ዓለምዬ – “ናና”….

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና…

የሚለው የድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን አሪፍ ዘፈን ትዝ ብሎኝ፥ በስሜት ጆሮዬን imagesCA4BEEXZመምታቱን ተከትሎ፥ “ናና” ከረሜላ ባይኔ ላይ ዞረ። ….ናናዬ፣ ናና ገላ፣ ናንነት፣ ናኑ፣ የእኔ ቆንጆ፣ የእኔ ክብ ጠፍጣፋ፥ ጎማ መሳይ – ጉንፋን ከረሜላም ትባል ነበር – ….በ5 ሳንቲም ገዝተናት በልጅነታችን የ5 ብር ዓለም ታሳየን ነበር። ናና ከረሜላ (በወጣትነት የሴት ቻፓ ሰረቅ አድርገን አይተን ደስ እንደሚለን  🙂 ) ገና ሲያይዋት ጀምሮ ነበር የምታረካው። ….ለእኔ እንደዚያ ነበር።

ደግሞ አንዳንድ ጊዜ፥ ላይዋ ላይ የሆነ ጽሁፍ ይጻፍባት ነበር። ….ምን ነበር ዛሬ አግኝቼያት ባነበብኩት ኖሮ? ይኽኔ “የኔ አፍቃሪ ጩጬው ጆዬ፥ ዓላማዬ ዓለምህን ማጣፈጥና አንተን ከፍ ከፍ ማድረግ ነው።” ሊሆንም ይችላል’ኮ። ሄሄሄ…. ናና በእጅ ስትጨበጥም የልጅነት እጃችንን ሞልታ ታስጨንቀን ነበር። ….አትወድቅም እንጂ!፥ ድንገት አፈትልካ ከእጅ ላይ ብትወድቅ ደግሞ ቀድመናት መሬት ደርሰን፥ ተነጥፈን ነበር የምንጠብቃት። …በዚያ ላይ ‘ከእጅህ ወጥቼ ካልዋጥኸኝ’ ብላ ስትታገል። ትኩስ ምራቅ አፍን ሞልቶ በሀሳብ ሲጎትታት! ….ይምጣብኝ አቦ!….በዚያ ላይ ነጭነቷ። ምጵጣ! ምጵጣ!

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና…

የልጅነት ቀልባችን፥ ከረሜላይቱን…. ጣፋጭቱን…. መልከመልካሚቱን…. ማሪቱን….. ነጪቱን…. ክቢቱን…. ጎማ መሳይቱን…. ስኳሪቱን…. ወለላይቱን….. ናናይቱን……… በማየትና፥ በምላስ በኩል ለመቅመስ በመከጀል መካከል ሆኖ ሲሰቃይ፣ በአውራ እና በሌባ ጣቶች መካከል ጨምድደን ይዘናት፤ ከናካቴው ሳናስገባው — ኋላ እስክንኮረሻሽመው ድረስ — ምላሳችንን አሹለን እያወጣን ጎን ጎኗን ላስ ላስ እናደርጋትና የበለጠ እንጓጓ ነበር።

ጊዜዋ ደርሶ ጥቅልል ብላ ከአፋችን ስትገባ ደግሞ ጥፍጥናዋ ከመሬት ከፍ ያደርገን ነበር። ….ናና እየመጠጡ አየር ላይ መቅዘፍ ደስ አይልም? – እጥፍ ድርብ ሀሴት!ውይ ናና፥…. ወላ ልጅ እያለሁ “ህብስተ መና” ሲባል ናና ይመስለኝ ነበር። የሆነ ከሰማይ ወርዶ ለንጹሀን ሕፃናት የታደለች። ከንጹህ ልጅነት ትንሽ ከፍ ብዬ ብልጠት ምናምን ስጀማምርና ናና ከገበያ ስትጠፋ ሰሞን፥…. መጥፋቷ አጢሀት መስራት ስለጀመርን፥ መቀጣታችን ይመስለኝ ነበር።

የናና ነገር ከሱቅ መስኮት እስከቤት በራፍ ድረስስ የት ያስችልና?! ….በተለይ እንደ እኔ “መንገድ ላይ መብላት የሌባ ነው። ሰው ቤት ሲበላ የሚያሳፍረውን ነው መንገድ ላይ የሚበላው። ልክስክስ አትሁን….” እየተባለ ያደገና፥ አታድርግ የተባለውን ቢያደርግ “ያዝኑብኛል“ ብሎ የሚሰጋ ልጅ ላይ ስቃዩ ይበረታል። …..አቤት ከሱቅ እስከ ቤት ርዝመቱ (ይህን ያህል ነበር፥ > ——————————————————————————— ∞ )…. በጊዜ ከለካነው ደግሞ፥ ከሱቅ ቤት እስኪደረስ የነበረው ጊዜ፥ በሚጎትት ቴፕ እንኳን ሶስት “ዓለምዬ ናና” አዘፍኖ “ኮርናስሜ”ን ያስመርቅ ነበር፤…. ለያውም በአዩኝ አላዩኝ ላስ ላስ ታጅቦ ነዋ!……

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

ማጋነን እንደው ዴሞክራሲ መብታችን ነው! ሃሃሃ….

ኡኡቴ…..
ከሰው ሰምታ’ቴ፣….
ይህቺ ፈጣጤ፣
ኡመቴ፥
መጥታ ተኛች ከደረቴ!
ቴ ቴ….

ናና ከረሜላ ተመጥጦ ጣእሙ በጉሮሮ ሲወርድ ሕልም ይመስልና፥ ጉሮሮውን ሁሉ ገብቶ መላስ ያስመኝ ነበር። ናና የተጨበጠበት እጅ (በምራቅ ረጥቦ ከሆነ) መዳፍ ሳይቀር ያስልስ ነበር። ለእኔ እንደዚያ ነበረ።… ወላ የመጨረሻውን የናና ወለላ ከዋጥኩኝ በኋላ፥ በማጣጣም ምላሴንና ላንቃዬን (ምጵጣ! ምጵጣ! እያልኩ….) ሳማታና ወደ ውስጥ መጥጬ ስውጥ፥ ታፍኜ እንዳልሞት ሁላ እፈራ ነበር። (ብዬ ማጋነንና ማጋጋል መብቴ ነው። ሄሄሄ….)

የሰፈሩን እኩያ ቁጫጮች ለማስገበሩና ለማቁለጭለጩ ቢሆንስ፥ ማን እንደ ናናዬ? — ደጉ ዘመን በ5 ሳንቲም አለቃና ምንዝር ይበጁ የነበረበት! ፓ! ዛሬ “ናልኝ…. ናና…..” ቢሉት፣ ቢጠሩ ቢያንቆላጵሱት የት ሊሰማ? ….ኦ ልጅነት – ዓለም! ….ኦ ልጅነት – ጉብል! ….ኦ ልጅነት – የአገር ልጅ!

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

እኛ ቤት ደግሞ ናና ከረሜላ ለትንንሾቹ የደስታ ምንጭ ብቻ ሳትሆን፣ ለትልልቆቹም የጨጓራ ህመም መድኃኒት ነበረች። ከታላላቅ ወንድሞቼ አንዱ (ሶስተኛው) “ጨጓራዬን አመመኝ” ብሎ እርሷን ያስልክና፥…. ገና አፉ ስትገባ “እፎይ” ማለት ይጀምራል። (እኔን ሲልከኝ የናናው ዱቄት እጄ ላይ እንዲቀርልኝ መታ መታ አድርጌ፥ መዳፌን ልሼ ነበር የምሰጠው።) ….የናናን የፀረ አሲድነት ሀልዮት ቀድሞ ወደ ቤታችን ያመጣውም እርሱ ነው።

ከዚያ ሌሎቹ “ጨጓራዬን” ሲሉ አሳምኖ እያዘዘላቸው ተለመደች። ….ታዲያ ግን በ“ላንቺም አምጪ ለእኔም ስጪ” ዘይቤ ነበር። ለእነርሱ ያዝዝና ለራሱም ይመጣታል። ….የእኔ ናና፣ የእኔ anti-acid!– ይኸው ዛሬም ድረስ ሰው ጨጓራውን ሲታመም ትዝ ትለናለች።  ዛሬም ተልኬ እጄ ላይ ዱቄቷን አራፍጌና ሸቅቤ መስጠት ያምረኛል። አዬ… ዛሬ ማን ሸጧት ማን ሊሸቅብ?!

እንዲያውም ከእለታት ባ’ንዱ ቀን ‘ናና ኪኒን’ ክፉኛ አምሮኝ፥ “አይዞህ” ብለው ቢገዙልኝ ብዬ፥ “ጨጓራዬን አመመኝ” ብዬ ተንቆራጠጥኩኝ። አንቆራጠጡን አልቻልኩበት ሆኖ ነው መሰል ነቄ ብለው፥ “ምኑ ጋር ነው ያመመህ? ጨጓራ የቱ ጋር ነው? ” ብለው ማፋጠጥ፤…. እኔም ጉሮሮዬን ነክቶ ማሳየት! ወዲያው ቤቶቼ ከት ብለው ሲስቁና እኔ ሳለቅስ እኩል ሆነ። ‘ልጅ ስላለቀሰ ማባበል ያጨማልቃል’ የሚሉት ነገረ  ባትኖራቸው ኖሮ፥ ….ማባበያ፣ የእንባ ተከታይ ናና ይሆንልኝ ነበረ። ያን ቀን ግን እንዳማረኝ ቀረ።

ውሸት ይቅር ሲሉኝ፥
“አልሰማም አልኩና!”
አመለጠኝ ናና!….
እንባ ገዴ ናና፣
አረጣጥበኝና፥
አስገዛልኝ ናና! ሃሃሃ….

(እንደውም ግጥም የለመድኩት “ናና…ና” ስል ነው ምናምን ብዬ ልቀውጠው እንዴ? ሄሄሄ….)

ግን እኮ ያን ጊዜ ጨጓራዬን አሞኝ ነበረ። — የናና ጨጓራዬን አሞኝ ነበረ። አሁንም ናና ናፍቆኛልና ጨጓራዬን አሞኛል። ….ናና የጨጓራ መድኃኒት ከሆነ፣ የእኔ ጨጓራ ያለው ጉሮሮዬ ላይ መሆን አለበት። ….ናና የጨጓራ መድኃኒት ከሆነ፣ መላ የልጅነት አካላቴ ጨጓራ መሆን አለበት። ….መንፈስና ስጋዬ ጨጓራ መሆን አለበት። — እንዲያ ነዋ የሚያክመኝ። እንዲያ ነዋ የሚፈውሰኝ። አሁን ይህን ታይፕ ሳደርግም ጉሮሮዬ ላይ የሆነ ነገር ይላወሳል። ምላሴም ላደርስበት ይንጠራራል። – እንዲህ ነው ናና ትዝ ሲል!

ካደግሁኝ ወዲህ ዝም ብዬ ሳስበው ግን፥ ወንድሜ ምናልባት “እንደልጅ ከረሜላ ይመጣል” እንዳይባል የዘየደውና፣ ለሌሎቹ አቀብሏቸው፥ መሸሸጊያ ያደረጓት ታርጋ ትመስለኛለች። ….ወይ ደግሞ በናናው ረክተው “እፎይ” እያሉ አየር ወደ ውጭ ሲያስወጡ፥ የጨጓራቸው ህመም ቀለል እያለላቸው ሊሆንም ይችላል። ይሆናል። ….መቼስ አይሆንም አይባልም። ….ልጅ እንዳይበላው ሲፈለግ፥ ማርስ ያኮላትፍ የለ? ሄሄሄ…

ልጅ እያለሁ “ተስፋሁን” የሚባል ኮልታፋ የት/ቤት ጓደኛ ነበረኝ። ተስፋሁንን በጣም እወደው ነበር። ሲኮላተፍ ደግሞ የሆነ ከሌላ ዓለም የመጣ ነበር የሚመስለው። ….የገዛ ስሙን እንኳን “ሸሽፋሁን” ነበር የሚለው። (እንግዲህ እኔን ሲጠራ እንዴት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ነው። ….የሆነ እንደተበላሸ ቴፕ “ሽሽሽሽ….” ይላል።) ….ከዚያ እኔ አማረልኝ ብዬ፥ የፍቅሬን “ሼሾ” አልኩት። ስሙም ሼሾ ሆኖ ቀረ። ያኔ… እኔማ የተኮላተፍኩ መስሎኝ ደስ ብሎኝ ነበር። ”ማር ያኮላትፋል” ሲባል ደስ ብሎኝ፥ ጓደኛዬን ልመስል ተደብቄ ማር መላስ ጀመርኩኝ።

ስልስ ስልስ ስልስ…. ከእለታት በአንዱ ቀን ከሌላ ኮልታፋ ከማይሉት ገመድ አፍ ጋር ተዋወቅሁኝ። ውይ ሲያስጠላበት። እኮላተፍ ብሎ ስም ያበላሻል። አስጠላኝ። ኮልታፍነትም አስጠላኝ። ….ናና ግን አላስጠላኝም። እንዲያውም በብስጭት የናና ሻይ ማፍያውን ተክል ተክዬ፥ ከስመ ሞክሼው ናና ሻይ ጋርም ፍቅር ያዘኝ። የናና ቅጠል መዓዛ ደግሞ ሌላ ነው። ….ኮልታፋና ማር ግን አስጠሉኝ። ከዚያ ከራሴ አልፎ ተርፎ ጓደኞቼን ሁሉ “ማር አትላሱ” እያልኩ እሰብክ ነበር።

እናቴ “ማር ፀጉር ከተቀባ ያሸብታል። እንጂ ልጅ ቢልሰው አይኮላተፍም። ….የድሮ ሰው ራሱን ስለሚንከባከብና ልጆች ጣፋጭ ስለሚወዱ ልሰው እንዳይጨርሱበት የፈጠረው መላ ነው….” ብላ ከአባቴ ጋር ስትከራከርና ሲናደድ (ምናልባት ስለነቃችበት ይሆናል) ደስ አለኝ። እንዴት እንደተንተከተኩኝ አልረሳውም።…. በጣም ጣፋጭ ሳቅ ስለሳቅሁኝ የናና ጥርሶች የበቀሉልኝ መስሎኝ ነበር። ….ታዲያ ካላኮላተፈማ ከማር ጋር ምን ፀብ አለኝ ብዬ ልተወው? ….“ና ግባ በሞቴ” እያልኩ እልሰው ጀመር። እርሱን ሳስብ አሁንም ጥርሶቼ ባሉበት አረገዱ። አሁን ያማረኝ ማር  ግን ናና ነው። የመቀሌ ማር ዓይነት ነጭ፤ ግን ደረቅ ክብና ጠፍጣፋ። ናናዬ፥ የልጅነት ዓለሜ….  — ናና!

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

ናንዬን ግን የትኛው የከረሜላ ፋብሪካ ነበር የሚያመርታት? ማን ነበር የሚያስመጣት? አሁን ለምን ተዋት ታዲያ? ለነገሩ እዚህ አገር ደንበኞች እንደሚወዱት ከታወቀ ምርት ይቆማል። ለምሳሌ: አድጌ በጉሮሮዬ ሳንቆረቁራት ሙዚቃ የምጠጣ ይመስለኝ የነበረችው የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ያመርታት የነበረችው የቲማቲም ጭማቂ፥ ፈላጊዋ ሲጨምር (ምናልባትም እኔ ስለወደድዃት) ደብዛዋ ጠፋ። እኔም በናፍቆት ጉሮሮዬ እየተንቀጠቀጠ፣ በቅዳሜዎች እርሷን ፍለጋ ሱፐር ማርኬት ለሱፐር ማርኬት ሳስስ አረጀሁ። ….መቼስ ይሁና! እስኪ ናና ሻይ ፉት እያልን ብርዱን በ “ዓለምዬ ናና” ሙዚቃ እንሸውደውማ።

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

ኩታ ትወዳለህ መባሉን ሰምቼ፣
ይኸው እፈትላለሁ እንዝርቴን አንስቼ።
እንኳን ለሚወዱት አርሶ ለሚጭን፣
ለእንዝርት ይከፈታል የሸጋጎች ጭን።
ድማሙ መሸ እንግዲህ ደግሞ
ደማሙ ደህና እደር ወዳጄ….

የዘፈኑን ግጥም ቀጥሉልንማ። ወይ ደግሞ ዘፈኑን ወዲህ ክሉልኝ!DSC02890

ብታምኑም ባታምኑም:

ይህንን ጽፌ ጨርሼ ልለጥፈው ስል ለወዳጄ ፍፁም “ናፍቆኝ፥ ስለ ናና እየጻፍኩ ነው” ብያት ተሳስቀን፥ ሰው እንደሰጣት ነግራኝ ሃያ የሚጠጉ የናና ፍሬዎች አበረከተችልኝ። (ናንዬ Pepermunt በሚል ስም ታሽጋ ዓለሟን አይታ። ፍፄም ከሶስት እሽጎች አንዱን ለቀቀችብኝ) …..እኔ አሁንም አሁንም እየዋጥኹኝ አላበረክት አልኩት እንጂ!(በዚህች ቅፅበት እንኳን እጄ ላይ 11 ፍሬ ቀርቷል። – you see my hand?  🙂 ) ….የምንፈልገውን፣ የናፈቀንን ነገር እንጎትተዋለን ማለት እንዲህም አይደል? — ‘law of attraction’ ይልሃል ፈረንጅ!

ከናፈቃችሁት ጋር ያገናኛችሁማ!

ከገጠር ወደ ከተማ የሚሰደዱ ስሞች…

ስም መጠሪያ ነው። – አንዱን ከአንዱ መለያ! አፍ ላይ ቀለለ፥ ከበደ፤… ጣፈጠ አልጣፈጠ፥ ያው መጠሪያ ነውና በስም አንቀልድም። ይህንንም የምጭረው የማንም ስም ላይ ለማሽሟጠጥ (ወይም እንዲያሽሟጥጡ በር ለመክፈት)፣ አንዱን ከአንዱ ለማለካካትና ለማበላለጥ… ወይም በሌላ የተለየ ምክንያት ሳይሆን፥ አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ በቀለለኝ መልኩ ለመጫወት በማሰብ ነው። ይህን ከገለፅሁ ዘንዳ ጨዋታዬን ልቀጥል…
*
*
*
ብዙ ጊዜና ብዙ ቦታ ለሰው ልጆች ስም ሲወጣ እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም። በሆነ ዓይነት ምክንያትና ፍላጎት እንጂ! በማውቀው ልክ (በብዛት ካስተዋልዃቸው መካከል) የስም አወጣጥ/አመጣጥ ምክንያቶችን ልከፋፍላቸው ብል፤… በጣም ውድ (ብርቅ) በሆነ ነገር መሰየም፤ ለምሳሌ: – አልማዝ፣ እንቁ፣ ወርቅነሽ፣ ብርቄ፣ ብርነሽ፣….፥ ለአፍና ለአጠራር በሚጣፍጥ ቃል መሰየም — ትርጉሙን አወቁትም አላወቁትም! (ይሄ በማደግ ላይ ያሉ ከተማዎች ውስጥ ይዘወተራል።)፤…

ልጅ የተወለደ ሰሞን በሚፈጠር ህብረተሰባዊ ክስተት መሰረት መሰየም፤ ለምሳሌ: – ደርጉ፣ ነፃነት፣ አብዮት፣ ህዳሴ፣ ግድቡ፣ አባይ፣ ድሌ፣ ፋሲካ፣ ገና፣….፥ በአንድ ገናና ወቅታዊ ጉዳይ ወይም ግለሰብ ስም መሰየም፥ ለምሳሌ: አብዮት፣ ሉሲ፣ ሚሊኒየም፣ ዚዳን፣ ኦባማ፣….፥ ምኞትን፣ ተስፋን ወይም ፍላጎትን ለማንፀባረቅ በማሰብ መሰየም፤ ለምሳሌ: – ተስፋዬ፣ ይልቃል፣ ስንሻው፣ አንሙት፣ ፍላጎት፣ ደምመላሽ፣ ማለፊያ፣ ሰላም፣ ይበልጣል፣….

ፅድቅና መንግስትን በማሰብ፤ ለምሳሌ: – ቸርነት፣ ምህረት፣ ፃድቁ….፥ ለማመስገን፤ ለምሳሌ: – ምስጋና፣ ስጦታ፣ ፀጋ፣ እድላዊት፣….፥ ልጁ እስከተወለደበት ጊዜ ድረስ የነበረን ተድላም ሆነ ውጣ ውረድ ጠቅለል አድርጎ ለማስቀመጥ በማሰብ፤ ለምሳሌ: – ሙሉቀን፣ ስንታየሁ፣ ብዙአየሁ፣ ምንታምር፣ ነጋ….፥ ከኑሮ ጋር የሚደረግን ግብግብና ሁኔታውን ለመግለፅ በመፈለግ፤ ለምሳሌ: – በርታ፣ ጠንክር፣ አንሙት፣….፥ ቅዱስ መፅሐፍትን በማጣቀስ፤….

በእዚያ አካባቢ በሚመጡ እንግዶች ስም መሰየም (ለምሳሌ: – እኔ በምሰራበት አካባቢ ዶክተር የሚባል ልጅ ነበረ። ገርሞኝ ምክንያቱን ስጠይቅ እርሱ በተወለደበት ጊዜ ዶ/ር ገዛኸኝ የሚባሉ ሰው እዚያ አካባቢ ስለነበሩ ነው። እዚህ ጋር ፈገግታ የሚያጭረው “ዶክተር” እንደማዕረግ ስም ሳይሆን እንደ መጀመሪያ (መጠሪያ) ስም መወሰዱ ነው።)፤…. ወይም ሌሎች ብዙ ምክንያቶችን ተንተርሶ ስም ይወጣል።
*
*
*
ዛሬ መጫወት ያማረኝ ግን በጣም ውድ (ብርቅ) በሆኑ ነገሮች ላይ ተመርኩዘው (በሌላ ምክንያት ሳይሆን፥ ብርቅነታቸው ተወድዶ ብቻ) ስለሚሰጡ ስያሜዎች ነው። እንደሚታወቀው ውድነትና ብርቅነት፥ ብዙ ጊዜ፥… በተዘዋዋሪ ከገቢና አቅርቦት ጋር ይያያዛል። ወርቅ ውድ የሚሆነው ወርቅ እንደልብ በሌለበት ነው። ብር ውድ የሚሆነው ብር እንደልብ በሌለበት ነው።… ወይም ደግሞ የቁሶቹ ተፈላጊነት ከፍተኛ በሆነበት ቦታና ሁኔታ ነው።

የልብን ፍላጎት ለማሟላት ወይም የሚወዱትንና የሚሳሱለትን ልጅ — “እንደዚያ ውድ ነገር የከበርክ/ሽ” ለማለት ስያሜው ሊወረስ ይችላል። በዚህ አካሄድ አስበነውም፥ የሆኑ ዓይነት ስሞች ከገጠር ወደ ከተማ ሊሰደዱ እንደሚችሉ መገመትና መጫወት እንችላለን። …. ከገጠር ተሰድደው መምጣት ብቻ ሳይሆን እንደ አዲስ የሚወለዱትንም መጠርጠር ይቻላል።
ለምሳሌ: – ድሮ መብራት ብርቅ በነበረበት ዘመን፥ የከተማው የመብራት መስፋፋት ወሬ ወደ ገጠሩ ሲዛመት፥… ልጅን በውዱ መብራት ስም “መብራቱ፣ መብራቴ፣ መብራት ነሽ፣ አበራሽ፣ ፋኖሴ፣ ማሾ….” እየተባለ ይሰየም ነበር።

አበው ወእመው፥ “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ” እንዲሉ በሁኔታዎች የጎደሉ ነገሮችን በስያሜ ይሞላሉ። በዚህ ረገድ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል።ራሱ “ከተማ” ብሎ ስም፥ ሰያሚዎቹ ለከተማ የሰጡትን ነገር ሊያሳየን ይችላል። ዛሬ ግን ከተማው ውስጥ በየጊዜው በሚታየው የመብራት መጥፋት ችግር ምክንያት እነ ”አበራሽ፣ መብራቴ፣ መብራት ነሽ፣ ፋኖሴ፣ ማሾ….” ከተማ ውስጥ ለሚወለዱ ልጆች …የነገሩን ብርቅ ድንቅነት በማድነቅ ብቻ ተወስኖ… መሰጠት ይጀምሩ ይሆናል። ከውኀ ጋር በተያያዘም እነ “ውሃ ወርቅ” ወደ ከተማ መጥተው ለሚወለዱ ልጆች ስያሜ ይሆናሉ።

የድሮ ባላባት መውዜርና ምንሽሩን ይወለውል እንደነበር፥ የዛሬ የከተማ እመቤትና ጌቶች ለውሃ መቅጃ እቃዎቻቸው የሚያሳዩት እንክብካቤ ሲታይ፥…. ምናልባት ወደፊት “ቧንቧዬ፣ ባልዲዬ፣ መቅጃዬ፣ ሃይላንዷ፣ ጀሪካን፣ ለገዳዲ፣….” እየተባለ እንዳስፈላጊነቱ ሌሎች ውድ ስሞች ከውድ ልጆች መወለድ ጋር ሊወለዱ እንደሚችሉ ያስጠረጥራል።

“ንፁህ” ም ከጠፋበት ይገኝና እንዳዲስ ያገለግል ይሆናል። እነ “ጥም ቆራጭ” የሚሉ ስሞችም ይወለዱ ይሆናል። ….ከስልክ አገልግሎት መስፋፋት ጋር የተሰጡ ስሞች መኖራቸውን ከዚህ ቀደም ሰምቼ ባላውቅም፣ ነገሩ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን “ኔትወርኬ” የሚል ስም በቅርቡ በሽ እንደሚሆን እንጠረጥራለን። 🙂

ያው ጨዋታ ነው! – ግን ብሶት ወለድ ጨዋታ!

በገጠርና በከተማ መካከል ግን ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ውጭ ምንም ልዩነት እንዳይኖር አገልግሎቶች በጥራትና በብዛት ይሟሉ ዘንድ እንማፀናለን!

እስኪ እናንተም ጨዋታውን ቀጥሉበት… አርብም አይደል?! 😉

መልካም የእረፍት ቀናት!

 

 

 

 

 

 

 

“የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards

ሰርግና ሙዚቃው

“ሙዚቃ እያሰሙ ገደል ይከቱታል።” የምባል ዓይነት ነኝ። ከየትኛውም ዓይነት ሙዚቃ ጋር መንፈሴን ልክክ አድርጌ ሌላውን ነገርና አካባቢዬን መርሳት እችላለሁ። ልክ የብርሃን ልክፍት መፅሐፍ ላይ ገፅ 60 ላይ በ“ፍቅሬ ሙዚቃዬ” እንዳልነው ዓይነት መሆኑ ነው….

“ሀገር ቢደባለቅ፣ ቢዘነብ ቢባረቅ፣
ቢተኮስ ቢደለቅ፣ ቢነጠፍ ቢወደቅ፣
ቢበተን ቢሰፋ፣ ቢወረቅ ቢጨረቅ፣
ቢከፈት ቢገለጥ፣ ቢቀበር ቢደበቅ፣
ቢታረስ ቢዘራ፣ ቢታጨድ ቢወቃ፣
ቢታዘል ቢታቀፍ፣ ቢጎሸም ቢደቃ፣
ውድሽ መች ልሰማ?!”

/ዮሐንስ ሞላ – የብርሃን ልክፍት ከገፅ 60 ላይ የተቀነጨበ/

በዚያም የተነሳ ይመስላል፥…. በስምና በመደብ ዓይነት መተንተኑን ባልካንም፥ ራሴን ደስ በሚያሰኘኝና ደረቴን በራሴ ፊት በሚያስገለብጠኝ (በሚያስናፋኝ) ልክ ሙዚቃ እንደምረዳም አምናለሁ። ሄሄሄ…. “ሁን” ተብዬ ተማክሬ ባውቅ ኖሮ “ሙዚቀኛ” ነበር የምለውና የምሆነው። በርግጠኝነት “ይህን በሆንኩ ኖሮ” ብዬ በማስብበት የትኛውም ቅፅበትም “ሙዚቀኛ በሆንኩ ኖሮ” ማለቴ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዝብኛል።…

ቢቀዳ ቢደፋ፣ ቢታረድ ቢበላ፣
ቢበጠር ቢነጠር፣ ቢሰጣ ቢቆላ፣
ቢሰባበር ባላ፣ ቢፈራርስ ገላ፣
ሕዝባ’ዳም ቢሸበር፣ ቢታመስ ከተማ፣
ሺህ ቢወድቅ ቢገደል፤ ቢቆስል ቢደማ፤
ሀገር ቢበረበር፣ ቢወረር ባድማ፤
ውድሽ መች ልሰማ?!”

/ዮሐንስ ሞላ – ላይ ከተቀነጨበው የቀጠለ/

አሁንም ቢሆን እንደ ኃይለኛ ህልም ውስጥ ገብቼ ምናምን ሳስብ …ራሴን የሆነ ጊዜ ላይ፣ የሆነ ቦታ ላይ፣ የሆነ ዓይነት ሙዚቃ ራሴን ችዬ ስጫወት አየውና ሳቅ ያፍነኛል፤ ደግሞ ጊታር ነው የምጫወተው… የምጫወተው ለህዝብ ይሁን ለራሴ እንደሆነ ሳልለይ ግን ህልሙ እልቅ ይልና ብንን እላለሁ። ስለሙዚቃ ሌላ ጊዜ እንጫወታለን፥ ዛሬ ግን ወደ አሰብኩት “የሰርግ ሙዚቃ” ወሬ ላሽ ልበል።

የሰርግ ሙዚቃ

ሰርግ አልወድም። የሰርግ ሙዚቃ ስሰማ ግን በሆነ ርቀት ልክ ከፍ እላለሁ።13792785-wedding-picture-bride-and-groom-in-love የሆነ ነገር መጥቶ ውርር ያደርገኝና ልቤን ያሳክከኛል። ወደ ሆነ የማላውቀው ቦታ ይወስደኝና ይመልሰኛል። ከዚያ ስመለስ ደግሞ ወደ ሆነ በትንሹ የምፈራው ቦታ ያደርሰኛል። የምፈራው ስለማላውቀው ነው። አብሮኝ የሚጓዘውን ሰው ምንነትና ከየትነት መንገር ስለማልችል ነው። ግን ያው ሲለመድ ይረሳል። ሙዚቃውም እየበረታ ሲሄድ ነገር ዓለሙን ያዘነጋልና ፍርሃቱም እንግድነቱም ቅፅበታዊ ነው።

ልጅ እያለሁ ከሰፈር ርቄ ወደ ማላውቀው ቦታ ከጠፋሁባቸው ምክንያቶች ከሌላ ሰፈር የሚመጣን የሰርግ ሙዚቃ ተከትሎ መሄድ— ይገኝበታል። ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ የሰርግ ሙዚቃ ተከትዬ ጠፍቼ አውቃለሁ። (ሙሾ ተከትዬም ጠፍቼ አውቃለሁ። እርሱን ሌላ ጊዜ እንጫወት ይሆናል።) ሰፈር ውስጥ ሰርግ ካለ ከጓደኞቼ ጋር ደጃፉ ላይ ነበር የማመሸውና ቤት ደስ አይላቸውም። ባይላቸውም ግን እየተቆጣሁም ቢሆን ሄጄ አመሻለሁ። ….ልቀላውጥ! ምግብ አይደለም… የሰርግ ሙዚቃ ልቀላውጥ!

ልቤ “ውድሽ መች ልሰማ?” ማለቱን ይቀጥላል!– በኩራት ከፍ ብሎ!

ሙዚቃውም ቀጥሏል…..

“ዲን ዲን ዲሪሪን
ዲን ዲን ዲሪሪን….
የወይን አበባዬ፣ የወይን፣
የወይን አበባዬ፣ የወይን፣
እኛም ወደናል ትሁን።”

አፅዳቂና ፈቃጅም አለ ማለት ነው። ግን ባይወዱ ኖሮስ….?! ውዷ መች ሊሰማ?!

“ሙሽሪት ባንድ አልጋ፣
ሙሽራው ባንድ አልጋ፣
መልአክ ይመስላሉ፥
ክንፉን የዘረጋ።….”

ከሙዚቃው ጋር ልቤ ቅልጥ ይልና፣ ሊቀየር ጋብ ሲል ልቤ ይጠይቃል። “ለምን በአንድ አልጋ በአንድ አልጋ ይሆናሉ? ሰርግ አይደል እንዴ? ክንፋቸውን የዘረጉ የሚመስለው አብረው ለመሆን ስላኮበኮቡ ነው? ለምን ጊዜ ይገድላሉ?….አብረው አይተኙምና ክንፉን የሰበሰበ መልአክ አይመስሉም?” ምናምን ምናምን…..

“አናስገባም ሰርገኛ፣
እደጅ ይተኛ….”

የሚለውን ሲሰማማ ልቤ በሳቅ ይፈርሳል። ማጨብጨቡን ትቶ ይበሳጫል። “ምን ያካብዳሉ?….ለምን ያስመስላሉ?“ ምናምን እያለ ብቻውን ይቆዝማል። ኧረ እንዲያውም ልጅ እያሁ “አናስገባም” የሚል ግጥም ፅፌ ነበር። (በኋላ ማስታወሻ ደብተሬን ፈልጌ እከልማትና፥ ብቻዬን እስቃለሁ።)

ሙዚቃው ቀጥሏል….

የሰርግ ሙዚቃ እውነተኛ ዳኛ ነገርም ይመስለኛል። “ማነሽ ባለተራ?” እያለ ሁሏንም እኩል ያንቆላጵሳል። ባለተራ የሆነችውን ሁሉ በውዳሴ ያቀላልጣል። ሚዜ አይቀረው፣ ቤተሰብ አይቀረው… ጎረቤትና ጓደኛ አይቀረው… አማረች አላማረች ጉዳዩ አይደለም። ወፍራም ብትሆንም ”ችብ አይሞላም ወገቧ“ ይባልላታል። እናቷ ፈትለው ባያውቁም ”እናቷ ፈታይ እንዝርት ሰባቂ“ ይባልላታል።…. ዓለሟ ነዋ!

“ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ፣
እቴ ሸንኮሬ….”

እያለ ማቀላለጥ ነው። እህ…. የራስ ዓለም ከሆነ ማን ምን ሊያገባው? ኧረ ማንም! የሰርግ ዘፈኖቹ ይውረዱ፣ እኛም ከአልጋችን እንውረድ። ዛሬ የሁለት ከባባድ ወዳጆች ሰርግ አለብኝ!
.
.
.

“ኦሆ… የቤተ ዘመዱ፥
ይታያል ጉዱ!
ኦሆ… ዘመድ ነን ያላችሁ፣
እስኪ እንያችሁ!
ኦሆ… ጓደኛን ያላችሁ፣
እስኪ እንያችሁ!

እስክስ… እስክስ…
እንዲህ… እንዲያ…
.
.
አይፈራም ጋሜ አይፈራም፣
ወገብሽ ልክ አይሰራም፤”

ሠናይ ቀዳሚት!

የብርሃን ልክፍትን ለመግዛት ከታች ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards

አድዋ – የሰው ልጅ ክቡር!

battle-of-adwa-1896ጂጂ “GIGI” የሚለውን 3ኛ አልበሟን በልዩ አዘጋጅታ፥ በደግነት ካበረከተችልን ጊዜ አንስቶ …ሁሌም ማለት ይቻላል… ለአድዋ ድል በዓል እለት ከእንቅልፌ የምነቃው በእርሷ ሙዚቃ ነው። ኧረ እንደውም በሰማኋት ቁጥር እንዳዲስ አድዋን አድዋን ታሸትተኛለች። ከልቤ ላይ የሆኑ ነገሮችን እየነቀለች በቦታው ላይ ሌሎች ነገሮችን ስትተክል አያታለሁ። አልከለክላትም። ደስ ይለኛል። እንዲያውም “ካህንዬ”ን ልሸልማት ይዳዳኛል። ምን ላርግ? ‘ልብን የሚመረምርና ከአንጀት ዘልቆ የሚገባ፥ ቃል ካንደበቷ እንደውሃ፣ እንደጅረት ሲፈስ’ሳይ?! እንድትል: –

♪♫ቃል ካንደበቱ እንደውሀ፣ ይፈሳል እንደ ጅረት፣
ልብን የሚመረምር፣ ዘልቆ የሚገባ ካንጀት ♪♫

ቀላል ከፍ ታረገኛለች አሃ?! ያየሁ… የነበርኩ… ታስመስለኝና በእጥቅ ኩራት ትሞላኛለች። “በደስታ፣ በፍቅር፣ በክብር፣ በድል” (በዜማ) ታራምደኛለች — ራሴው ባቀናሁት የሀሳብ ጎዳና ላይ፣ በመስመር…! በቀደምት ጀግኖች በተሰመረ ጠንካራ መስመር። የደምና የአጥንት መስመር። አስታውሳለሁ፥ አምናም “አድዋ” እየዘፈንኩ ነበር የነቃሁት። እንደነቃሁም ‘ የሆነ የሆነ ነገር ተጫውቼ ነበር። በከፊል እንዲህ ይቀነጨባል: –

ዛሬ ከእንቅልፌ የነቃሁት ይህንን ሙዚቃ እያንጎራጎርኩ እና የአድዋ ጦርነት እንዴት እንደ ነበረ በዐይነ ህሊናዬ ለመሳል እየሞከርኩ ነበረ። የተሰማኝም ስሜት የተለየ ዓይነት ሆኖ ፍፁም የሚያም ነበር። ልብን የሚሰብር አስቀያሚ ስሜት። ዓመት በመጣ ቁጥር ቀኑን ከመዘከር ውጪ፥ ስለኛ ነፍሳቸውን እንደከፈሉልን ቀርቶ እንዳልከፈሉልን አድርገን እንኳን መክፈል አልቻልንም። አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስህተት፣ ስለኛ የፈሰሰውን ደማቸውን ችላ ብለነዋል። ጥለን የምንሄደውን ሀብት ለማካበት ስንሽቆጠቆጥ፥ ዛሬም በወኔ ቢስነት አለን። ዛሬም የራሳችንን ክብር አሳልፈን ሰጥተናል። ትናንት አንድ ወዳጃችን  ተገርሞ ያደረሰን ወሬ፥ ከነውሮቻችን ባህር ውስጥ በማንኪያ ሲጨለፍ ነው። እንዲህ ነበር. . .

ሸገር ኤፍ ኤም ላይ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እየተናገሩ ነው። የሚያወሩት በአዲስ አበባ ለግንባታ ሲባል በየቦታው በተቆፈሩ ጉድጓዶች ምክንያት ስለሚያደርሰው አደጋ ነበር። እናም ባለፈው ዓመት ብቻ 10 ሰዎች ጉድጓዶች ውስጥ ወድቀው መሞታቸውን ገለጹ። ለጥቀውም “በጣም የሚያሳዝነው”አሉ “በጣም የሚያሳዝነው የውጭ ዜጎችም በዚህ ምክንያት መሞታቸው ነው። ይህ ደግሞ ለገጽታችን….”

 ከዚህም በላይ ብዙ ብለናል። ከዚህም በላይ ብዙ ሰምተናል።… በርግጥ እንግዳን ማክበሩና መንከባከቡ ጥንትም የነበረ ባህልና ማህበራዊ እሴታችን ነው። ግን እርሱም ራስን በማዋረድ ወጪ ሲሆን ያስጠላል። ለተከባሪውም ቢሆን አስቀያሚ ሽንገላ ነው። ደግነቱ ቅሌታችን በአማርኛ ነው። ለራሳችን በሰራነው ቋንቋ።  ዓለምን በቀደምንበት መግባቢያ። እንደ እኔ ግን….ዛሬም ወኔ ያስፈልገናል። ከአባቶቻችን ድል ወኔ መቅዳት ግድ ይለናል። ከአድዋ ድል መማር አለብን።

በአካሉ ጣሊያንን ባይሆንም ብዙ ማባረር ያለብን ጠላት አለ። ዛሬም የአድዋ መንፈስ ነፃነታችንንና በኩራት ቆሞ መሄዳችንን ትናፍቃለች። እርስ በእርስ መከባበራችንና መተባበራችንን ትወዳለች። መሪዎቻችንም፣ እኛ ተመሪዎቹም አድዋን መዘከር ብቻ ሳይሆን እንደ አገባቡ በሚመች መልኩ ልንኖረው ይገባናል። ባፈሰሱልን ደም ፊታችንን ታጥበን፣ ከጠፈረን የዱካክና የእንቅልፍ ስሜት መላቀቅ ግድ ይለናል። የጂጂን ሙዚቃም በእንደዚያ ዓይነት የአካልና የአእምሮ ሁኔታ ላይ ሆነን በጋራ ስናቀነቅነው ይበልጥ ይጣፍጣል። ….ይህ የእኔ ሀሳብና ምኞት ነው!

  • በነገራችን ላይ: – ሰሞኑን የአባይን ግድብ በተመለከተ ሳውዲአራቢያ ለእነ ግብፅ ወግና፥ ኢትዮጵያ ላይ ስንትና ስንት ማሽሟጠጦች አድርጋ ሳያባራ/ሳይረሳ፣ ቁጭቱም ብስጭቱም ሳይለቀን… በመነጋው (ከትናንት በስትያ) ጠሚው ሃይለማርያም የሳውዲ ልኡካንን ጠብ እርግፍ ብለው አቅፈው እየሳሙ ማስተናገዳቸው አይረሳም። ያም ሳያንስ አብረው ሆነውም የአትክልት ዓይነቶችን እያዩ ሲምነሸነሹ ነበር።  እንዲህ ሆነናል እኛ! አድዋ ተዘንግታለች!!

ዛሬም ከያኒዋ በአድዋ ዜማዋ ትጮሃለች: -…

♪♫ የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆንኧ ክቡር
ሰው ሞቷል – ሰው ሊያድን፣
— ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፥ ሰው ሊኖር — ሰው ሞቶ፤” ♪♫

. . . እያለች፣ የሰው ልጅን ክቡርነት አንስታ፥ የተከፈለለትን የሰው ህይወት ዋጋና የተከፈለበትን ምክንያት በውብ ትርክት እያወሳች ስታንቆረቁር ቀሰቀሰችኝ።… ለማንም አላጋጭ ፊት ላለመስጠት በቁጭት የምታስታውስም ይመስላል።

ለነገሩ እኔና ቅዳሜ ቀስቃሽ አናጣም። ብናጣ ብናጣ “ስብሰባ እንዳትቀሩ፣ ምርጫ ካርድ ውሰዱ፣ የኮብል ስቶን አዋጡ፣… ምናምን” ብሎ በቅስቀሳው የሚያበሳጨን ቀበሌ አናጣም። ተሰብስበን እንዲያገኙን ብለው ነው መሰል፥ እንደ ልብ ወዳጅ የእረፍት ቀን ጠብቀው ነው በራችንን የሚቆረቁሩት። የአደረ የኢቲቪ ወሬ አናጣም።…

በአዘቦቱ በመቀስቀሻ ደወል (alarm) ቀድመን የምንነቃባቸው ድምፆች ሁሉ ቅዳሜ ሲሆን ሊቀሰቅሱን ይበረታሉ። የመንደርተኛው ጫጫታ፣ የባለ ምስሩ “አለ ምስር ምስር ምስር….” ድምፅ፣ የዐይነ ስውሩ የኔ ቢጤ

“ዐይኔን ግንባር ያርገው ብላችሁ አትማሉ፣
ይቸግር የለም ወይ መሪን ማባበሉ?!”

…አሳዛኝ ወ ሸንቋጭ እንጉርጉሮ፣ የቀን በሌዎቹ “ቆሻሻ አውጡ” ተማፅኖ፣ (ከቆሻሻው ጋር እንጀራቸውን እያሰቡ) የባለ ሱቁ የለስላሳ ጠርሙስ ለቀማ፣ የቤተስኪያናቱ ደወል…

“ቀን በቀን ተፈጭቶ፣ ቀን በቀን ተቦክቶ፣ ቀዳሚት ስትመጣ፣
የሚሰማ እንጂ፣ ቀስቃሽ መች ቸገረ?፣ ‘ሚጋግር መች ታጣ?!”
/ዮሐንስ ሞላ/

ያልነውም በቅዳሜው ነው። የአዘቦት ቀናቱ ሲገፉልንና የእረፍት ቀናችን ሲመጣ ቀስቃሹ ብዙ ነው። ጋጋሪው፣ አቃጣዩ፣ ጠባሹ ብዙ ነው። ወይ ደግሞ በ“መቼስ ማልጎደኒ” ብሂል ችለን ኖረን… ኖረን… ኖረን… ቅዳሜ ሲደርስ ይሆናል የሚሰሙን?! ይበልጥ የሚቆጠቁጡን?! – ምናልባት?!
— እንደ እኔ ነው!

ድካሜን ይበልጥ የምረዳው ስራዬን ጨርሼ ሳርፍ ነው። የመታፈኔ/ዝም የማለቴ ልክም መናገር ስጀምር ይበልጥ ይታወቀኛል። ከንፈሮቼ እርስ በርስ እየተነካኩ እንደኩበት ሲንኮሻኮሹ ተጠባብቀው ዝም የማለታቸው ነገር ይታያል። ቅዳሜ ቀን …በፈቃዴ… አንፃራዊ ነፃ እሆናለሁ። እናም መታፈኔ ይበልጥ ይሰማኛል። በፍፁም ነፃነት፣ ኩራትና ክብር በመንቃቴ ስሜቴን ካለፉት ቀናት ጋር ሳነፃፅረው የመታፈኔ ልክ ይጎላል።

ብዙ ድምፆች ጆሮዬ ስር ተኮልኩለው መጥተው ይጮሁብኛል። ይቀሰቅሱኛል። የአብዛኞቹ መቀስቀስ ማስጠላት የለውም። ማንቃትና ቀኔን የማራዘም ስራ ነው የሚሰሩት። እንዳሳርፋቸው ነው የሚማፀኑኝ። (ላልችልበት)… እነሆ ዛሬም ነቅቻለሁ። ዛሬ ግን ድል፣ ኩራት፣ ክብር፣ ነው የቀሰቀሱኝ። አደዋችን ከቅዳሜያችን ጋር ገጥበው ድርብ በዓል ሆኖ፤ እያንቆላለጩኝ! ‘ብትነሳ ይሻልሃል። ቀንህን አታባክነው።’ ዓይነት። እንድትማፀን ጂጂ: –

♪♫ እምዬ እናት ዓለም እስኪ አንቂኝ ከእንቅልፌ፣
ቀኔን ሳላሳምር እንዳልቀር ሰንፌ፣
ቤቴን ሳላፀዳው እንዳልቀር ሰንፌ…♪♫

ወይ ጂጂ! በእውቅ የሙዚቃ አዋቂዎች ተቀምሞ ለ50 ሰከንዶች የሚንቆረቆረው መግቢያ የሙዚቃ ቅንብር እዚያው አድዋ ነው ወስዶ ጠብ የሚያደርገኝ። አልጋዬን ሳልለቅቅ ሩቅ ተጉዤ፣ ከድል አምባዬ… ከአድዋዬ… ከመመኪያዬ… ከማስፈራሪያዬ… እደርሳለሁ። ሾፌሩ – ሙዚቃ፣ ከሙዚቃም – የጂጂ ሲሆን ደግሞ ለእኔ መንገዱ ሌላ ነው። አልጋ ባልጋ ሆኖ ታሪክ ዘካሪ ሳይሆን፣ ታሪክ መስካሪ ያደርገኛል።

♪♪ የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካአጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፤ ♪♪

…ያየ የነበረ ያህል ነው የምትነግረን። ደግሞ ወዲያው እኛንም ያየ የነበረ የምታስመስለን። ደግሞ የሚጠራጠር ቢኖር ምስክር ትጠራለች። ምስክር ስትጠራ ሰው (ጀግና) አይደለም። ጀግኖቹማ ተሰውተዋል።… አደዋን ነው። አገሯን ነው። ኢትዮጵያን ነው። “እንዴት ፊታችሁ ቆሜ በኩራት እንዳለሁ አድዋ ትንገራችሁ። ጠይቋት እስኪ… አገሬ ትዘክዝክላችሁ።” ትላቸዋለች።

♪♫ በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኧው በቀን በቀን
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን። ♪♫

…ስትል ደግሞ መከራና ሰቀቀኑን የተከፈለውን መስዋዕት ሁሉ ታወሳለች። የምታመሰግንም ይመስላል። ‘እኔ በየቀኑ ልኖር እነሱ በየቀኑ ሞቱ’ ዓይነት ጥልቅ ምስጋና። የአድዋ ድል ቀጣይነትንም ታስረግጣለች። የወዳደቁና መነሳት የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉም ትጠቁማለች። ታመሰግናለች። እንዲህ ስትል: –

♪♫ አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣♪♫

የድሉን ወሰን የለሽነትና ለመላው ጥቁር በረከትነት ደግሞ እንዲህ ቅልብጭ አድርጋ ታስቀምጠዋለች። አፍሪካን በእማማ ኢትዮጵያ መቀነትነት ሸብባ በአንድ ትመቀንተዋለች። አሁን ምስክሯን ስታጠናቅር ሰፋ አድርጋው… አፍሪካንም ትጠራታለች። ‘ምን አሰፈራሽ? ተናገሪ እንጂ።’ እያለች ትወሰውሳታለች። ‘አንቺ ካላወራሽው ማን ያወራዋል? ሰው እኮ ከንቱ ነውና ይረሳዋል።’ መሆኑ ነው። ‘ዛሬ ግን ምን ሆነን ፈዝዘናል?’ የምትልም ይመስላል።

♪♫ የጥቁር ድል አምባ፣ አድዋ
አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ… የድል ታሪክሽን አውሪ። ♪♫

የዛሬ ዓመት “የታሪክ አልጋችን” ብዬ የፃፍኩትን ግጥም ልጎትተውና መልካም ቀን ተመኝቼ ጨዋታዬን ላብቃ።

ከታሪክ አልጋ ላይ፣ በምቾት አርፌ፣
የኋሊት ስጋልብ፣ በሀሳብ ተንሳፍፌ፣
በምኞት ቃዥቼ፣ በተስፋ አንኳርፌ፣
ሰርክ ስንጠራራ፣ ደክሜ፣ ሰንፌ፣
አለሁ — እንደተኛሁ…
…ገፅ ልገነባ፣ ገፅ እያበላሸሁ፤
ፍቀድ አባታ’ለም !
__ቀስቅሰኝ ከንቅልፌ፣ ገፅታዬን ገንባ፣
ወኔህን አስቀዳኝ !
__በደምህ ታጥቤ፣ ድል አ’ርጌ ልግባ።
/ዮሐንስ ሞላ/

ሙዚቃው ይቀጥላል…
…የአድዋ ድል ስሜትም!!

♪♫ የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆንኧ ክቡር
ሰው ሞቷል – ሰው ሊያድን፣
— ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፥ ሰው ሊኖር — ሰው ሞቶ፤ ♪♫

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

541417_10200632967135850_273434459_n

ማስታወሻ:

አንጋፋውና ውዱ ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህ የዛሬ ዓመት በዚህ ቀን ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። የካቲትና የአገር ባለውለታዎች ሞት ግን ምንድን ነው የሚያገናኛቸው? 😦

ነፍስ ይማር!!

ኮብል ስቶን ስትለክፈኝ….

የውድ እህቴ፥ ውድ ባለቤት ቀስቅሶኝ ነገሬን በ‘ነበር’ ባያስቀርብኝ ኖሮ… ዛሬ ጠዋት አርፍዶ መነሳት ነበር እቅዴ። ከእንቅልፌ ሲቀሰቅሰኝ፥ ከሞት የመንቃት ያህል ከብዶኝ ነበረ። ሆኖምለዛሬ…ቀጠሮ የያዝንለት ጉዳይ እንዳለን ሳስታውስ፥ ሳላንገራግር ከመነሳት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረኝምና ተነሳሁ።… ተነስቼም ከቤት ወጣሁ።…. እስካሁንም ከተማውን ሳስስ አለሁ።

ዛሬ ጠዋት…

ፊቴን ታጥቤ ከቁርስ በፊት ከቤት ወጥተን ወደ ጉዳያችን ቢሮ አመራን። ሆኖም ግን ጉዳያችን ያለበት ቢሮ ቦታው አልነበረም፡፡…. ማለቴ ባለቢሮዋ ቢሮዋ ውስጥ አልነበረችም። ከብስጭት በፊት ድንገት አርፍዳ እንደሆነ ብለን  ጎረቤት ቢሮ ጠየቅን።  “ዛሬ አልመጣችም…. ሰኞ ትመለሱ ተባልን፡፡” (በትህትና እና በቀጭኑ) ከትናንት ወዲያም ለዚሁ ጉዳይ ወደ ቢሮዋ ሄጄ አልነበረችምና ሰኞ መመለሷም አጠራጠረን። በመሆኑም ለጎረቤቱ ባለቢሮ ነገሩን አስረድተን ስለሁኔታው ለማጣራትምንም… ምንም አያውቅም፡፡ እሱ እቴ!  ጭራሽ…”ከትናንት በስቲያ እኮ ቢሮው ክፍት ነበር። አልመጣችሁም።” ብሎ ሸመጠ፡፡

ያን በካደበት ሁኔታ ላይም እሱን ማመኑ ከባድ ነበርና እኔ ቆይቼ ልመለስ ተስማምተን ከእህቴ ባል ጋር ተለያየን —
የእህቴ ባል ወደ ስራ….
እኔ ወደ ቤት…
“ወደ ቤት…
ወደ ማድቤት…
አንድ እንጀራ ለጎረቤት…”

ወደ ቤት የተመለስኩት ቁርስ ለመብላት ነበር፡፡ ከዚያ በልቶ ለመመለስ፡፡ ከዚያ በኋላ፥ ሲሄዱ…. ሲሄዱ… ሲሄዱ… እንዲሉ፥ እኔም ስሄድ… ስሄድ… ስሄድ… ለኮብልስቶን ስራ በየቅያሱ ወደተቆፋፈሬው ሰፈሬ ተቃረብኩኝ። ስሄድ ያልታወቀኝን ያህል ስመለስ ቀፈፈኝ። በየቅያሱ ያልተቆፈረ መንገድ ለማግኘት እንደነዳጅ (ወይ ማዕድን) ፈላጌ መቆፈር ያሰኝ ነበርና ከተቆፈሩት በአንዱ ገባሁ። መቼስ ማልጎደኔ?!…
“አልበር እንዳሞራ፣ ሰው አርጎ ፈጥሮኛል፣
አንተን ባጣሁ ጊዜ ግራ ይገባኛል፡፡” ሃሃሃ….

ይሄንን ዜማ በጠዋቱ የመዘዝነው ከቁርስ በኋላ ለምናገኛት ቡና ማንቆላጰሻ ነበር። ውይቡንዬ…ቡኒ…ቡና…ቡን…፤ ድብርታችንን ሁሉ ቡን ለማድረግ፣ ሳንጨርሰው የወጣነውን እንቅልፍ ቦታው ላይ ለመበየድ፣ እንዲሁም ቀናችንን ለማንቃትና ለማቃናት…. ቡና ጥሩ መላ! ብለን ነው። ቡና የመጠጣቱ ሀሳብ ነበር መንገዴን ያስቀየረኝ: ከወደ ቤት –> ሰፈር ወዳለ ሆቴል —> ከዚያ ፊትለፊቱ ወዳለ ቡናቤት —-> ከዚያ….

ሀሳቤን እንዲያ ብቀይርም መንገዱ ግን ያው በየመውጫ መግቢያው እንደተቆፋፈረ ነው። አማራጭ ባጣ፥ ከተቆፈሩት ካንዱ ወጥቼ ወደተቆፈሩት ወዳንዱ ዘለቅሁኝ፡፡ ከወዲያኛው የመንገዱ ጫፍ ሰዎች ቆመው ያየሉ፡ ወጣቶች… እናቶች… አባቶች… የትምህርት ቀን ስለሆነ ለአቅመ ት/ት መማር የደረሱ ህፃናትና ወጣቶች ሲቀሩ ከሁሉም አይነት ሰው ተኮልኩላል።

መጀመሪያ ጠብ ተፈጥሮ መስሎኝ…. የተፈነቃቀሉትን ድንጋዮች እያሰብኩም ‘ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው!’… በለው! ብዬ በልቤ ሳጋግል ነበር፡፡ ከዚያ ግን ከግርግሩ ጎን የቆመ የጭነት መኪና ላይ ድንጋዮች እየተጫኑ እንደሆነ ሲገባኝ፥ ከመሀላቸው አንድ ቻይናዊ የመንገድ ሰራተኛ እንዳለ ጠረጠርኩኝ፡፡ መቼስ የእኛ ሰው ቻይኖች ሲሰሩ ማየት ይወዳል፡፡ እንዲያውም ትክ ያለው አስተያየታቸው፣ የቻይኖቹ አይኖች ጠባቦች ስለሆኑ ስለነሱ ሊያዩላቸው ነው የሚመስለው፡፡

እዚህና እዚያ እየረገጥኩኝ፥ መንገዱን አጋምሼ ስቃረብ… ድንጋይ ሰራተኞቹ ቻይኖች እንዳልሆኑ አየሁ። በዚህ ሁኔታው… ቁፋሮው እኛ በር ጋ ሲደርስ ታታሪዋ እናቴ ስራ ፈትታ ቆማ እንደማታያቸው እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል አስቤ ፈገግ አልኩኝ፡፡  ፈገግግግ! — እናቴ ወሬ ስትከልም ታይቶኝ… ኧረ ጨዋታ እንጂ እሷስ ወሬ ጠላቷ ነው።…ብቻ ግን ድንጋዩ ሸክሙን ለመመልከት ከብበው ከቆሙት ምስኪን እናቶች ሁኔታ ውስጥ እናቴን ተመለከትኳት። ቤት ስሄድ ደግሞ ምናልባት የእናቴ ሁኔታ ውስጥ እነሱን እመለከታቸው ይሆናል።

ከመንገዶቹ ግራና ቀኝ ያሉት ቤቶች አብዛኞቹ እድሳት ላይ ነው የሚመስሉት፡፡ በተለይ ፊትለፊታቸው ከሚሰራላቸው የኮብልስቶን ሀሳብ ጋር ሲነፃፀር መድከማቸው ይጎላል። …ልዩነቱ ሱፍ በላስቲክ ጫማ እንደማድረግ ነው የሚሆነው፡፡ አዳሽ ያስፈልገዋል፡፡ ነዋሪው ቤቱን እንዳያድስ የሚፈርስ ሰፈር ስለሆነ በሚል ሰበብ ቀበሌው የእድሳት ፈቃድ የማይሰጥበት ጊዜ እነደነበር ትዝይለኛል፡፡….ለዚህም ይሆናል ያዘመሙ አጥሮች ይበዛሉ፡፡

‘አጥሮቹ እንደጠ/ሚው ጥርስ ፍንጭት ይበዛቸዋል’ ልል አልኩና ‘ተውኩት እንደገና’…- ለካስ እኔም ጥርሰ ፍንጭት ነኝ፡፡ ሃሃሃ…. – “ለጥርሰ ፍንጭት ሰው ምስጢር አትንገረው” ይልሃል አማርኛው ደግሞ! — ሳያውቅ! ሂሂሂ…. የምር ግን አጥሮቹ የሳዝናሉ፡፡ የሚንሾካሾኩ ይመስል እንደሾካካ አንዱ ወዳንዱ ሹክክ ብለው ነው የቆሙት፡፡ በዚያ ላይ የስር ጠባቂ ድንጋዮቻቸው ተፈልቅቀው ተወስዶባቸው… — በለው! ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ’…– ልቤ አሁንም ያጋግላል፡፡

እንዲህ እንዲያ እያልኩ….
“ድናጋይ ለድንጋይ ዘለለች ጦጣ
እኔ አልለቅም ነፍሴ ብትወጣ…”

የሚለኝን የቡና አምሮቴን ላስታግስ ድንጋይ ለድንጋይ እየዘለልኩ ስተላለፍ….. ከፊትለፊቱ 60 ዓመት የሚገመቱ አዛውንት የቆሙበት በስርዓት ያልተቀመጠ ድንጋይ አይቼ እግሬን ጢብ አረግሁበት፡፡…. አዛውንቱን ለትንሽ ገፍቶ ሳታቸው፡፡ ጮሁ። ደነገጥኩኝ። ወዲያው ግን ምንም ስላልተጎዱ ደስ አለኝና ዝቅ ብዬ እግራቸውን እየዳበስኩ “ይቅር በሉኝ አባቴ!” አልኳቸው… አልሰሙኝም።… እሳቸው ይራገማሉ… ሰፈሩም ይራገማል… እንዳልሰማ ሆኜ ይቅርታዬን እያደጋገምክ ጎዘጎዝኩት። አልሰሙኝም ወይም አይፈልጉም ነበር። ብቻ በጣም አመረሩ…

እኔም ነገሩ ግራ ገብቶኝ “አባ እኔ እኮ አይደለሁም፣ ድንጋዩ አጉል ቆሞ ስለነበር ነው፡፡ ከተጎዱ ደግሞ ሀኪም ቤት እንሂድ፤ ግን ምንም አልሆኑምና ይቅርታዬን ተቀበሉ፡፡” …አልኳቸው፡፡ (በልባዊ ትህትና) አልሰሙኝ መሰል በቁጣው ቀጠሉ፡፡ እኔም በልቤ ተናደድኩ፡፡ ዝም ብዬ እንዳላልፍ ሰዉ ወሬ ቅርሚያ ከፊት ለፊቴ ተከምሯል፡፡ ግራ ገባኝ…

በቆምኩበት… ከጎረምሶቹ አንዱ፥ “ደግሞ ይናገራል እንዴ? መሰባበር ነበር…” ሲልና እርሱን ተከትለው እርግማኑን እንዳዲስ ሲቀባበሉት….ንዴቴን ከልቤ ወደ ምላሴ አመጣኋትና….

“እንደውም ምንም ይቅርታ አያስፈልገውም፡፡ እስካሁንም ይቅርታ ብዬ የለመንኩዎት በትህትና ነው፡፡….እንግዲህ እርሱን ካልወደዱ ደግ አደረግኩኝ!…. ድንጋይም በተፈጥሮው ሰባሪ ነው፣ እግርም ተሰባሪ ነው፡፡… እርስዎስ መጀመሪያ አይተው አይቆሙም፡፡ ተጎዳሁ ሲሉ አሳክሞታለሁ፡፡ ወንጀል ሰራ ሲሉ ይክሰሱኝ፡፡…ፓራራራ…. ታታታ…. ” ምናምን ምናምን አዘነብኩባቸው። እርግማኑ ቀጠለ… መንገዱም ተከፈተ….

ነገሩ በማበሳጨትና በማዝናናት መሀል ሰንጎኝ ስሄድ፣ የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የገጠመኝ ነገር ትዝ አለኝ….

እንድ ግድንግድዬ ወጠምሻ ከሁለት (ወይም ከሶስት) መሰል ጎረምሶች ጋር እየተንከባለለ ይመጣል፡፡ እኔም ወሬ እየቃረምኩ ክጓደኞቼ ጋር ግራ ቀኝ እያየሁ ነበርና የምሄደውና…ከየት መጣ ሳይባል (ከየት ሄድኩ ሳይባል) ሆዱ ላይ ተቀረቀርኩኝ፡፡ እሱም እሳት ለብስ እሳት ጎርሶ፣ (ሁኔታው ከነመልኩ ዛሬም ትዝ ይለኛል)… እኔንም እንደሚጎርሰኝ ሁሉ ጠቅልሎ ይዞኝ…

“እያየህ አትሄድም?” አለኝ፡፡

….ሰደበኝ። ሲሳደብ ስላላስቻለኝ (ከመሰደብ መመታት ይቀለኛል)

“እኔ ባላይ አንተ አታይም?” አልኩት እኩል ተቆጥቼ….

ጓደኞቹ ሳቁበት…አዝኖ እንደለቀቀኝ ሁላ “አሳዛኝ” ብሎ የምንተፍረቱን ትቶኝ ሄደ።
(አማርኛ አተረፈችኝ። እነሆ ከዚያም በኋላ እንደ ነፍሴ መውደድ አረጋት ጀመርኩ ብዬ ላካብድ? ሃሃሃ…)

የቆሎ (የልጆች) ገና

ዛሬ ዋዜማ ነው። — የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ዋዜማ። አንድ ጊዜ ተኝተን ስንነሳ ደግሞ ገና ይሆናል።… ዋዜማው እኛ ቤት (እኛ ሰፈር) “የቆሎ ገና” ወይም “የልጆች ገና” ተብሎ ይታወቃል። ቆሎ በየቤቱ ስለሚበላ ‘የቆሎ ገና’ …. ልጆች ካለከልካይ ስለሚጫወቱና ስለሚቦርቁ ደግሞ በተለዋጭ ‘የልጆች ገና’ ይባላል። እነሆ ቆሎው ቀራርቦ እየተበላ ነው። ሲሆን ጠላም ይቀርባል። እኔም ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እጆቼን በየመሀሉ የኮምፕዩተሩን ቁልፎች ከመጫን የማሳርፈው ጠረጴዛው ላይ ባለው የቆሎ ሳህን ነው። ….ገና ነዋ! የቆሎ ገና!

እንደልጅ የገና ጨዋታውን ተጫውቼ ዋዜማውን ‘የልጆች ገና’ በሚል ስያሜው ባላከብረው እንኳን ቤት የተዘጋጀውን (በእውቅ ተዘጋጅቶ የተገዛውን) ቆሎ እየቆረጠምኩኝ ‘የቆሎ ገና’ ብዬ አከብረዋለሁ። ሰፈር ያሉ (ባጋጣሚ በዋዜማው ገብቼ የማውቅባቸው) ቤቶችም ውስጥ በዋዜማው ሁሉም ተሰብስቦ ቆሎ ይበላል። በቆሎ ገናው ውጪ ስናመሽ ደግሞ የእኔ እናት ደስ አይላትም። ለምንም አይደለም…ቆሎውን እየቆረጠምን አብረናት እንድንጫወት ስለምትጓጓ እንጂ። እነሆ ቤት በጊዜ ሰፍረን ቆሎውን እንቆረጥመው ይዘናል…

እስከዛሬ ድረስ የቆሎ ገና ወይም የልጆች ገና በሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ውስጥ የዋዜማው መጠሪያ ስያሜ ይመስለኝ ነበር። ቅድም ከወዳጆቼ ጋር ስለዋዜማው አከባበር ስንጫወት ግን እንዲያ እንዳልሆነ አወቅሁኝ። ውጪ እንድናመሽና ፐርቸስቸስ ብለን እንድናሳልፍ ሲጋብዙኝ ‘አይ… እናቴ በገና ዋዜማ ውጭ ብዙ ስናመሽ ይደብራታል። ቤት ሄደን ቆሎ እንበትን እንጂ…በቆሎ ገናው ቤት ተሰብስቦ ቆሎ መቆርጠም ነው…’ ምናምን ስላቸው በግርታ ‘የምን ቆሎ?’ ብለው ጠየቁኝ። ስለእኛ ቤት ዋዜማ አጫወትኳቸው። እንዲያ ያለውን ባህል ከዚህ ቀደም እንደማያውቁ ተረዳሁ።

ከዚያም ቤት ስገባ እናቴን ስለባህሉ አመጣት ጠየኳት…. “መቼም ሌላ ቦታም የራሱ አከባበር ይኖረው ይሆናል… የቆሎ ወይም የልጆች በዓል የሚባለው ግን በጉራጌዎች ነው….” በማለት ጀምራ እንዲህ …

(ለአቀራረብ ያመቸኝ ዘንድ ቃል በቃል ከማድረግ ይልቅ አንዳንዱን ወደራሴ አፃፃፍ አምጥቼዋለሁ።)

“…ልጆች ገና ሲደርስ የገና ጨዋታ (ሩር) ይጫወታሉ። ከተማ ውስጥ ቢቀርም ገጠር ግን አሁንም አለ። በዓሉ ከመድረሱ በፊት ህፃናት በቃጫ ኳስ ጠፍረው በቆልማማ እንጨት እየጠለዙ ይጫወታሉ። ኳሱ “ቁር” ይባላል። እንጨቱ ደግሞ – “ድቤ”። ሩር ብቻ አይደለም፤ ፈረስ ጉግስም አለ ሌላም ብዙ ዓይነት ጨዋታ…– “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” ይባላል። እውነትም ማንም አይቆጣቸውም። — በተለይ በዋዜማው።….

ያሆ ያሆ…ለበሞ542224_590713924288943_733926906_n
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
ለበሞ ብንብና
ነባቼም በጉማ
ለበሞ ለበሞ
ድየ መሸም ይገቦ፣
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
የገና ያበቾ፣
ያምና የርጅ ወርዶ፣
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
በርጅ ኧርጆ
ሳምር ትፍጆ
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
የገና ግየቶ
አዠሁ በዝ ቤቶ
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
በገና ጨዋታ
አይቆጡም ጌታ
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ”

ይጫወታሉ። ይጨፍራሉ። … ጨዋታና ጭፈራው ለአንድ ቀን ብቻ ቢሆንም ደስታው ልዩ ነው። ጨዋታውን የሚያበቁት በዋናው በዋዜማው ምሽት ነው። ጨዋታውን ሲያበቁ ደግሞ በአካባቢው ካልወለዱ (መሀን) ሴቶች ካንዷ በራፍ  ላይ ጥለውት ለዓመቱ ልጅ ትወልድ ዘንድ ተመኝተው ነው። የጭፈራው ግጥምም በደፈናው ሲተረጎምም እንዲያ ነው የሚለው።

እንግዲህ በዚያ ቀን ያልወለደች ሴት እርሷ ደጅ ላይ ይጣልላት ዘንድ ጓጉታ ትጠብቃለች። “እኔ ደጅ ጣሉልኝ” ብላ አፍ አውጥታ የምትጠይቅም ትኖራለች። ያው የልጅ ጉጉቷ ነው የሚያስጠይቃት። እነርሱ ግን ቆመው ተመካክረው ነው ካንዷ ደጅ የሚጥሉት። የተጣለላትም ሴት እንደ አቅሟ ትሳላለች።…

…ከዚያ አምና ድቤውን ወደጣሉበት ቤት ይሄዳሉ። እዚያ ቆሎና ጠላ ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል። ስለት ከሰመረ ደግሞ በመነጋው የስለቱን ድግስ እዚያው ቤት ተገኝተው ይበላሉ።… እምነታቸው ይገርመኛል ብዙ ጊዜ ግን እንጨቱ የተጣለበት ቤት ሴት በዓመቱ ትወልዳለች። ከየቤታቸውም አምጥተውም ይጨምሩበትና ቆሎ ሲበሉ ሲበትኑ ያድራሉ። ገና ስለሆነ ቢበትኑም ግፍ የለውም። ማንም አይቆጣም።… ዛሬ ግን አይበተንም። ኑሮው አይሰጥም።

ከዚያ በዚያ ቤት ውስጥ ያድሩና ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ ተነስተው ወጥተው እሳት ያነዳሉ። እንጨት ካልተዘጋጀላቸው አጥር ገንጥለውም ቢሆን ማንደዳቸው አቀርም። እሳት አንድደው ሲጨፍሩ ይነጋል። በገና ጨዋታ አይቆጡም ቤታ  ስለሚባል ምንም ቢያደርጉ ማንም አይቆጣቸውም። ሲነጋ ቤት ቤታቸው ሄደው ገላቸውን ታጥበው ገንፎ ይበላሉ። ተመልሰው ደግሞ አምና የጣሉበት ቤት ይሰበሰባሉ። ብዙ ጊዜ ስለምትወልድ ደስታ ነው….

ዛሬ ዛሬ በልምድ ተላልፎ በዓሉ ተረሳ እንጂ ሁሉም ትርጉም አለው። ቆሎው እረኞቹ የጌታን መወለድ ሲሰሙ ይዘው ይጓዙ የነበረውን ስንቅ በማሰብ ነው። እሳቱም የሚነደው ብስራቱን የሰሙት በሌሊት ስለነበር ነቅተው በመጠበቅ እሳት ይዘው ወደ በረቱ መሄዳቸውን በማሰብ ነው። ስለቱም ከአምላክ መወለድ ጋር ላልወለደ መልካም ለመመኘት ነው።…”

መልካም የገና በዓል!!

(ማስታወሻ: ፎቶ ከወንድም ዘሪሁን ተስፋዬ ግድግዳ የተገኘ)

ሰካራም ቀለም

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፥ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል፥ በ2001 ዓ/ም ያዘጋቸው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሰከረ”ን በግስነት — ‘በአልኮል መጠጥ፣ በዕፅ…ምክንያት ስሜቱን የሚሰራውን መቆጣጠር አቃተው።’ ይልና፤… ከሰከረ ለቅፅልነት የረባውን “ሰካራም” —
1. አልኮል መጠጥ አዘውትሮ የሚጠጣ፥ ጠጪ።
2. አልኮል መጠጥ ጠጥቶ የሰከረ።’ ብሎ ይተረጉመዋል።

የእኛ ቤት (የእህቶቼ) መዝገበ ቃላት ደግሞ “ሰካራምን” ከስካር (ስ) ከረባ ቅፅልነትstock-photo-paint-splashing-blotches-of-different-colors-105645551 ባሻገር በቀለም ዓይነትነት ያስቀምጠዋል።… ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር። [ትንሽና ትልቅነታቸው እርስበርሳቸው ሲተያዩ ሆኖ]… ትንሿ እህቴ ትልቋ እህቴን….
“እሙዬ ክሩን አቀብይኝ” አለቻት።
ትልቋ ቀልጠፍ ብላ ቀዩን ክር ብድግ ስታረገው …
ትንሿ: “አይ…ሰካራሙን አለቻት”… ሌላ ቀይራም አቀበለቻት። ደብለቅለቅ ያለ ቀለም ያለውን ቱባ ክር አንስታ አቀበለቻት። መግባባታቸው ገረመኝ። ልቤ ‘ጉድ’ አለ! (ብለን እናካብድ? ሃሃሃ…)

እነሆ ከዚያ በኋላ “ሰካራምን” በቀለም ዓይነትነት አወቅሁኝ። ሰካራም ማለት ብዙ ዓይነት ቀለማት በአንድነት ሲሰፍሩ (ካለመደባለቅ) የሚኖር መልክ መሆኑን ተማርኩኝ። ስሙን ከማወቄ (ከመማሬ) በፊት ሰካራሙ ክር ተቀምጦ ሳየው፣ በአቀላለሙ መልክና በቀለም አቀያየጡ ስርዓት እገረምና …‘ወይ ጉድ! እንዴት አቀለሙት?’ ብዬ ለራሴ እጠይቅ ነበር።… ከርሱ በፊት በስንቱ ተገርሜ ስጠይቅ እንዳልኖርኩ፤…. ከርሱ በኋላ በስንቱ ተደምሜ እንደማልጠይቅ፤… ላሊበላና ይምርሀነ ክርስቶስን አይኔ አይቼ የአድናቆት ጥግ ላይ እስክደርስ ድረስ…. (ውይ እርሱንም መፃፍ አለ ለካ?! :-/)

ከዚያ በኋላ በልጅ አእምሮዬ ሰካራም ሳይ ደስ ይለኝ ነበር። fክሩንም የሰከረውንም። እንደ ስምም እንደ ቅፅልም። (እንደ ስም – ቀለሙን፤ እንደ ቅፅል – ጠጥቶ ራሱን የሳተውን)። ከማንም በተሻለ ሰካራምን እንደተረዳሁ ይሰማኝና በልቤ እሸልል ነበር። የሰዉን ግድግዳ እየደበደበ (ሲያጠብቅ፣ ሲያላላ)፣ ያገኘውን እየጠለዘ፣ እየተሳደበ፣ እየተዘለፈ… ሲያልፍ፣ ህፃናቱ እየተከተሉትና ኮቱን እየጎተቱ : –

“ሰካራም ቤት አይሰራም፣
ቢሰራም ቶሎ አይገባም
ቢገባም ቶሎ አይተኛም
ቢተኛም ቶሎ አይነቃም…”

…ሲሉት እኔ በራሴ ሀሳብ እብሰለሰል ነበር። (ቃሉን በቀለምነት ካወቅሁ በኋላ ፀባዬ ተቀይሮ) ለእኩዮቼ ሰካራሙን ሰውዬ ከቀለሙ ጋር አነፃፅሬ እንዴት እንደማስረዳቸው አስብ ነበር። ሲሰክር ስለሚያየው የሚያምር ሰካራም ቀለም ዓይነት እንዴት እንደማስረዳቸው (ቢከራከሩኝ እንኳን ክሩን ከቤት አምጥቼ ማሳየት እንደምችል ሳይቀር እያሰብኩ) በልቤ አቀናብር ነበር። ቅንብሬን ሳልጨርስ ሰካራሙ ያልፍና ይረሳ ነበር። ሌላም ሰካራም ይመጣል… እርሱም እንደ አዲስ ሳቀናብር ያልፋል። ሌላም… ሌላም… ሌላ ቅንብርም… ሌላአአአ…

ሰካራም ቀለም እና ቅዳሜ

አሁን አሁን ግን ትንታኔውን ልብ አልለውም፡፡ እንዲያው imagesከሰካራም ቀለም አመሰራረትና ትንታኔ፣ እንዲሁም ከልጅነት ትዝታዬ ይልቅ የቀለሙ ዓይነት ተዋህዶኝ የቀለም ዓይነት ለመጥራት እጠቀመዋለሁ፡፡ የሚያምር ቀለም። ሁሉም ነገር ያለው። ሁሉም የሞላለት። ምንም ያልጎደለው። ቅዳሜ ለእኔ እንዲያ ነች። ቅዳሜ መጥቶ ምን ጠፍቶ? ሁሉ ነገር ሙሉ ነው…. ቀይ ቢሉ፣ አረንጓዴ ቢሉ፣ ሀምራዊ ቢሉ፣ ሰማያዊ ቢሉ…. የቀለም ዓይነት። የመልክ ዓይነት። ድርድርድርድርድር….ጥቁርም ሳይቀር!…
ግን ጥቁሯን የምታሳየው ከስንት አንዴ ነው። ምናልባት በዓመት አንድ ጊዜ? – “እንደ ባቲ መንገድ?” ውሸት ምን ይሰራል?… የባቲ መንገድ የመጣልኝ አሁን ነው። ልክ አሁን። የጂጂ ሙዚቃ ዞሮ ተዟዙሮ “ባቲ”ዋ ጋር ሲደርስ… ባቲን ስትጫወት… ባቲን ስታንቆረቁር…. ወይ ግጥምጥሞሽ! ብለን ተደመምንና እንደምንም ሰካናት! ሃሃሃ…

“♩ ♬ ኧረ ባቲ ባቲ፣ ባቲ ከተማው
ከሚበላ በቀር የሚጣል የለው፤
እንደ ባቲ መንገድ፣ እንደ ወዲያኛው፣
በዓመት አንድ ቀን ነው፣ የምትገኘው፤ ♪

♫ ጨረቃ ባትወጣ፣ ደምቃ ባትታይ፣
አንተ ትበቃለህ፣ ለአገሬ ሰማይ፣
አንተ ትበቃለህ፣ ለአገሬ ሰማይ። ♫”

ተኝተን ስንነሳ…

አዋሳ ገብርኤሏ ደርሷል። — ቅዱስ ገብርኤሏ! — መልአከ ገብርኤሏ! – ነገ ነው። በልጅነት አፍ 735219_299686156819091_45223971_n ደግሞ – ‘አንዴ ተኝተን ስንነሳ ገብርኤል ይሆናል።’ ቀጤማው፣ ዳቦው፣ ጠላው፣ ጠጁ….. – ፌሽታ!! — አንዴ ተኝተን ስንነሳ ሁሉም ይሆናል። (ልጅ እያለሁ ‘አንዴ ተኝተን ስንነሳ….’ ‘ሁለቴ ተኝተን ስንነሳ…. እንዲህ ይሆናል!….. እንዲህ ቀን ይመጣል።’ ምናምን ስንል ዛሬ ናፕ የምንለውን ዓይነት ቆራጣ እንቅልፍ ተኝቶ መነሳትና ቀኑን ጎትቶ ማምጣት ያምረኝ ነበር። የማልፈልገውን ቀን ለማራቅ ደግሞ (ለምሳሌ ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን) ብዙ በማምሸት (ባለመተኛት) ቀኑን መግፋት ያምረኝ ነበር። — አይ ልጅነት!)

ገብርኤሏ ሲደርስ ከተማው ብቻ ሳይሆን የሰዉ ስሜትም ድብልቅልቅ ይላል። የልቡ ሁኔታም ድብልቅልቅ ይላል። [በልባቸውም ቢሆን]…. አማኙ – ይሸልላል!…. ሌላ አማኙ – ይቀናል! ….. ፈታ ያለው ኢ-አማኒ በፌስቲቫሉ ይደመማል! – የልቡ ዳሌ በደቡብ ስልት ይደንሳል!… ወግ አጥባቂው ኢ-አማኒ ደግሞ ይበሳጫል! – የርሱን ማወቅ (በራሱ የተረጋገጠውን፣ ባነበባቸው መፅሀፍት የፀደቀውን ማወቅ) እየተነተነ ለህዝቡ አዛኝ ይመስላል (ወይም ያዝናል)!… – ያም ሆነ ይህ ዓመት በዓል ነው – የሽለላ! የቅናት! የድማሜ! የብስጭት ዓመት በዓል! – ሁሉንም እንኳን አደረሰው!!

እመት አዋሳም ከዓመት በዓሎቿ አንዱ ደርሶባት ወገቧን አስራ ሽር ጉድ ትላለች። ሰው ተቀብላ ታሳርፍና ሌላ መምጣት አለመምጣቱን ለማየት ከአንገቷ ቀለስ በማለት ዓይኖቿን በጥቁር ውሀ በኩል ወርወር ታደርጋለች። (ሻሸመኔ ባለውለታዋ ነች።… የወዲያኛዎቹን ከየአቅጣቻው አሰባስባ ታሳልጥላታለች። ታስተናብርላታለች። ታስተላልፍላታለች።) ደግሞ ታያለች… መለስ ብላ በቱላ፣ በቦርቻ በኩል ወደ ይርጋለም – ዲላ — ይርጋ ጨፌ — ሀገረ ማርያም —- ያቤሎ —– (ጲጲጲጲ…) ተምዘግዝጋም፣ እንዴትም አባቷ ብላ ቢሆን ሞያሌ ድረስ መብቷ ነው… – ልብ ካለች፥ ለገብርኤሏ የሚሸክፍ እንግዳ አታጣም።

አመት በዓሏ ሲደርስ እንዲህ ነች።… መለስ ቀለስ ነው ስራዋ። እንግዶቿን ትቀበላለች። — ዳኤ532674_3168644382957_136314712_n ቡሹ! – አኒ ኬራ!! መኪኖቹ ምዕመኑን ሞልተው ከተለያየ ቦታ እያመጡ መናህሪያዋ ላይ ያራግፉላታል። ቤተስኪያኑ በራፍም ያራግፉላታል። መኪኖቹ ደርሰው ማራገፊያቸው እንደቆሙ…. ቤንዚን ጠብ እንዳለበት እሳት ቦግ ያለ የመራገፍ ትርምስ ይታያል። — ምዕመናን ከመኪኖቹ ሲወጡ…. ቀን በሌዎች፣ ተራ አስከባሪዎች፣ ሌቦች (ያው ግርግር ለሌባ ያመች የለ?) ወደ መኪኖቹ ሲሮጡ እኩል ይሆናል። — እቃ ለመያዝ….. እቃ ለማስያዝ…. — ትርምስ!

ቦግ ያለው የሰው ትርምስ (እንደ እሳት ያለው) ወዲያው ክስም ይላል። (የሰው ቤንዚን ሲደፋበት መልሶ ቦግ እስኪል ድረስ) … ደርሰው ሲበተኑ። ምዕመናኑ ወደ ማረፊያቸው…. ቀን ሰራተኞቹ ወደ ጥጋጥጋቸው…. — ፀሀይዋን ሽሽት! ውይ ፀሀይ…. ለነገሩ ለማያውቃት ጥቁር እንግዳ እንጂ ለኗሪዎቿ ብርቅ አይደለችም። ስትጠፋ ነው ብርቅ። — ‘ኡኡቴ…. ማን ሊሞት ይሆን?’ ይባልላታል። ማን ሲሞት ፀሀይ ጠልቆ እንደሚያውቅ… — ራሳቸው ኡኡቴ!

እንግዲህ ነገ ነው ቀኑ። ከየቦታው የተሰበሰቡት ምዕመናን ነጠላቸውን አንጠላፍተው ከተማው282820_299685563485817_469295871_n አስፓልት ላይ ከቤተክርስቲያኑ ወደ ሀይቅ — ወደ እርሻ ጣቢያ መንገድ — ወደ ማውንቴይን —- ወደ ሰፈረ ሰላም (አቶቴ) (አላሙራ) —- ወደ ቅያሶቹ —- ወደ…. ይሰመራሉ። ልክ መንገዱ ላይ የተደፋ እርጎ ሊመስሉ (በታላቁ Adam Reta ልጅ፣ የግራጫ ቃጭሉ መዝገቡ አገላለፅ)። ከቤተስኪያኑ የተደፋ እርጎ ግን አይመስልም።… መሀል ላይ፣ ከቤተስኪያኑ ፊት ለፊት የቆመው የሀውልት ደንቃራ ያደናቅፈዋል….

ኤፍ ዋይ አይ!

ዮሐንስ ረቡዕ ረቡዕ ጫት አይቅምም።
— ሀሙስ ሀሙስም….
— አርብ አርብም….
— ቅዳሜ ቅዳሜም…
— እሁድ እሁድም…
— ሰኞ ሰኞም…
— ማክሰኞ ማክሰኞም…!!
ይህን ብለን ጨዋታችንን እንቀጥላለን. . .
* * *
ድሮ (ወግ ነው መቼስ ዮሐንስም ድሮ አለው!) ሲባል ይሰማ ነበር… አሁን ግን ተምታቶበት በደንብ አይለየውም። ወይም ያኔ ሲነግሩት በደንብ አልሰማቸውም ነበር። ወይ ደ’ሞ በደንብ አልነገሩትም. . . (ምናልባት ነጋሪዎቹ ቃሚ ከነበሩ፥ ለመቃም ሲጣደፉ፣. . . ሊፈርሹ ሲዋከቡ. . . ወይም ደግሞ አጣርተው ስለማያውቁት. . . ወሬውን አጥርተው አልነገሩትም። ወይ ደግሞ በምርቃና አዛብተውታል። ወይ ደግሞ. . . ) የራሳቸው ጉዳይ! ብቻ ግን እንዲህ ነበር ያሉት. . .
             ‘ያልቃመ ተጠቀመ፣
የቃመ ተለቀመ?!’
ወይም. . .
‘የቃመ ተጠቀመ፣
ያልቃመ ተለቀመ?!’
እነሆ ዮሐንስ አለመለቀሙን ግን እናውቃለን። ቢቅም ኖሮ ግን ማን ነው የሚለቅመው?… ማለቴ ማን ነበር የሚለቅመው? ዱካክ በወፍ አምሳል? (ስለ ዱካክማ መዓት ያውቃል።) የምሩን፥ ይህቺ ለቀማ ግን ፌክ ሳትሆን አትቀርም። ይልቅስ የሆነ ነገር ትዝ አለው. . .
* * *
መርካቶ . . . መሀል ከተማ. . . እዛ የማይሸጥ የለ መቼስ. . .! ከእለታት በአንዱ ቀን. . .

ከሚሸጡ እቃዎች፣ አልባሳት፣ ሸቀጦች፣. . . መሀል ጥቅሶች ነበሩ። የሚሸጡ ጥቅሶች። የድሀን ቤት ማስዋቢያ። ቀዳዳን ሸፍነው እግረ መንገዳቸውን የሚነበቡ። ከምሁር ተርታ የሚያስሰልፉ። በተስፋ የሚሞሉ። ከሀይማኖታዊ እስከ ፆታዊ. . . –ልክ እንደ facebook status update የሚመስሉ ጥቅሶች. . . ጥቅማቸው የሁለት እዮሽ ነው። የልብን ቀዳዳ ባይደፍኑም ማባበል። እንዲሁም የቤት ግድግዳ ቡድርስ መሸፈን። (ብርድ ለመከላከል? ለዐይን ለመሙላት?)

ከ “የሚረዳኝ የለምና ከእኔ አትራቅ” (መዝሙረ ዳዊት 22፥11) እስከ. . . “አድርገህልኛልና ለዘለዓለም አመሰግንሀለሁ።” (መዝሙረ ዳዊት 52:9) ከ “rose is rose, sky is blue,/….and I love you!” እስከ “ሮዝ አበባ ላይ ታምሜ ተኝቼ/….ምናምን ምናምን….” በቀለም (በማርከር) ያበዱ ጥቅሶች። እነሱን የሚያጅቡ ምስሎች ተለጥፎባቸው። ሁሉም ነገር በእጅ ነበር የሚሰራው….

አቤት የጥቅሱ ገበያ: ከመጠቀሚያ. . . እስከ መጠባበቂያ. . . ጥቅስ ድረስ የተሟላለት። ከችግር ቀን ስሞታ (አቤቱታ) እስከ ምቾት ቀን የእፎይታ ድምፅ። የችግሩ — በችግር ቀን፣ የሚበላ ሲጠፋ፣ ወዳጅ ፊት ሲነሳ፣ ጎረቤት ደጁን ሲዘጋ፣ ፀሀይ በቤቱ ስትጠልቅ ይለጠፋል። (ወይ ደግሞ እንዲያ የሆነ ሰው ይገዛዋል። እንዲያ ነኝ ብሎ ያመነ። ራሱን የመዘነ ሰው – ደሀ ሰው. . . ) በቦታዋ ጥቅሷ ቦግ ትላለች። — ችጋር ወለድ ፀሎት፣ ልመና፣ ተስፋ፣ እምነት. . . ከዚያ ሁሉ በላይ ደሞ የቤትን ቀዳዳ የመድፈን ተልዕኮ የሰነቀ!

የእፎይታ ድምፃም ጥቅሱ፥ በተድላ ቀን ይወጣና ይለጠፋል። በአንፃራዊ ተድላ። በአንፃራዊ ጥጋብ. . . በአንፃራዊ ምቾት. . .ፀሀይ በቤቱ ብቅ ስትል። ኩራዞች ላምባ ሲሞሉ። ምድጃው እንጨት ሲነድበት። (ምናምን ውስጡ ያለው ድስት ሊጣድበት) ድስት ሲታጠብ. . . (ወይም እንዲያ ሆነልኝ ብሎ ያሰበ ይገዛዋል።) — ምስጋና፣ እፎይታ፣ እርካታ. . . ከዚያ ሁሉ በላይ ደግሞ ማንቆላለጭ! ማናፋት! ማቅራራት! (ሰው እግር ጥሎት ቤት ዘው ሲል ጥቅሱ ዘው እንዲልበትና እንዲማረር።)

ገጣሚዎቻቸው የማይታወቁ ግጥሞች። ከ2 እስከ 4 መስመር የሚሆኑ ድርድር መስመሮች። ደሀው፣ ያልተማረው፣ ጎረምሳው. . . እንደሙላቱና እንደጉድለቱ የሚገዛቸው። ከገዙበት ስሜት ውጭ ሆነው (ትንሽ ሲሻሻሉ) ቢያነቧቸው በሳቅ ባያፈርሱ እንኳን በፈገግታ ሊያፈኩ የሚችሉ ጥቅሶች….ግጥሞች….– ከዚያ ባሻገር ግን ብርድ የሚከላከሉ። የቤት ቀዳዳን የሚደፍኑ። (የኑሮው ቢቀር)

ሻጩ (የነቃው ነጋዴ) ‘እልል በል ሀበሻ….’ እያለ ለተራበ ሀበሻ ይሸጣል። መንገደኛውን ለመማረክም ጮክ እያለ በተራ በተራ እያነሳ ያነባቸዋል። ሀበሻውም በልቡ ‘እልል’ እያለ ይከባል. . . ገበያውን! የጥቅሱን ጥብስ ገበያ!

አንደኛው እንዲህ ይነበባል. . .
“በጠፍጣፋ ድንጋይ ከተዘጋ በሩ፣
እናት አትገኝም፣ እንደ ወፍ ቢበሩ።”

ሞያዊ ትንታኔ አያሻውም። መልእክቱ ደርሷል። ድንጋይ…በር…ምናምን… ምንም እንደማይሰሩ፣ በሩ ተከፈተ ተዘጋ ምንም እንደማይረባው….. ገጣሚውም፣ ሻጩም ገዢውም ግጥም አርገው ያውቁታል። ግን ግድ የላቸውም። (ለነገሩ ማን ይመረምረውና ቀድሞ?) በቃ እናት ወርቅ ናት ነው መልእክቱ። ናት! ናት! ናት!

ብዙ ሰው ለሚያምነውና ለሚያውቀው ነገር ማረጋገጫ ደስ ይለዋል። ምናልባት ለዚያ ይሆናል ግብይቱ—ማረጋገጫ መፈለግና፣ ማረጋገጫ መስጠት። ይሄም ማረጋገጫ ነው።…. ግን ደግሞ ንግድ! በምስኪን ኗሪ ስስ ጎን የታለመ ትርፍ! –ከዚያ ሁሉ በላይ ለሰሪውስራ!! ‘ስራ ለሰሪው፣ እሾ ላጣሪው!’ ለተሰሪው ደግሞ የግድግዳን ሽንቁር መድፈኛ ወሽመጥ! ግድግዳን ማሳመሪያ ቀለም!

ሌላው እንዲህ ይቀጥላል. . .
“አንድ ፍየል ነበር እንደ እኔ የከፋው፣
የሆዴን ብነግረው፣ ያ’ፉን ቅጠል ተፋው።”

ፍየሉ ይቅም ነበር? ፍየሉ ይሰማል? እርሱ ሞኝ ነው ለፍየል የሆዱን የሚነግረው? ምናምን ምናምን….ብዙ መጠየቅ ይቻላል። ግን ማንም አይጠይቅም። ዋናው መልእክቱ ነው። — ‘በሆዴ ብዙ አለ….ፍቶኛል’ ነው መልእክቱ!

ይቀጥላል. . .
“ሁለት ውሾች አሉኝ የማሳድጋቸው፣
ሰምቶ መቻልና ችሎ ማለፍ ናቸው።”
እዚህም መልእክቱ ደርሷል። ስለችሎ ማለፍና ስለሰምቶ መቻል (ህብተረሰባዊ ምርጥ ባህርያት) ይሰብካሉ።. . . ሌላም ብዙ ብዙ. . .

ከእነርሱ መሀልም ስለጫት የሚያወራው እንዲህ ይላል. . .
“የዓለም ሳይንቲስቶች በእውቀት የመጠቁ፣
ሁሉም ይቅማሉ እየተደበቁ።”

ይህኔ ጉድ ፈላ። ሲያዩት (በልጅ ወይም ባልበሰለ አእምሮ) ብስለቱ ይማርካል (ወይም በሳል ይመስላል)። ፍልስፍናው ይጠልቅለትና አንድ ብሯን መዠረጥ አርጎ መግዛት ነው (ያው ለተገለጠለት)። ግን ከዚያስ? አሃ….መልእክቱስ? ‘ቃሙ ችግር የለውም?!’ ‘እንኳን እናንተና የዓለም ሳይንቲስቶችም ይቅማሉ?!….ጫት ጀት ያደርጋል?!’…. ምናምን ምናምን….

መቼስ የእኛ ሰው ለሚያደርገው እያንዳንዱ ነገር ደጋፊና አረጋጋጭ አካል ሲያገኝ ደስ ይለዋል። ድጋፉ በግጥም ተገልፆ በወረቀት ሲሰፍርማ በቃ! ዮሐንስ ጥቅሱን (ግጥሙን) or whatever ባየበት ቅፅበት መደቡ ላይ አንድ ኮፒ ብቻ ነበረ። ኪሱ ውስጥ ደግሞ አንድ ብር። አናፍቶ ገዛሁት። ተከራክሮ። (ክርክሩ ለደንቡ ነው….ለገዥና ሻጭ ደንብ….)

ያኔ ጥቅሱን የገዛው ማርኮት አልነበረም። የዋህ ቃሚ (ከሰው ተደብቆ እየቃመ ለማቆም የሚታገል) አግኝቶት ሀሳቡን እንዳይለውጥ አሰቦ እንጂ።….የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበር… ፓ! ጀትነቱ!…. ቅሞ ነበር እንዴ? ሆሆሆ…..የምር ግን እንዲህ ዓይነት ተቆርቋሪነት ያስቀናል። እነሆ ዛሬ በ6ኛ ክፍሉ ዮሐንስ ቀና…. (ይሄ ነገር ለራሱም አስቆታል) የምር ግን 6ኛ ክፍሉ ናፍቆታል….ትናንት 6ኛ ክፍል ሲደርሱ የተለውን የሚወደውን ጓደኛውን ከ16 ዓመታት በኋላ በድምፅ ሲያወራው ባሰበት….

ከጥቅሱ መደብ ጥቅሶች ይሄም ጥቅስ ትዝ አለው. . .
“ታምሜ ብተኛ፣ ቆሜ ባንቀላፋ፣
እንገናኛለን እኔ አልቆርጥም ተስፋ።”
***

አሁን ልቡ እየዘመረ ነው….በደማቋ ጨረቃ ውበት ልቡ ጠፍቷል…. ኧረ እንዲህም አድርጋው አታውቅ… ልጆቹ ሲዘምሩ በሀሳቡ ይሰማዋል። የርሱም ድምፅ ይሰማዋል….መዝሙራቸውን እየሰማ በየመሀሉ ይጠይቃል….

“ጨረቃ ድምቡል ቦቃ
አጤ ቤት ገባች አውቃ፣
/እሿ ደግሞ ሾካካ ነች። ንጉስ ቤት መግባት ትወዳለች። ማለቴ ንጉስ ልብ…:)/

አጤ ቤት ያሉ ሰዎች
ፈተጉ ፈታተጉ
/ገብሱን? አጃውን?/

በቁልፊት አስቀመጡ
/ለምን?….ከዚያስ?/

ቁልፊቷ ስትሰበር፣
/ውይ….ማን ሰብሯት ይሆን?/

በዋንጫ ገለበጡ፣
/ቢራውን?…አሃ! ሊጠጡ?/

አጃ ቆሎ፣ ስንዴ ቆሎ
/ውይ…. ስንዴ ቆሎ ይምጣብኝ። በሱፍ ያበደ ስንዴ ቆሎ። አቆላሉ…አበላሉ… ኧረ ማቅረቢያ እንቅቡስ ቢሆን?! መብላት ግን ደስ አይለኝም። ሲቆላ ሳይና ሰዎች ሲበሉ ሳይ ግን ሰው ይናፍቀኛል። በክረምት. . . ስንዴ ቆሎ. . . ከሰል ተቀጣጥሎ. . . ጋቢ ተለብሶ. . . ሲበላ. . . ሲቆረጠም. . . ሲሞቅ. . . ፓ!/

ያቺን ትተህ፣ ይህቺን ቶሎ!”
/ወይ ጉድ…የቷን ትቼ? የቷን ቶሎ?/

በላይ በላዩ ይጠይቃል። ልጅነቱ ናፍቆታል. . .
***

ቀጠለ. . .
በሀሳቡ መጡበት — ልጅነቱ. . . ጓደኞቹ. . . የሚቀናበት (ጠብቆም ላልቶም ቢነበብ ግድ የለውም) ዮሐንስ. . . ዘፋኙ. . .

“ኧረ ልጆች ልጆች እንጫወት በጣም፣
ከእንግዲህ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም።”
/ከ6ኛ ክፍል በታች የነበሩ ጓደኞቹ/

“…………………………………………………..
……………………………………………………
……………………………………………………
……………………………………………………”
/የሚቀናበት ዮሐንስ/

“ላይታረስ ጉም (?)፣ ኑግ እንደ ሱፍ ላይነጣ፣
ተመልሶ ናፈቀኝ፣ ተመልሶ ላይመጣ…”
/ዘፋኙ/

ወደ ጨረቃዋ ተመለሰ. . . አይፈረድበትም ኧረ! በጣም ታምራለች. . .
አሁን አይጠይቅም. . . ዝም ብሎ ይዘምራል. . .

“…ጨረቃ ድምቡል ቦቃ
አጤ ቤት ገባች አውቃ፣
አጤ ቤት ያሉ ሰዎች
ፈተጉ ፈታተጉ
በቁልፊት አስቀመጡ
ቁልፊቷ ስትሰበር፣
በዋንጫ ገለበጡ፣
አጃ ቆሎ፣ ስንዴ ቆሎ
ያቺን ትተህ፣ ይህቺን ቶሎ!…”