የኑሮ ዘይቤ… – ሰዎቹ “ኬረዳሽ” የሚሉ ይመስላል። አምሽታ የምትተኛው አቴንስ፥ አርፍዳ ነው የምትነቃው። (ሱቆች 5 ሰዓት ላይ ቢከፈቱ ነው።) ደግሞ “በኋላ እገዛዋለሁ” ብለው ያለፉትን ነገር፥ ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ትዝ ብሎ ቢኬድ፥ ሱቁ ተዘግቶ ሊጠብቅ ይችላል። የቱሪስት መስህብ የሚባለው የአክሮፖሊስ የጉብኝት ሰዓት እንኳን ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ብቻ ነው። የሰዉን እርጋታ ግን ምንም የሚቀማው አይመስልም።ከቤቲ እና ከራሄል ጋር (በስልክ)፥ የታሪክና የአቴንስ ከፍታ የሆነው አክሮፖሊስ ወጥተን ዙሪያ ገባውን ቃኘን። አካባቢውንም በረበርነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከሰፈረበት፥ ሊካቪቶስ ድንጋያማ ከፍታ ላይ ሆነን ከተማዋን አቆልቁለን እያየናት፥ ፀሐይቱን ወደማደሪያዋ ሸኘናት። ፕላካ ደርሰንም ዙሪያ ገባውን ያሉ መዝናኛዎችን ቃኝተን ሻዩን ቡናውን ቀማመስን። ዋና አደባባይ የሚባለው ሲንዳግማ ላይ ተሰይመን፥ የገናን ድባብ፣ የሰዉን እንቅስቃሴና የፓርላማውን ጥበቃ ፖሊሶች ትዕይንት ተመለከትን።

የገበያ ማዕከሎቹን እየጎበኘን አልፈን፣ ሞናስትራኪ እና አቢሲኒያ አዳባባዮችን ተንጎራደድንባቸው። – ሞናስትራኪ ድድ ማስጫ ነገር ነው። አቢሲኒያ ስሙና ታሪኩ በቀድሞ ሰዎች ብቻ የሚታወቅ ሆኖ፥ ንግድ የሚቀላጠፍበት ቦታ ነው። (ለኃይለ ስላሴ ክብር የተሰየመ እንደሆነ ሰምቻለሁ)

ድመትና ፍሉት6e1b91600032958f551451c4683632db

ከሞናስትራኪ ወደ አክሮፖሊስ ዳገቱን ስወጣ፥ አንድ ኩርባ ላይ 26 ድመቶች (ቆጥሬያቸው ነበር)፥ ፍሉት እየተጫወተ የሚለምን ጎልማሳ ዙሪያ ተኮልኩለው አየሁ። መጀመሪያ ድመቶቹ እሱ የሚያረባቸውና ይዟቸው የመጣ ነበር የመሰለኝ። ምንም እንኳን ‘የነብር ዘሮች የፍሉት ድምጽ ይስባቸዋል’ ሲባል ብሰማም፥ ብዛታቸው እና ምሳጤያቸው እንደገረመኝ መንገዴን ቀጠልኩኝ። ስመለስ ግን 2 ድመቶች ብቻ ቀርተዋል። የቀሩት የት እንደሄዱ ስጠይቅ፥ ቀድሞም ሙዚቃውን ሰምተው የተሰበሰቡ እንደነበሩ ተረዳሁ።አንቲዎርፕ እና ብረስልስ

በልብ ወዳጄ መሪነት፥ ከአንቲዎርፐን የ600 ዓመታት የምስረታ እድሜ ካለው፥ እስከ ብረስልሱ ‘ኤፍል ታወር’ አቶምየም፤ ከልዩ ኪነ ህንጻዎች እስከ አውሮፓ ኮሚሽን፤ ከቢራ ሙዚየም ደጃፍ፥ እስከ ጦር ሰራዊቱ ሙዚየም ውስጥ፤ ተዟሩረን አየን። የድንች ጥብስ (በተለምዶው ፍሬንች ፍራይስ የሚባለው፥ ቤልጂየም ውስጥ ደግሞ ፍሪትስ በመባል የሚታወቀው) እዚያ ለጉድ እንደሚበላ ታዝበን፥ “ለምን ነበር ቤልጂ ፍራይስ ያልተባለው?” ማለታችን አልቀረም። (ፈረንሳይን እስክናይ ድረስ ነው። 🙂 )የግራንድ ፕሌስን ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች እና የጎዳናውን እንቅስቃሴ አለፍ ስንል ያየነው፥ 400 ዓመት እድሜ ያለውን ‘manneken pis’ (a little man pee) ስመለከት ግን አንድ ቁም ነገር ተ
ሰማኝ። እዚያ አካባቢ ስለማኒከን ፒስ ይወራል። እንኳን ቦታው ደርሰው፥ ቤልጂየምን የሚያውቅ ሰው ‘ማኒከን ፒስን ሳታይ እንዳትመጣ’ ሊል ይችላል። ወይ ደግሞ በየጉዞ ማስታወሻው ስለማኒከን ፒስ ተዳንቆ ተጽፎ አንበበናል። – ሽንታሙ ልጅ ዝናው እንዲህ ነው።

secreto_manneken_pis_3173ቤልጂየማውያኑም ስለማኒከን ፒስ ሲያወሩ እንደትልቅ ቅርስ በኩራት ነው። ለዚህም ይመስላል፥ ዙሪያ ገባው ያሉ ቤቶች የማኒከን ፒስን ምስል ደጃፋቸው ላይ በተለያየ መልክ የሚያስቀምጡት። ከአሻንጉሊት ወይም ቁልፍ መያዣ አንስቶ፥ እስከ ግዙፍ ቼኮሌት ድረስ በማኒከን ፒስ ቅርጽ ተሰርቶ ሲታይ፥ ማኒከን ፒስ ያጓጓል። ደርሰው ሲያዩት ግን፥ ደቃቅነቱን ትታዘባላችሁ። ብዙ የተባለለት የሽንታሙ ህጻን ልጅ ሀውልት፥ 61 ሴንቲሜትር ርዝመት ብቻ ነው ያለው። ታዲያ ይዘመርለት ዘንድ፥ ትልቀትና እንሰት ምን ቦታ አላቸው? – የሚሸከመው ታሪክ እንጂ!

የመኪና ገበያ እና የእስልምና አስተምሮ ምርምር የሚደረግበት መስኪድ የሚገኙበት፣ ጁቤል መናፈሻ ግቢ ውስጥ የሚገኘው፥ የጦር ሰራዊቱ ሙዚየም ውስጥ ሲገባም ይህንኑ ነው የሚታዘቡት። ያልታወሰ የጦር መሪ፣ ያልተዘከረ ባለታሪክ፣ ቦታ ያላገኘ የጦር መሳሪያ ያለ አይመስልም። ሁሉም በወግ በወጉ፣ በስርዓት በስርዓቱ ተሰድሮ፥ እዩኝ እዩኝ ይላል። ታዲያ እንደኢትዮጵያ ካለች የ3000 ዓመት ባለታሪክ አገር ለሄደ ሰው ቁጭቱ ብዙ ነው። ‘ሁሉም የቀደመውን አጥፍቶ የራሱን ለማድመቅ በሚሽቀዳደምበትና የአገሪቱን የታሪክ ዕድሜ ለመቀነስ በሚራኮትበት ሁኔታ ስንቱ ታሪክ ተንኮታኩቷል? ስንቱ ባለታሪክ ተፈቅፍቋል?’ ያሰኛል። ዛሬም የታሪክ ሽሚያ ላይ መሆናችን ያንገበግባል።

‘አይ አምስተርዳም’

16782574_m
ስለአምስተርዳም በምስል ታግዞ የሰማ፥ ወይም አምስተርዳምን ያየ ‘I AmSterdam’ የሚለውን የተቀረጸ ጽሁፍ ያስባል። እኔ ገና ከአውሮፕላን ማረፊያው ወጥቼ ታክሲ ፍለጋ ስሄድ ነበር የተመለከትኩት። ኋላ ግን፥ ወደ ሴንትራል አምስተርዳም ዘልቄ፣ ውስጥ ውስጧን ጎራ ስል፣ ‘ቡና’ ቤቶቿን ስመለከት፣ በየጉራንጉሩ ስሽሎከሎክ፥ …በአማርኛ “አይ አምስተርዳም” አልኩ። – I AmSterdam!? 🙂የአመለካከት ለውጥ ውጤቶች

የሰው ሀገር በታየ ቁጥር ትዝ የሚለን የለምለሚቷ አገራችን ጉዳይ “አባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል”ን እና “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ”ን ያስታውሰናል። የአፈሩ ገራገርነትና፣ የአየሩ መልካምነት ሲታይ ደግሞ ስንፍናችንን ይበልጥ ያጎላውና፥ ያንገበግባል። ሌላው የትራፊክ መንገድ አጠቃቀም ጉዳይ ነው። እግረኛውና አሽከርካሪው ያላቸው ስርዓት፣ ትዕግስትና መናበብ ሲታይ ለአገር ይመኙታል። (ለምሳሌ፥ አቴንስ ውስጥ ያለው የመኪና ብዛት ለጉድ ነው። ግራቀኙ ሁሉ በቆሙና በሚንቀሳቀሱ መኪኖች መሞላቱ ገርሞኝ ስጠይቅ፥ “ነዋሪው 11 ሚሊዮን፣ የመኪናው ቁጥር ደግሞ 12 ሚሊዮን ነው” ተባልኩኝ። ታዲያ ግን ሁሉም ነገር በስርዓት ነው።)ሌላው ሳይጠቀስ መታለፍ የማይገባው ነገር፥ የቆሻሻ አወጋገድ እና የአካባቢ ንጽህና ጉዳይ ነው። ሁሉም ሰው በሀላፊነት ከሚሳተፍባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። የአካባቢን ልምላሜ መጠበቅ፣ የትራፊክ መጨናነቅን ማቅለል፣ እና ንጽህና፥ ከኑሮ መሻሻል ጋር ሊሻሻሉ የሚችሉ ቢሆኑም፥ ከድህነትና ከሀብት ጋር የሚያያዝ ቀጥተኛ ነገር የላቸውም። ከግንዛቤ ስፋትና ከአመለካከት ለውጥ ጋር እንጂ!

መመለስ

መሄድ ደስ ይላል። መሄድ ደስ የሚለው ግን መመለስ ስላለው ይመስለኛል።ረጅም እድሜ ለመሄድ!
ረጅም እድሜ ለመመለስ!