ጋሽ ተስፋዬ ለማ – ነፍስ ይማር!!

እኛም አለን ሙዚቃ፣
__ስሜት የሚያነቃ!
በገናችን — ♫ ♬♩ ♪ ♫ ♬
መሰንቆአችን — ♩ ♪ ♫ ♬ ♬
ክራራችን — ♩ ♪ ♫ ♬ ♫
ዋሽንታችን — ♩ ♫ ♬♩ ♫ ♬
እምቢልታችን — ♩ ♪ ♬♩ ♪ ♬…

የኢትዮጵያ ሬድዮ እንዲህ ሳይበላሽ በፊት፣ የባህል ሙዚቃዎች ምሽት መግቢያ የነበረው530849_322089074578799_1430219762_n ሙዚቃ የተስፋዬ ለማ ስራ ነበር። እንዲህ ብሎ ስለሙዚቃዎቻችን በሙዚቃ ያወራው ተስፋዬ፥ በተለይ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ በማስተዋወቅ ረገድ ከተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎችና ብሔሮች የተውጣጡ ከ30 በላይ አባላት በነበሩት “ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ” ዳይሬክተርነት (3ኛው ዳይሬክተር በመሆን) የተጫወተው ሚና ጉልህ ነበር።

በጎ ፈቃደኛ በመሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (በቀድሞ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርስቲ) እንግሊዘኛ ትምህርት ያስተምር የነበርውን ጀማሪ ሙዚቀኛ፥ አሜሪካዊው ቻርለስ ሳተንን ወደ ኦርኬስትራው በመደባለቅ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር አስተዋውቆት፤…. በኋላም ከቻርለስ ጋር በመተባበር የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃዎችን ይዞ “ብሉ ናይል ግሩፕ” በሚል ስም፥ ከ20 በላይ የአሜሪካ ከተሞች ዞሮ ያቀርብ ዘንድ ተስፋዬ የመሪነትና የአስተባባሪነት ስራ ሰርቷል።

በኋላም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ 2ሙሉ ስራዎችን አስቀርፆ አበርክቷል። (የአንደኛውን ባላውቅም አንደኛው በኢትዮፒክስ ቁጥር 23 ላይ ያለው መሆኑን ቀን ፋና ኤፍ ኤም የጣዕም ልኬት ላይ አድምጫለሁ።) ከዚህ በተጨማሪም ጋሽ ተስፋዬ ብዙ ሙዚቃዎችን ለብዙ ሙዚቀኞች ሰርቶ ሰጥቷል። ከብዙ በጥቂቱ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ነዋይ ደበበ፣ ፀሀዬ ዮሐንስ፣ ኤልያስ ተባባል፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ይጠቀሳሉ። (እንዲያውም ፀሀዬና ነዋይን ችሎታቸውን ተገንዝቦ በራስ ቴአትር የሙዚቃ ባንድ እንዲታቀፉና ዘርፉን በይፋ እንዲቀላቀሉ ብዙው ጥረት የርሱ እንደነበር የጣዕም ልኬት ፕሮግራም ላይ ተዘግቧል። በዚህ ባለሞያን ፈልጎ ከሙዚቃው ጋር በማገናኘት ግብሩም በሚያውቁት ዘንድ ዘወትር ይመሰገናል።)

ጋሽ ተስፋዬ፥ በተለይ በድራማዊ ሙዚቃ ስራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን፤ ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው ማህበራዊ ጉዳዮችንም በሙዚቃ በመስራት ረገድ ሚናው ትልቅ ነበር። እንደምሳሌ ለፀሀይ እንዳለ የሰራላትን “የህፃኑ ልጅ ለቅሶ” እና ለጥላሁን የሰራለትን “አንዳንድ ነገሮች”ና “አጉል ነው” ማንሳት ይቻላል፤ ከሙዚቃዊ ድራማዎቹ ደግሞ “ማሚቴና ከበደ” እና “ለቅዳሜ አጥቢያ” መጠቀስ ይችላሉ። ከዚህ ባሻገር ዛሬም ድረስ በተማሪዎች የምረቃ ባህል ላይ የምንጠቀምበትን የ“እንኳን ደስ አላችሁ” ህብረ-ዝማሬ ሰርቶ አበርክቷል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1980ዎቹ ተስፋዬ ወደ አሜሪካ በስደት ሄዶ፣ ቆይቶ73770_322089047912135_1438254975_n የኢትዮጵያን ሙዚቃ፣ ባህል፣ እና ጥበብ ከአሜሪካዎቹ ጋር ለማቆራኘት በማሰብ፥ የኢትዮ-አሜሪካን የባህል ማዕከል፣ የናይል ኢትዮጵያ ጥምረትና ተስፋ ሙዚየምን መስርቷል። በመካከል በገጠመው የጤና እክል ምክንያት እንቅስቃሴዎቹን እስኪገታ ድረስም ቀድሞ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ሳለ ከሚተዋወቁ ሰዎች መሀል አራቱ – ተስፋዬ፣ ቻርልስ ሳተን፣ ጌታመሳይ እና መላኩ ገላው – ድጋሚ አሜሪካ ላይ ተገናኝተው በጋሽ ተስፋዬ ዳይሬክተርነት “ዞሮ ገጠም” (reunion) የሚል መጠሪያ ያለው የኢትዮጵያ የባህላዊ ሙዚቃዎች ስብስብ አልበም አስቀረፁ። አልበሙን “ዞሮ ገጠም” (reunion) በማለት የሰየሙትም፥ ዞረው መገናኘታቸውን ለመዘከር የነበረ ሲሆን፣ ከአልበሙ የተገኘው ገቢ በሙሉም ለ Institute of Ethiopian Studies (ለኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም) እንቅስቃሴዎች መርጃ አበርክተዋል።

ጋሽ ተስፋዬ ለማ በ2000 ዓ/ም Ethiopian Yellow Pages የተባለ ድርጅት ያዘጋጀውን ኢትዮጵያ ሚሊንየም የክብር ሽልማት ተሸላሚ እንደነበረም ይታወቃል። ከዚህ አስተዋፅኦው ባሻገር ጋሽ ተስፋዬ በኤትኖሙሲኮሎጂስትነት ደረጃ፥ የሙዚቃንና የዳንስን ህብረተሰባዊና ባህላዊ ባህርዮቻቸውን ሲያጠና ነበር። ኋላም ላይ ከቅርብ ወዳጁ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የሚያጠነጥን መፅሀፍ ፅፎ አበርክቷል። በነበረበት የጤና ቀውስ ምክንያት ለረዥም ጊዜ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በትናንትናው እለት (ጥር 24/2005 ዓ/ም) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የሚችልና ስለ ጋሽ ተስፋዬ ለማ አስተዋፅኦዎች በሰፊው ለማወቅ ያደረበት ቢኖር ከዚህ በፊት ከመዓዛ ብሩ ጋር በስልክ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ነገ ምሽት ጨዋታ ፕሮግራም ላይ (ሲደገም) አልያም ከሸገር ኤፍ.ኤም. ማህደር ውስጥ አውርዶ ያዳምጥ ዘንድ እጋብዛለሁ።

ከተስፋዬ ግጥምና ዜማ ስራዎች ውስጥ የኤልያስ ተባባል “ማማዬ” እነሆ ተቀንጭቦ…

ኦሆሆሆሆ….
ከረጅም ማማ ላይ ጥንቅሽ የበላ ሰው፣
ከጎድጓዳ ስፍራ፣ ጠይም የሳመ ሰው፣
እንኳን ሽማግሌ፣ ዳኛም አይመልሰው፣ (2x)
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ ከእንግዲህ ታከተኝ፣
የሆዷን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ?!

ማማዬ ማማዬ፣ ኧረ ነይ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ሸጋ ልጅ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ቆንጆ ልጅ ማማዬ፣

ዐይነ ኩሎ (?)፣ ሽንጠ ሎጋ የወለዱ እንደሆን፣
መልካም ፀባይ ያላት የወለዱ እንደሆን፣
እውቀት የምትሻ፣ የወለዱ እንደሆን፣
ታመጣለች አማች ብረት መዝጊያ ‘ሚሆን።

ማማዬ ማማዬ፣ ኧረ ነይ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ሸጋ ልጅ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ቆንጆ ልጅ ማማዬ

ነፍስ ይማር!!

እንዲህ ባሉ ቀናት 1…

ዛሬ አብረን ተጫወትን ነው የሚባለው፤ ቁጭ ብድግ ስንል… – ከኋላችን ያሉት ሲጮሁብን! — እኛም ከፊት ለፊትያሉት ላይ ጮኧን አፀፋችንን ስንመልስ፤ በሙከራዎች ሁሉ ስንተቃቀፍ፤ ስንጮህ፣ ስንጨርፍ… – መቼስ ከሞላ ጎደል ሁሉም ጋር እንዲሁ ነበር?!… ደግሞ ስታዲየሙ ውስጥ ያለው ሀበሻ ሲታይ አንዠት ሲበላ?! ለነገሩ እኛንስ በጭለማው ማን ለይቶ አይቶን እንጂ፥ ቀላል እናባባ ነበር?!

ብቻ ሁላችንም በየፊናችንና በየቋንቋችን….
“ያ አላህ ያ ረቢ፣
አትበለን እምቢ!”

(ሀሳቡን) እያልን በሆያ ሆዬ ስንኝ ቋጠሮ ስንማፀን…. ‘ማርያም… ማርያም…’ እያልን ስንቋጥር! ‘የማርያም ልጅ ሆይ እባክህን….’ እያልን ስንጣራ! ….ደግሞ ሁሉም ዝም ጭጭ ያሉን መስሎን ስንተክዝ!….. ብቻ ከየትም መጣ ከየት፣ ማንም ፈጨው ማንም በዚያች ቀውጢ ሰዓት ዱቄቱ ነበር የሚፈለገው። – ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምቺው!”ም አይደል ተረታችን?!

ክብሩ ይስፋ! ቆይቶ ዱቄቱም ከተፍ አለልን። ደስም አለን። አያልቅ የለ 90 ደቂቃው አልቆም ይበልጥ ደስ አለን። ተመስገንም አልን!! እንደ እምቦሳ ቦረቅን። ፈነጠዝን። ዘለልን። እልልልልል…. ተመስገን!!

መሀል ላይማ ብንጣራ፣ ብንጮህ…. ጠብ የሚል ብናጣ ጊዜ…. ለጆሮ ጠብ የሚል ነገር ፍለጋ በሀሳባችን አስርት ዓመታትን ወደኋላ ተጉዘን ስነቃል ይዘን መጥተን ነበረ…

“ቀና ብዬ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
አላህንም ሰፈራ ወሰዱት መሰለኝ።”

….ይሉትን ስነቃል። የጨነቀው ያለውን። – ያልኖርንባቸውን፣ ያነበብናቸውን፣ የሰማናቸውን አስርት ዓመታት ተጉዘን…. – ምን ተስንኖን?!…. የጨነቀው እንዲሁ ነው። ከእግዜር ጋር ጠብ ደንቡ ነው። እርጉዝ ያገባል።

ግና ከምኔው ተገላብጦ፣ ከእረፍት መልስ ነገሩ ሁሉ ፉርሽ ሲሆንብን፣ ቡርቅርቅ ብለን…. ሌላ ስነቃል ፈልገን መዘዝን (ይህችን ስነቃል እንኳን መጀመሪያ ከወዳጃችን ነበር የሰማናት)

“ወረዳ ፈረመ፣
ቀበሌ ፈረመ፣
አላህ ካልፈረመ፣
ነገሩ ከረመ።”

በቀይ ወጣ፣ በአረንጓዴ ገባ፣ በቢጫ ተጠነቀቀ…. ትርጉም አጥተው ነገሩ ሁሉ በድል ሆነልን። አረንጓዴ ቢጫ ቀይም አሸበረቀች!! በግሌ ከማሸነፍም በላይ ብዬዋለሁ። አይደለም እንዴ? የምር እንዲህ ያለ የጨዋታ አቅም አለ ብዬ የት ጠርጥሬ? የት ጠብቄ? ቀላል አይደሉምሳ አያ?! እሰይ…. እንኳን ያልሆኑ። እንኳን የከበዱ። እንኳን ያከበዱን። እንኳን ያሰከሩን። እንኳን የሆነልን። አሃ! ፐርቸስቸስ ብለን አመሸናታ….- ‘እንኳንስ ዘንቦብሽ፣ እንዲሁም ጤዛ ነሽ’ ይሉም የል?!

* እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት ፖሊሶች ያሳዝኑኛል።…. ፌደራል ፖሊሶች። የሚገኝ ሳይኖር ልባቸውን መሬት ከህዝቡ ጋር ጥለው፥ በመኪና አርፋ ይዘው (ተንጠላጥለው) ከተማዋን እንዳበደ ዶሮ ይዞሯታል። በእግራቸው ዱላቸውን በወግ እያርመሰመሱ ይኳትናሉ። …መቼስ መጨፈር አይፈልጉም አይባልም። ቀላል ይፈልጋሉ? አየናቸው እኮ…. ባለፈው ማለፋችንን ያወቅን ጊዜ ዱላቸውን ትተው በስታዲዮም ዙሪያ ከእኛው ጋር ሲያረግዱም አልነበር?!
ብቻ እንኳን ደስ አላቸው!!

* * እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት የኤርታ ጋዘጤኞች ያሳዝኑኛል። በተለይ የቲቪው። ውይ… ዝም ብለው እኮ ነው የሚቀባጥሩት። እኩዮቻቸው ሲቦርቁ እነሱ የእነሱን ቡረቃ ፖሊቲሣይዝ ያደርጉታል። ያድርጉታ! – ቀረባቸው። ግን እንዲያው እንዲያ ሲባክኑና ሲካለቡ ሳይ አንዠቴን ይበሉታል። የሆድን ስፋትም ቁልጭ አድርገው ያሳዩኛል። ቀላል ሰፊ ነው አያ?!

ግን ምናለ እንዲህ ባሉ ቀናት ጣቢያውም ስራ ቢያቆም? ለእርሱም ክብር ነው። …መቼም ‘በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ!’ ነውና ነገሩ ብዙ ባወሩ ቁጥር ብዙ ይገመታሉ። እነሱ ደግሞ እንዲህ ባሉ ቀናት ብዙ ያወሩ ዘንድ ግድ ነው። ሆድ ነዋ… እንጀራ…. – ድንቄም እቴ!
ብቻ እንኳን ደስ አላቸው!!

* * * እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት ህዝቡ አንዠት ይበላል። በቋፍ እንዳለ ሁሉ ትንሽ ነው የሚበቃው። ከ__ እስከ__ ሳይል ወጥቶ፣ ከ__ እስከ__ ሳይል ቅርጥፍጥፍ አርጎ ነው የሚበላው። የምር… እምባ አማጭነቱ ያይልበታል። በቃ ሊለያዩት ያሰቡትን ሁሉ አንድ ሆኖ ያበሳጫቸዋል። አቅሉን ስቶ ይቦርቃል። ማንም ማንንም አቅፎ ይስማል። ጎዳናው ላይ ተጥለቅልቆ ጎርፍ ይሰራል።

— የሰው ጎርፍ! የነፃነት ጎርፍ! የፍቅር ጎርፍ! የጉጉት ጎርፍ! የናፍቆት ጎርፍ! የምኞት ጎርፍ! የትልቅነት ተስፋ ጎርፍ! የአገር ስስት ጎርፍ! አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ጎርፍ… ልጅ አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ ሙስሊም ክርስቲያን፣…ምንም ሳይመራረጥ ሰውነትና ኢትዮጵያዊነት በቅተውት እርስበርሱ ይንቆላለጫል።
ኧረ እሰይ ሆነለት። እንኳን ደስ አለው!!

* * * * እንዲህ ባሉ ቀናት….
እንዲህ ባሉ ቀናት ግራ ገብቶኝ እንከላወሳለሁ። የምይዝ የምጨብጠው ነው የሚጠፋኝ። ውይ….ግራ ሲሉኝ – ቀኝ! ቀኝ ሲሉኝ – ግራ!… በቅጡ አልሰማም። በቅጡም አላወራም። እንዲህ ደስ ሲለኝ ከጣሪያ በላይ እጮሃለሁ። ወይ ደግሞ ከመሬት በታች ዝም እላለሁ። ኧም ጭጭ!… ኧረ ምኔም አይታወቅ። ሆኖም ግን አገላለፄ ይለያይ እንጂ ደስታ የእኔው ነች። የሰዉን ሁኔታ ሳይ ደግሞ እንባዬ ቅርርር ይላል። ችሎ ባይወርድም ቅርር ይላል… እንደ ስስ… እንደ ሆደ ቡቡ…. – ነኝ እንዴ? የራሴ ጉዳይ! ዛሬ ግን ችሎ ፈሰሰ… – ግን መነፅራም መሆኔ በጀኝ አያ!
ኧረ እንኳን የሆነልኝ። እንኳን ደስ ያለኝ!!

* * * * * እንዲህ ባሉ ቀናት. . .
እንዲህ ባሉ ቀናት የፌስቡክ ወዳጆችን ማየት ደስ ይላል። (ያው በወል ከህዝቡ ቢደመሩም)… በፅሁፍ ሲታዩ ደስ ይላል። ሲነበቡ ያምራል። ዜማው ሁሉ አንድ ነው። ወሬው ሁሉ ተቀራራቢ ነው። ጉዳዩ ሁሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ላይ ያጠነጥናል። ከዚህ ቀደም በሀሳብ ከእኛ አይገጥሙም የምንላቸው እንኳን እንዲህ ባሉ ቀናት ልክክ ነው የሚሉት። የእኛኑ ሙዚቃ ይሞዝቃሉ። እኛም የእነርሱን ሙዚቃ እንሞዝቃለን። – ሲገርም! ለምን? ምናምን… ብለን በማጣራት አንደክምም። አንድም አይደለን?!
ኧረ እንኳን ሆነልን። እንኳን ደስ አለን!!

* * * * * * እንዲህ ባሉቀናት. . .
እንዲህ ባሉ ቀናት እናቴን ማየት ደስ ይለኛል። እርሷን ዝም ብሎ ማዳመጥ። የሆነ የሆነ ነገር እያወሩ ብዙ ማስወራት። ውይ! ስታውቅበት!…. እናቴ አልተማረችም። ‘ዐይኔ አይሰጠኝም’ ብላ ሞክራ ትተወዋለች እንጂ በስሱ ማንበብ ትችላለች። (ለምሳሌ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ታነሳና “አዲስ ነገር” የሚለውን ካነበበች በቃ!! …ስትፅፍ ከስሟ አትዘልም። ‘ዐይኔ የት ያያል?’ ትላለች። …ግን እርሱንም ‘እድሜ ለመንግስቱ ኃ/ማርያም እያለች ነው።’ በመንግስቱ ጊዜ መሰረተ ትምህርት ተምራ ነበር። ደግሞ ጎበዝ ሆና ትሸለም ነበር።

ያም ሆነ ይህ ግን ‘ተማርን’ የሚሉ ጎረቤቶቻችንን አለቅልቃ ትበልጣቸዋለች። (ወይም ለእኔ እንዲያ ይታየኛል።) እናቴ ስለሆነች አይደለም። በሀቅ ነው የምናገረው። የእኔ ሁለት ዲግሪዎችንም ችላ አፈር የምታበላቸው እናቴ ብቻ ነች። በፊቷ ያሸነፍኳት ልምሰል እንጂ ከእርሷ ጋር ማውራት ስጀምር ልቤ በቂጡ ቂብ ይላል። አይችልበትም።

እንደ እኔ መፅሀፍ አታጥቅስም። (ምናልባት ምዕራፍ ቁጥሩን ትታ መፅሀፍ ቅዱስን?!…እርሱንም ቢሆን የእምነት አባቶቿ ካስተማሯት አስታውሳ።) መጣጥፍ አታውቅም። ጋዜጣ የለ! መፅሄት የለ!…. ግን ‘መቼስ ካንተ አላውቅም… አልተማርኩም’ እያለች ልክ ልኬን ትነግረኛለች። ደስ ይለኛል። ከዚያ በላይ ደግሞ ስለምታሳምነኝና በአመክንዮ ስለምታምን በጣም ደስ ይለኛል። ስታምንም አታስቸግርም። ራሷን ከጊዜውና ከዘመኑ ጋር ማስተካከል ማንም አይችላትም። የማታውቀው ነገር ዛሬ ቢነገራት፣ ከዛሬ በኋላ ትተገብረዋለች… – ብቻ ትመንበት!

ገፍታ አለመማሯ ቢቆጫትም አትጠላውም። እንዲያውም ታመሰግንበታለች።…. በዚህ ረገድ ከ10 ዓመት በፊት ያለችኝን አልረሳውም። ሳጥኗን ከፍታ መሰረተ ት/ት ስትማር የተሸለመችውን የምስክር ወረቀት አውጥታ አየችውና በቁጭት “አዪ… ባላቋርጠው ይሄኔኮ እጨርስ ነበር።” አለችኝ።…. ወዲያው ደግሞ “ለነገሩ እንኳን አልተማርኩ። ደግሞ ልጅ አታብዙ የሚል ትምህርት ተምሬ አልወልዳችሁም ነበር ይሆናል።” ብላ አጣጥፋው ወደቦታው ወረወረችው።

እኛ ነን ማመስገኛዎቿ። እኛ ኮምፑተር ወይም መፅሀፍ ገልጠን ጓደኞቿ ቡና ሊጠጡ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ እንዲያረጉ ቀስ ብላ ተጠቁማቸዋለች።… ‘የእኔን ስራ ነው የሚሰሩት…መጦሪያዬን…’ ትላቸዋለ። [ሲጀመር እኛ ቤት ካለን ጠይቃን ነው ቡናም የምታፈላው] … (ከመስመር ወጥቼ ቀባጠርኩ አይደል?)

ብቻ እንዲህ ባሉ ቀናት እርሷን ማየት ደስታን ይጨምራል። ዛሬ ግን ቤት አይደለሁምና አላየኋትም። ሆኖም ግን መገመት አይቸግረኝም። እንዲህ ያሉ ጨዋታዎችን ስናይ አብራን ትቀመጣለች። ሲጀመር ጀምሮ ተማፅኖዋ ብዙ ነው። “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን።” ብላ ጀምራ ብዙ እያለች ትቆያለች። ማን ከማን እየተጫወተ እንደሆነ ብትጠየቅ ግድ የላትም። “ኢትዮጵያ አለች አይደል?” ትላለች። መልሱ “አዎ” ከሆነላት ሌላው ትርፍ ነው። “ቢሆንም ባይሆንም አገር ነው መቼስ” ትላለች…

አንድ አስር ደቂቃ እንደታየ ደግሞ ጭንቀቱ አላስችል ቢላት ብድግ ብላ ወደ መኝታዋ ለመሄድ ትነሳለች። “እግዚአብሔር ይሁናቸው። ጭንቀቱ ገደለኝ….ልተኛ። ካገቡ ግን ቀስቅሱኝ…” ብላ…። ግን ችላ አተታኛም። – እርሷም እኛም እናውቃለን። ከመግባቷ ሙከራዎችን ምናምን አይተን ድምፅ ካሰማን አያስችላትም… ድምፅ ባናሰማም አያስችላትም። መጀመሪያ መኝታዋ ሆና የአንዳችንን ስም ትጣራለች። ማንም አልሰማ ሲላት ደግሞ ከነፒጃማዋ ከመኝታዋ ብቅ ትላለች። የመጀመሪያ ጥያቄዋ “አገቡ?” የሚል ነው…

ከዚያ ደግሞ ዐይን ዐይናችንን ታይና መምከር ማፅናናት ትጀምራለች። “አይዟችሁ አባኤ…. ለነርሱ ካለው አይቀርም። አትበሳጩ።” ምናምን ብላ በተራ በተራ እያየችን ትደጋግመዋለች። – ሰማናትም አልሰማናትም! ለርሷ ጭንቀቱ የሁለት እዮሽ ነው። — አንድም ስለ ኢትዮጵያ፣ ሌላም ስለልጆቿ።…. ‘የወለደ አልፀደቀ’ እንድትል ራሷ።
ብቻ እንዲህ ወጣ ገባ ስትል እንቅልፏንም በቅጡ ሳታንቀላፋ ከእኛ ጋር ታመሻለች። ጨዋታው ሲያልቅ ደግሞ የእኛን ጨዋታ እንቀጥላለን። ዛሬ ግን ናፍቃኛለች። ክፉኛ!! ልደውልላትም ብሞክር ኔትዎርክ እምቢ አለኝ። ደስታዋ ግን አይጠረጠርም….
ኧረ እንኳን ሆነላት! እንኳን ደስ አላት የእኔ እናት!!

* * ኳሱ ፍቅሯ….
ታይቶኝ ከባህር ስትጠልቂ፣ ከምድር ከሰማይ ስትርቂ፣
ታይቶኝ ከነፋስ ስትረቅቂ፣ ከፀሀይ ጨረቃ ስትደምቂ፣
ሲጠጣ እንዳደረ ሰው ሲጨልጥ ውስኪ አረቂ. . .
ጢንቢራዬን የሚዞረው፣ ሰውነቴ የሚርደው፣
ኧረ በምን ነው ዓለሜ? በምን ያል የቀን ለከፋ፣
ስምሽ ሲነሳ ‘ሚያልበኝ፣ ነገር ዓለሜ ሚጠፋ?
በዐይኔ ዞሮ የሚያስቀኝ. . .

ንቅሳትሽ፣ ድምድማትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ኩል፣ ቀለምሽ፣ ውቅራትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ብር አምባርሽ፣ ድሪና አልቦሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ጥበብ ቀሚስ፣ ውስጥ ልብስሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
የአንገት ልብስሽ፣ መቀነትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ነጠላ ጋቢ፣ ኩታ ጃኖሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
በዐይኔ ዞሮ የሚያስቀኝ. . .

ነበር ያልነው ጠዋት? አሁን ሌላ አንጨምርም። ይህንኑ እየደገምንና “አለ ገና” እያልን እንስቃለን…
እንኳን ሆነልን!! እንኳን ደስ አለን!!!

ዐይኔ ዓለም አየ! (በትውስታ…)

ላሊበላ ሁለት ጊዜ ሄጃለሁ። መጀመሪያ የሄድኩት በ2001 ዓ/ም ነበር። ቀጥሎ ደግሞ በ20032011 Lalibela Felsen-Kreuzkirche ዓ/ም…. በ2004ም ላሊበላና ዙሪያው በዐይኔ ሲዞሩ ነበር፤ ሆኖም ግን ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነውብኝ ሳንተያይ ተሸዋወድን። ይህ ዓመት ከማለቁ በፊት ብሄድም ደስ ይለኛል። በሚቀጥለው ዓመትም። ከዚያም… ከዚያም…. ኧረ ከዚያም…. ከኧኧኧኧ…ዚያም! ኧረ ከዚዚዚዚ….ያም!

እንደውም የላሊበላ ነገር ውል ሲለኝ እንደማልችልበት ልቤ የሚያውቀውን – “እዚያም በገደምኩ” ያሰኘኛል፤…ግን እርሱ ለተጠሩት ነው። ለእኔ ግን ደርሶ መመልከቱም እንደ መጠራት ሆኖልኝ አንዴ ያየሁት ዓለም ስሙ በተነሳ ቁጥር ያስፈነጥዘኛል። ከዚህ ቀደም ላሊበላን አይቶት የሚያውቅ ቢኖር ነገሬ ከጫፍ ጫፍ ይገባዋል። ከጫፍ ጫፍ

DSC01443ባይገባው እንኳን ጫፍ ጫፉን አያጣውም።

አይቶት የማያውቅ ደግሞ ‘አቦ ምን ያካብዳል?’ ዓይነት ስሜት ውስጥ ቢገባ አይፈረድበትም። – አላየማ! ….ደርሼ እጄን አፌ ላይ ጭኜ፣ ‘ኦ ማይ ጋድ!  ኦ ኦ ኦ… ኦ ማይ ጋድ!’ ብዬ እንደ ድንጋይ ክልትው ብዬ እስክቀር ድረስ፥ እኔም እንደዚያ ነበር የምለው። – ‘አቦ ምን ያካብዳሉ?!’… አሁን ግን አይቻለሁና፥ እላለሁ…. እመክራለሁ…. እዘክራለሁ….

ሀይማኖቱ — ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ጴንጤ፣ ሙስሊም፣ dsc01433ጣኦት አምላኪ፣ ጠንቋይ ቀላቢ፣ ኢ-አማኒ፣ ግራ-ገብ…. ሌላም የፈለገውን ሆኖ፣ መረዳቱ የፈቀደለትን እምነት የሚከተል ማንም (በተለይ ኢትዮጵያዊ) በህይወት እያለ፣… በላሊበላ ለመደነቅና ቦታው ደርሶ አይቶ ‘በዐይኔ ዓለም አየሁ’ ለማለት፥ ማህበረሰባዊ ጤና ያለው (socially healthy) ቢሆን በቂ ነው። ምናልባት ጤነኛነቱ ላይ የአገር ፍቅር ስሜት ቢጨምርበትና ባንድራው ትዝ ቢለው ደግሞ ደስታው እጥፍ ድርብ ይሆንለታል፡፡ — እንደ እኔ ነው!

የመጨረሻውን ትንፋሽ ከመተንፈሱ በፊት… ዓለምን DSC01372ከመሰናበቱና ወደ መጨረሻ ቦታው የመሄጃ ትኬቱን ከመቁረጡ በፊት…. ልቡ እንደምንም ቆርጦ፣…‘አልበላም አልጠጣም’ ብሎ ሳንቲም ቀርቅሮ፥ (ኧረ ሰርቆም ቢሆን) …ትኬት ቆርጦ በእድሜው ላሊበላን ቢያየው አይቆጭም። ስንት ነገር ለሚሆንላት፣ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ስለርሷ ነፍሱን ለሚበድልላት ስጋውም ትልቅ ውለታ ነው። ከዚያ ወዲያ ምናልባት ላሊበላን በተመለከተ ሊቆጨው የሚችል ነገር ቢኖር ‘ወይኔ ላሊበላን ድጋሚ ሳላየው ሞትኩ’ ምናምን የሚል ቢሆን ነው። — ይሄም እንደ እኔ ነው!

DSC02900

ከዚያ በፊት ስለላሊበላ በእውቅ እና በጥበብ የተቀናበረ የቪዲኦ ምስል ተመልክቶ፣ በአንደበተ ርቱዕና አፍ አስከፋች ተራኪ ተተርኮለት፣ ወይም ሌላ… ብቻ እንዴትም ተደርጎ ስለላሊበላ አስደናቂነት ተነግሮት ቢሆን፥ ልክ እዚያ ሲደርስ ነገሩ ሌላ ሆኖ ነው የሚጠብቀው። ቪዲኦውን – ይጠረጥረዋል! ፎቶውንም! መጀመሪያ የነገሩትን የተረኩለትንም ይታዘባቸዋል! – ብዙ አጉድለውበታላ። እየቆየ ሲሄድ ግን አይፈርድባቸውም። እርሱም የተመለከተውን ለማውራት እንዴት ጀምሮ እንዴት እንደሚጨርስ ግራ ሲገባው ይረዳቸዋል።

ፎቶ ሊያሳይ ያወጣና ፎቶው ከሚያስታውሰው ጋር ሲነፃፀር 2011 Lllibela Felsengangይደበዝዝበታል፡፡ ሰውየው ነገር መጠፈር የሚቀናው ከሆነ ደግሞ…. “የፎቶ፣ የቪዲኦ እና የትረካ፥ ከንቱነትና ስንፍና ሊታዩ  ከሚችልባቸው ቦታዎች አንዱ ላሊበላ ነው” ብሎ ቢደመድም አይፈረድበትም። “ይናገራል ፎቶ” ብለን ዞር ከማለታችን ለላሊበላ ሲሆን ፎቶ እንደማይናገር እንታዘባለን። ከዚያም እናሻሽለዋለን – “ፎቶ አንዳንዴ አይናገርም! ቪዲኦም!”

መጀመሪያ ስሄድ የ16 ቀን ጉዞ ነበር። መንገድ ላይ ያሉትን የጎብኚ መዳረሻ ቦታዎች አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ እየበረበርን ነበር ያለፍነው። ጉብኝቱን ስናቅድ ላሊበላ መካተቱ ጉዞውን ሀይማኖታዊ ያደርገዋልና ይቅር ብለው አጥብቀው የተሟገቱ አንድ፣ሁለት፣ ሶስት… ወዳጆች ነበሩ። (ሁለቱ ፕሮቴስታንት ነበሩ። አንደኛው ደግሞ ሙስሊም።) ከዚያ ግን በሰው ብልጫ እና በብዙ DSC01328ሙግትና ማስረዳት ተረቱና ላሊበላም ተካተተ። ከዚያ በፊት በምንደርስባቸውና በምናርፍባቸው በፊት ቦታውን ከመበርበር በፊት ማረፍ ነበር የሚቀድመው።  ላሊበላ ስንደርስ ግን እንዲህ አልነበረም….

ማረፊያ ክፍል ይዘን እቃችንን ካስቀመጥን በኋላ መጀመሪያ ይቅር ብለው ሲከራከሩ የነበሩት ሶስቱ ሲቀሩ ሁላችንም ተያይዘን ወጣን። (ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሶስቱም ያሳዝኑኛል) ሁላችንም በየፊናችን ስለ ላሊበላ ‘ቱቲ’ ሰምተን ነበርና ተጣድፈን ቦታውን በቅምሻ ለማየት ጓጓን። በቀጣዩ ቀን ለመጎብኘት የትኬትና የአስጎብኚ ከፍለን DSC01359ካመቻቸን በኋላ ወደ ቤ/ክኑ ተጣድፈን ገባን። የሌላውን በርግጠኝነት ባላውቅም እኔ ጭው አለብኝ። ፍዝዝ… ጭው…

ውሸት ምን ይሰራል? በወቅቱ የተመለከትኩትና የሄድኩት ሁሉ ህልም ህልም ይመስለኝ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ እስክሄድ ድረስም በዚያው የህልም ስሜት ውስጥ ነበርኩኝ። ህልም ይመስለኝና ደስታዬ ወሰኑን ሲያጣ “ህልም – እልም” ብዬ ለራሴ መሳቂያ አበጃለሁ፡፡ በፎቶና በቪዲኦ ከተመለከትኩት በላይ ትልቅ (ሰፊ) መሆኑ የመጀመሪያው የአግራሞት ምንጭ ሆኖልኝ ነበር። ከዚያ ሌላ ደግሞ ላሊበላ ሲባል፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በቅፅሩ ውስጥ እንዳሉ DSC02952በወሬ ብሰማም በቴሌቪዥን አዘውትሬ የማየው ቤተ ጊዮርጊስን ነበር። በሚገርም ሁኔታ ግን ሌሎች 10 አስደናቂ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ግቢው ውስጥ መኖራቸውን አወቅሁኝ።

ስለ አሰራሩማ ምኑ ተወርቶ ምኑ ይተዋል? እንዲያው ታምር ነው። ካለምንም መሸራረፍ በቅርፅ መፈልፈላቸው፣ የመስኮቶችና የማዕዘናት እኩልነት፣ የውሀ ልኮች ልኬት፣ የግድግዳው መስተካከልና ልሙጥነት፣ የበሮች አሰራር፣ ስዕላቱ፣ በቅርፅና በደንብ የተሰሩት መተላለፊያዎች…. ምኑም ቢዘረዘርና ቢብራራ ነጋሪውንም ተነጋሪውንም አያረካም። ብቻ ጉድ እንዳልኩኝ አይቼው፣ ጉድ እያልኩኝ ተመለስኩኝ። ዛሬም ሳስበው ሌላ ነገር አልልም፡፡ — ጉድ ነው የምለው። “ሰው ነው የሰራው” “መንፈስ ቅዱስ” ብለው ለሚሟገቱ ሰዎች መልስ ለማቀናበር ሳልደክም ለራሴ ግልጋሎት የሚሆን መልስ ስላገኘሁ ደግሞ ይበልጥ ደስ ይለኛል። DSC01446እንዲህ ነው….

በእኔ እምነት ሰው ይህን ሰራ ቢባል እንኳን ያስበውና ደፍሮ ይጀምረው ዘንድ ወይ እብድ (የአእምሮ ህሙም) መሆን አለበት፣ ወይ ደግሞ የተለየ መንፈስ ሊኖረው፣ ሊያመላክተው ይገባል። ሌላ ሌላውን ብተወው እንኳን የድንጋዩና የፈልፋዩ በአንድ ቦታ መከሰት እንዲያው ግጥምጥሞሽ ነው ማለት ይከብደኛል። በተለይ መፈልፈሉና መፈፀሙ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መውሰዱን ሳስተውል፤ ያም ሆነ ይህ ግን ከሚታየው ነገር ርቄ በማይታየው ነገር እየተብሰለሰልኩ የማንንም ዋጋ (credit) የማሳጣት ሀሳቡም፣ መብቱም፣ አቅሙምDSC01463 የለኝም። ማንም ሰራው ለምንም ሰራው… ላሊበላ ለዐይኖቼ ታምር ነው።

እንግዲህ ከ900 ዓመታት በፊት እኒያን የመሳሰሉ ህንፃዎች ተፈልፍለው ባለበት ሁኔታ በአካባቢው ላይ ተመሳሳይ የኗሪዎች ቤት አለመኖሩን  መመልከት ሌላ አግራሞት የሚያጭር ነገር ነው። (የሰው ሀሳብ ነው ብለን ለአፍታ ስናስብ) ሌላው ቀርቶ በአካባቢው ለመውቀጫና ለወፍጮ የሚፈለፍሉት ድንጋይ እንኳን ያን ያህል ሊስተካከልና ቀልብን ሊያማልል፣ ገና ሲታይ እንዲያስቅ ተደርጎ የተሰራ ነው የሚመስለው፡፡ በየመንገዱ የገበጣ ጉድጓዶችን ለመፈልፈል የተጀመሩ DSC02900ድንጋዮችም አሉ። ታዲያ ግን የጉድጓዶቹ ቁጥር ከመደበኛው የገበጣ ጉድጓድ ቁጥር ሳይደርስ ወይ መሽቶባቸው ወይ ደግሞ ደክሟቸው ሳይጨርሷቸው ሄደዋል። በመነጋው አልተመለሱበትም…. ወይ ረስተውታል… ወይ ደግሞ ከብዷቸዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ ስሄድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአየር መበላሸት ምክንያት ጉዞው እየተስተጓጎለበት ካሰብነው ጊዜ በላይ ነበር የቆየነው። በግማሽ ልብ እንደተጉላላሁ ቢሰማኝም፣ በግማሽ ልብ ደስ እያለኝ ነበር፡፡ ላሊበላ እንደ አዲስ ሲታይ እንደ አዲስ ሰለሚናፍቅ አምሮት ለማውጣት ጥሩ አጋጣሚDSC01361 ነበር የፈጠረልኝ፡፡ ምናልባት ለዚህም ይሆናል – የሁለተኛው ጉዞዬ ህልም አይመስለኝም። ሆኖም ግን ስሙን በሰማሁ ቁጥር ይናፍቀኛል፡፡ ያኔ አብሮኝ የተጓዘ እንግሊዛዊ ወዳጄ ስለተመለከተው ነገር ሲነግረኝ፣ – ‘ከዚህ በፊት ብዙ ቦታዎችን ተመልክቼ ተደንቄያለሁ ላሊበላን የሚያህል አስደናቂ ነገር ግን አላየሁም፡፡ ወደፊትም የማይ አይመስለኝም፡፡’

ከላሊበላ 42 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘው ደግሞ በዋሻ 20ውስጥ የተገነባው ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ዋሻው ለቤተ ክርስቲያኑ እንደ ክዳን ሆኖለታል፡፡ ወይ ደግሞ ዋሻው እንዳይወድቅ ህንፃው ደግፎት ይመስላል፡፡ ይምርሀነ ክርስቶስ ከላሊበላ በ90 ዓመታት ገደማ  (ትክክለኛ ቁጥሩን አላስታውሰውም) የሚያረጅ ሲሆን በመፈልፈል ፈንታ የተገነባ ህንፃ መሆኑ ይበልጥ ያስገርማል፡፡ ግንባታ ከመሆኑ አንፃር በአካባቢው ተመሳሳይ ባይሆን እንኳን እንደ ነገሩ የተሞከሩ ግንባታዎች አይታዩም፡፡ እኔ ያየሁትን ተናገርኩኝ እንጂ፣ በላሊበላ ዙሪያ ይምርሀነ ክርስቶስdsc02870 ብቻ አይደለም ያለው፡፡ እንግዲህ የሞላለት ቦታው ደርሶ ልቡን በፈለገው ዜማና ስልት ማስዜም ነው፡፡ ምንም ሆነ ምን ግን የዜማው ይዘት

‘ዐይኔ ዓለም አይ እግሬ ደርሶ፣
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ፣’

ከሚል እንደማይዘል ይሰማኛል፡፡ ነገሬን ስቋጭም… ከላይ ካሰፈርኳቸው አንቀፆች አንዱን ደግሜ በማለት ነው…. ሀይማኖቱ — ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ጴንጤ፣ ሙስሊም፣ ጣኦት አምላኪ፣ ጠንቋይ ቀላቢ፣ ኢ-አማኒ፣ ግራ-ገብ…. ሌላም የፈለገውን ሆኖ፣ dsc03086መረዳቱ የፈቀደለትን እምነት የሚከተል ማንም፣ (በተለይ ኢትዮጵያዊ) በህይወት እያለ፣… በላሊበላ ለመደነቅና ቦታው ደርሶ አይቶ ‘በዐይኔ ዓለም አየሁ’ ለማለት፥ማህበረሰባዊ ጤና ያለው (socially healthy) ቢሆን በቂ ነው። ምናልባት ጤነኛነቱ ላይ የአገር ፍቅር ስሜት ቢጨምርበትና ባንድራው ትዝ ቢለው ደግሞ ደስታው እጥፍ ድርብ ይሆንለታል፡፡ — እንደ እኔ ነው!

 

DSC01372

DSC01441

DSC01442

DSC01447

DSC01458

19

21

bet emanuel lalibela

arcade-with-star-of-david-lalibela

aerial view,Lalibela comp

images

254881_533474059998532_520872321_n

ማስታወሻ፡ መጨረሻ ላይ በተከታታይ ያሉት አምስት ፎቶገራፎች ከኢንተርኔት የተገኙ ናቸው፡፡

መልካም የገና በዓል ለሚያከብሩት በሙሉ፡፡ 

ያልተዘመረለት – ‘የተረገመው ባለቅኔ’!!

ሁሉም ቢያገኘው፣ሁሉም ቢያነበው፣ ሁሉም ቢረሰርስበት፣ ሁሉም ቢማርበት፣ ሁሉም ቢያውቀው፣ ሁሉም ቢደመምበት፣ ሁሉም ቢያከብረው፣ ሁሉም ቢዘምርለት…ብዬ ብጓጓ፤ምድር በጥበቡ ከመረስረሷ ባሻገር፣ ነፍሱ ባለችበት ሀሴት ታደርጋለች፣….ብዬ ባስብ…. ከትናንት በስትያ (ወዳጄ አብዲ ሰይድ “ወፍዬ”ን ለጥፎ ቢቆሰቁሰኝ) ያልተዘመረለትና በወጉ ሳይታወቅ ያለፈው ታላቅ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ የባለቅኔ ምህላ መፅሀፍ ድጋሚ ይታተም ዘንድ ስንዱ አበበን ስጠይቃት፣ (ኮፒው በእጄ ቢኖርም፣ ቢያንስ የህትመት ወጪዋን አንባቢው ይጋራ ዘንድ፣ የርሷን (የአሳታሚዋን) ፈቃድና መብት እንዳልጋፋ በመፍራትና… መፍራቴን በመግለፅ…)

(እዚህ ጋር አብዲ በአበበ ተካ ወፍዬ ተቆስቁሶ…የተዘነጋ ገፅ በሚል ርዕስ የከተባት ማስታወሻ ብዙ ትጨምራለች፡፡ እኔም ይህችን እከትብ ዘንድ በእጅጉ ወስውሳኛለች፡፡)

በመጀመሪያ ህትመቱ ብዙ ብር በመክሰሯ ድጋሚ እንደማታሳትመው፣ ሶፍት ኮፒውን ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ስጦታ ይሆንላት ዘንድ በመሻት ለወዳጆቼ ባካፍልላት ደስታዋ መሆኑን ገለፀችልኝ፡፡  በፊት ከነበራት በሚጠልቅ ደግነት፡፡ ቀድሞ በአሳታሚ ድርጅቷ በኩል ካሳየችን በሚልቅ ርህራሄ፣ ፍቅርና ቅርበት፡፡ለነገሩ ወትሮም የርሷ ጉዳይ ጥበቡን መዝራት፣ ተሸጦ ገቢ ቢኖረው በትርፉ ሌላ ያልተዘመረለትን አንስታ ለማዘመር እንጂ መች ሌላ ሆኖ….፡፡

መቼም ጉኖዬን (ሙሌክስ እንደሚጠራት) አለማመስገን በብዙ ፍቅር አለማክበርና ስለርሷም  አለመዘመር አጉል ስስት ነው የሚሆነው፡፡ አድሮ የሚቆጠቁጥስስት፡፡ ከሄዱ በኋላም የሚያሸማቅቅ፡፡ እነሆ የመፅሀፉን ኮፒ ከዚህ ጋር ተያይዞ ይገኛልና ረስርሱበት፡፡ ፍቅርና ክብራችሁን ለፀሀፊው ለሙሉጌታ ተስፋዬ እና ለአሳታሚዋ (እንዲሁም አሳታሚዋ አመስግኑልኝ ላለቻቸው) እያበረከታችሁ አንብቡት፡፡ አንብባችሁ ስትወዱት ደግሞ ባላችሁበት ዘምሩለት፡፡ ሌሎችም ይዘምሩለት ዘንድ አስተላልፉት፡፡

Yebaleqine-Mehela

እኔ ሙሌን ሳስበው እንባ ይቀድመኛል፡፡ ሳላውቀው የቆየሁበት (በዘፈን ግጥሞቹ ተወስኜ) ጊዜ ይቆጨኛል፡፡ መሀላችን አለመኖሩ ያንገበግበኛል፡፡ በኖረና ብዙ በፃፈ….በኖረና ቋጠሮዎቹን በፈታ…. እያልኩ፡፡ እንደ አዲስ ዳስ ጥሎ፣ ንፍሮ ቀቅሎ ለቅሶ መቀመጥ ያምረኛል፡፡ ግና መፅሀፉን ከመደርደሪያዬ ላይ አንስቼ ጠረግ ጠረግ አድርጌ ማንበብ ስጀምር እንባዬ ይታበሳል፡፡ ብዙ መኖሩ ይሰማኛልና ቁጭቴን ሁሉ በደፈናው “ከንቱ” እለዋለሁ፡፡ ከንቱ ሀዘን፡፡ ደርሶ በጥበቡ የሚበርድ፡፡አንዳንድ ጊዜ ስቃዥ ደግሞ ቆሪጡን ማግኘትና ማናዘዝ ያሰኘኛል፡፡

የግጥምቆሪጡን፡፡  የቅኔዛሩን፡፡ ማስለፍለፍ….ማስቀባጠር…ማናዘዝ… ከስር ከስሩ እየተከተሉ መቃረም…. ወደኗሪውማጋባት… አይ ሙሌክስ፣ …እርሱን ሳስብና ሳገኝ(እድሜ ለስንዱ) እንዲህ ብቻ አይደለም የምሆነው፡፡ የቃላትን ስንፍና የሚያሳይ ብዙ የማይገለፅ ነገር፡፡ በቃላት ለመጫወት መፍጨርጨሬን (ግጥም መፃፍ መሞከሬን)ማ ስንት ጊዜ እንደሚኮረኩመው፡፡ ስንት ጊዜ እንደሚያሸማቅቀው…. የተረገመ!! ዛሩንባገኘው ኖሮ ግን ስንት ነገር አናዝዘው ነበር…. ስንት ነገርስ እቃርም ነበር…. እግሮቹ ስር ቁጭ ብዬ፣ ቢፈቅድ ፀጉሬን እየደባበሰ…. ቲሽ! አጉል ቅዠት!!

በመግቢያው ላይ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር (ነፍሱን ይማረውና) እንዲህ ብሎ ነበር… (አቤት…ከሙሌክስ ጋር ሲገናኙ ግን እንዴት ሆነው ይሆን? … ምናልባት ለስንዱ ደብዳቤ ከላኩላት ታስነብበናለች፡፡ እርሷ እንደው ደግነቷ ብዛቱ…፡፡)

ሙሉጌታ ግን ከቅዳሴ እስከ ቅኔ፣ ከዛም ተሻግሮ ቁርአን፣ ሀዲስንና መንዙማን የሚያውቅ ምሁር ነው፡፡ ይህም ባንዳንዶቹ ግጥሞቹ ውስጥ ይታያል፡፡ እግዜርንም ሸይጣንንም በእኩል ንቀት እየገረመመ ሲያናግራቸው እንደ ዳኛ ነው፡፡ ምንም ምክንያት ሳላገኝለት እውስጤ የሰረፀ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ በሞተበት ቦታና ሰዓት ከሰይጣን ጋር እየተፋጠጠ፣ እየተናነቀ ነበር ይሆን…

እዝጌርም ሰይጣንም የለም የሚሉ አንባብያን ሁሉ፣ እዝጌርም ሰይጣኑም የመለሱለት የራሱ ህሊና የፈጠረቻቸው ህልም ወይም ቅዠት ናት በሉ፡፡ ሌላ ማለት ብትፈልጉም መብታችሁ በህገ-መንግስቱ የተጠበቀ ነው፡፡

ስንዱዬ ደግሞ በምናቧ ከሙሌ ያስላከቸው ደብዳቤ ደግሞ እንዲህ ይቀነጨባል፡፡….

በምድር ስኖር ለግሌ ብዬ ያከማቸሁት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ እንግዲያውስ በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ከመስራት እስከ ኢህዴን – ብአዴን – ኢህአዴግ ድረስ ታገልኩ! በግሌ ያገኘሁት ነገር፣ መናቅ፣ መዋረድ፣ ለዐይን አለመሙላት ሆነ፡፡ ዋጋና ችሎታዬን ያወቁና የተረዱ ‹‹ጓዶች›› እንኳን የሚፈልጉኝና የሚያስፈልጉኝ ‹‹የድል በዓል›› በሚል ሰበብ ቅኔ እንድቀኝ፣ ግጥም እድገጥም፣ በአጭሩ የድግሳቸው አድማቂ፣ ተራ ‹‹አዝማሪ›› የሆንኩ እስኪመስለኝ መጎሳቆል ተሰማኝ፡፡

ይህንን ይሁን ብዬ ጓዶቼን ፈትቼ፣ ህዝቤንም አምኜ፣ ችሎታዬን ለዘፋኞች ልሰጥ አልኩና ተነሳሁ፡፡ ገበያው እጅግ የደራ ከመሆኑ የተነሳ እንኳን ሌላ ነገርሽን ከዐይንሽ ላይ ኩልሽን ሊሰርቁሽ የሚችሉ ሰዎች የበዙበት ሆነ፡፡ ይህን ትልቅ የገበያ ስፍራ ለመቀላቀል ስንት አሳር እንደቆጠርኩ ዛሬም ሳስበው ይዘገንነኛል፡፡ በቃ የስልጣናቸው የመጨረሻ ዳር ድንበር አሁን ትዝ አለኝ! ‹‹የኢኮኖሚው ባለቤት የፖለቲካውም ዋና ባለቤት›› እንደሆነው ሁሉ የስራው ባለቤቶች ነጋዴዎች ብቻ ሆኑ፡፡

‹‹እኔ እበላ – እኔ እበላ›› እያሉ ከሚሻሙት ጋር ለጨው፣ ለበርበሬ፣ ለውሎ ለአዳሩ እንኳ ብዬ አብሬያቸው ለመቆየት አቃተኝ፡፡ ይልቅ ጠጋ ያሉኝ ጋር በማርያም መንገድ፣ በማተብ፣ በክርስትና ለየግል ተነጋግረን፣ ቀኑን አሳምረንን ዱአ እያደረግን፣ ተፈጥሮንና ፈጣሪን ሳይቀር እየተፋጠጥን አብረን ጎጆ ልንወጣ ሰርተን ፈረንካው ሲገኝ ዐይኔን ለማየት እንኳ ይፀየፋሉ፡፡ አልፈው ተርፈው ብኩርናዬን ሳይቀር እንድሸጥላቻ ሁሉ ጠየቁኝ፡፡

ጉኖዬ – እንጂማ እኔ ወንድምሽ፣ ጥንቅቅ፣ ጥንፍፍ ያልኩ ጀግና ነኝ፡፡ ቅሱስም ንጉስም እሆናሁ አላልኩሽም ነበር… ካልሆንኩ ኋላ ትታዘቢኛለሽ፡፡ ለጊዜው ‹‹ብርዕ በደም ዕንባ››፣ ‹‹አንተሙሽር››፣ ‹‹ከመንበርህ የለህማ››፣ ‹‹ከነዓን ነው ዘንድሮን›› ግጥሞቼን ብቻ እንኳ ልጥቀስልሽ፡፡ እያደር እንደምትሰሙኝ ተስፋ አለኝ፣ ታዲያ እኔ እንዴት አባቴ አድርጌ ብኩርናየን ልሽጥ?!

ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ግጥሞችን፣ ሁለት ቲያትሮችን (ደጀ ሰላምንና ግምሻን) እና በርካታ ዘፈኖች ሰርቻለሁ፡፡ ውድነሽ በጣሙ፣ አማራ ነኝ ያውም ደሜ አረንጓዴ (ራዲዮ ፋና ሰነበው ቀድቶኛል፣ ጠይቀሽ ስናፈቅሽ ደግመሽ ስሚው፡፡ ‹‹ከመንበርህ የለህማ›› ኢትዮጵያ ሬድዮ ነበር፡፡ …እና ታዲያ ጉኖዬ አንቺ ግን ‹‹ጉዳዬ ሞተብኝ!›› ብለሽ በጣም ያዘንሽው ለእኔ ነው?

ይልቅስ ለሁሉም ሰው ይቅርታ መድረጌንና ይህ አካሄድ በእኔ ቢያበቃ ደስ እንደሚለኝ ንገሪልኝ፡፡ የሰራሁትን፣ ሀቄን፣ ገንዘቤን አንድጄ ብሞቀው እንኳ የሚያገባው እንዳልነበረ ደሞ መንገር እንዳትረሺብኝ!!

ቀብሬን ለማከናወን በእጅጉ የተባበሩሽን ጓዶቼን፣ መላ ጓደኞቼንና ቀባሪዎቼን አመስግኝልኝ፡፡ በምድር ሳለሁ አብረን የተሽከረከርናቸው ሰፈሮች የማስታውሳቸውን የምድር ጀለሶቼን አለምገናዎችን፣ ተረት ሰፈርን፣ ፈረንሳይ ለጋሲዎኖችንና ስድስት ኪሎዎችን፣ ቅድስት ማርያሞችን፣ ዶሮ ማነቂያዎችን፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድዮችን፣ አጠና ተራዎችን፣ ሰንጋ ተራዎችን….መላውን ወዳጆቼን ‘እንገናኛለን እኔ አልቆርጥም ተስፋ!’ ብሏል በይልኝ፡፡

ከልጆቼ ቀጥሎ የወለድኳቸውን ስራዎቼን እያስታወሳችሁ ‹‹አደራ ልጄን አደራ›› የሚለውን የብፅዓት ስዩምን ዘፈን እንድትሰሙልኝም ጋብዘዤያችኋለሁ፡፡ ጉኖዬ – ሆድ ሲብስሽ ደግሞ የሀና ሸንቁጤን ‹‹ሆዴ ባለአብሾ››ን ስሚ፡፡ በጣም ደግሞ የአበበ ተካን ‹‹ወፍዬ››ንም ስሚ!

ስሚ እንጂ …አንድ ቀን ‹‹ያንተን የተለያዩ ዘፈኖች መደዳውን ዛሬ አራት በኤፍ ኤም ሰማሁ›› ብለሽ በልብሽ ያጨበጨብሽልኝን ዕለት አስታውሼ ምን ትዝ አለኝ መሰለሽ… ያወጣሁላቸው ስሞች! ታምራት ‹‹ሀኪሜ ነሽ››፣ መሰረት ‹‹ጉም ጉም››፣ ፀደንያ ‹‹ገዴ››፣ ብፅአት ‹‹ገዳዬ››፣ ሸህ አብዱ ‹‹ሀዋብስል›› ኸረ ስንቱን አድምቄዋለሁ አያ!…ምንስ ቢሆን ሙሉጌታ ተስፋዬ ወዲ ሀለቃይ! ተጋዳላይ ነኝ እኮ!…

ከመፅሀፉ ላይ አሟልታችሁ ድገሙት፡፡ (ገፅ 133 – 135)

እስኪ ‘እውነት ከመንበርህ የለህማ’ን ፣ ቀንጭቤ ነገሬን ልቋጭ፡፡ወትሮም ለአመሌ ነው መቀባጠሬ እንጂ፣ መፅሀፉንካ ወረደ በኋላ ማን ይሰማኛልና?!

ምነዋ መንግስተ ሰማይ! የምህረትሽ ቀን ራቀ?
ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ?
ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ….ወዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ?
እንደ ዳጉሳ ድፍድፍ….ላቦትሽ ተንጠፈጠፈ
አሳርሽ ጠሎ አሰፈፈ

ምነው እርሾው ተሟጠጠ….ጎታው ጎተራው ታጠጠ
ረሀብ ላንቃው ፈጠጠ….ያዳም ልጅ አፅሙ ገጠጠ
ምነው ጭር አለ ቀየው! ሀሩር ነዲዱ በረታ
ኮርማው ጥማዱ ተረታ

ምነው ነበልባሉ አየለ! ማሳው ተንቀለቀለ?
ነቀለ ሞፈር ሰቀለ! ተገድራ ደቀለ
ምነው ምድር ጨነገፈች….ዝላ ተርገፈገፈች?
ካስማ እንደተደገፈች ምነው ሳታብብ ረገፈች፡፡

ምነው የናት ጡት ደረቀ…..አራስ ልጅ ተስረቀረቀ?
ምነው አንጀቱ ታለበ….በውኑ ተለበለበ?
ኮሶ ስንብቱን ለለበ
ምነው ወላድ ተነስለሰለ….ልሳነ ቃሉ ሰለለ
በቁሙ ቆስሎ ከሰለ፡፡

አቤት የርግማን ቁርሾ…
በንጣይ እርሾ መነሶ
ምነው ላይፀድቅ በቀለ
የሰው ልጅ ዋጋ ቀለቀለ
ትቢያ አፈር ተቀላቀለ፡፡
ሆድና ጀርባው ተጣብቆ
አንጀቱ በራብ ተሰብቆ
እንደፈረሰ ክራር ቅኝት
ሰርቅ እንዳነቀው ድብኝት….

ከመፅሀፉላይጨርሱት፡፡ (ገፅ 11)

ከዚህ ወዲያ ሽብር?!

አካላዊ ጥቃቶች (physical violences)

ባል ሚስቱን ደብድቦ ገደለ፣ ሚስት ባሏን ገደለች (የአቅምም ሁኔታ ታክሎበት ነው መሰል፥ ይሄ ብዙም አይሰማም። ሲሰማም ሞቱ እንኳን ለህብረተሰብ ጆሮ ወንጀሉን ለሚፈፅሙት ሴቶችም ድንገቴና አስደንጋጭ ነው የሚሆነው።) ፣ ልጅ አባቱን ገደለ፣ ልጅ እናቱን ገደለ፣ ባል ሚስቱን አቆሰለ፣ ሚስት ባሏን አቆሰለች፣ አሲድ ደፋባት፣ አሲድ ደፋችበት፣ ዐይኗን አጠፋት፣ ከፎቅ ወረወራት፣ በስለት ወጋችው….ሌላም ሌላም በተለያዩ  ምክንያቶች ተፈፀሙ የተባሉ የተለያዩ ዓይነት ጥቃቶችን በተለያዩ ጊዜያት ስንሰማ ኖረናልና፥ ነገሩን ጆሮአችን ለምዶታል። ያም ሆኖ እንዲህ ያሉትጥቃቶች ብዙ ጊዜ በደፈናው ይድበሰበሱና ‘ፆታዊ’ በሚል ስም ይጠቀለላሉ። ‘ህፃን ደፈረ’ማ ተነግሮንም ሳይነገረንም የሚገጥመንን የመብራት ፈረቃ ያህል እንኳን የማያስገርመን ነገር ሆኗል።

በወቅቱ ወሬውን ስንቀባበል፣ ስንሰበሰብ፣ ስናራግብ፣ስንፅፍ፣ ስናነብ፣ ነገሩን ስናወግዝ፣ “እግዚኦ” ስንባባል እንከርምና ወዲያው ወከባ በበዛበት የኑሮ ባህራችን ውስጥ እንደ አንዳች ነገር ጠብ ብሎ ይረሳል።ይደክመናል። ወይም ደግሞ ተከትሎ የሚመጣውን የፍርድ መጠን እንገምተውና ወሽመጣችን ቁርጥ ብሎ ጉልበታችንን ይወስነዋል። ያም ሆኖ… ድንጋጤና ሀዘኑ ባይሆን እንኳን ወሬ መቀባበልና ነገሩን ማውገዙም ቢሆን ብዙ ጊዜ በአድልዎና በቲፎዞ የሚደረግ ነው።ብቻ ግን የአንድ ሰሞን ጉድ ሆኖ ይከርማል። ወዲያው ደግሞ ይረሳል። ህይወት ትቀጥላለች።ምናልባት በሌላ የከፋ የወንጀል ዓይነት እየተተካና “የባሰ አታምጣ” እያስባለን።  – የሞተ ቀረበት!

እንዲህ ያለውን ነገር በፊት ፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ላይ ሲተላለፍ እናቴ “ቅጣቱን አብረው ካልነገሩ ባያወሩት ይሻላል። ካልሆነ አዲስ ዘዴ ነው የሚያስተምሩብን።” ትል ነበር። እውነት ነው። አንድ ዓይነት የወንጀል ዘዴ በዜና ሰበብ ለህብረተሰቡ ከተዋወቀ በኋላ በቀጣይ ተመሳሳይ የወንጀል ዓይነቶች ሲፈፀሙ እንሰማለን። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን አሲድ በመድፋት ጥቃት ማድረስ ነው። እንደ ቀልድ ተፈፅሞ (ምናልባት መጀመሪያ የደፋው ሰው ‘ይሁን’ ብሎም ሳይሆን በአቅራቢያው ስላገኘው ብቻም ሊሆን ይችላል።) እንደ ጉድ ተወራ፣ ከዚያም አሲድ መደፋፋት ተለመደ። ጆሮአችንም ለመወደው። እንዲህ ነን እኛ።

የቤት ሰራተኛዋ አሰሪዋንና ሁለት ልጆቻቸውን ገደለች

ዛሬ በጠዋቱ ከሸገር 102.1 የሬድዮ ጣቢያ የሰማሁት ጉድ ደግሞ ለጆሮዬ እንደመርግ የከበደ ነው። ምናልባት ከመሰል የሰራተኛ አሰሪ ጥቃቶች ጋር እስክንላመድ ድረስ። በርግጥ ሰራተኛ አሰሪን ሲበድል የመጀመሪያ አይደለም። ሆኖም ከዚህ በፊት የተለመደው ልጆችን ማጥቃት እንጂ እንዲህ ቤተሰብ መፍጀት አልነበረም። ወይም እኔ ስሰማ ይሄ የመጀመሪያዬ ነው። ፈፃሚና ተፈፃሚው ዞሮ ያው ሰው መሆኑ ከከዚህ በፊቶቹ ወንጀሎች ባይለየውም የጥቃት አድማሱ እንዴትና ወደየት እየሰፋ መሄዱን አጉልቶ ያሳየናል። ሸገር ላይ የተሰማው ወሬ “የቤት ሰራተኛ አንዲት ሴት ወይዘሮንና ሁለት ልጆቻቸውን ገደለች።” ብሎ ይጀምርና እንዲህ ያብራራል።…

“በሻሸመኔ ከተማ አንዲት የቤት ሰራተኛ በደመወዝ ጨምሩልኝ ሰበብ በተነሳ ጭቅጭቅ አሰሪ ወይዘሮዋንና ሁለት የአራት ዓመትና የሰባት ዓመት ልጆቻቸውን በተኙበት በመጥረቢያ ደብድባ ገደለቻቸው። ድርጊቱን ፈፅማ ለጊዜው ተሰውራ የነበረ ቢሆንም በፖሊሶችና በአካባቢው ነዋሪዎች ክትትል በወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ከተደበቀችበት ተገኝታለች።” (ቃል በቃል አልፃፍኩትም።)

የደቡብ ሰዎች (ወላይታዎች መሰሉኝ) እንዲህ ያለ፥ ለጆሮ ከባድ ነገር ሲገጥማቸው (ሲሰሙ) ‘ጎንዶሮ!’ ይላሉ። ‘አያድርስ’ እንደማለት ነው። አያድርስ ቢባልም ግን እነሆ ደርሶ የቤተሰቡ ህይወት ተቃርጧል። መቼስ ሁሉም በራስ ደርሶ ይታይ አይባል። ሆኖም… – ጎንዶሮ!

ምን ሰይጣን አሳታት?

መቼስይሄምድርጊት ማብራሪያ አያጣም ይሆናል። ምናልባት ወንጀለኛዋ የመክፈል አቅምና ፈቃድ ያለው የቅርብም ሆነ የሩቅ ቤተሰብ ካላት የሚቆምላት ጠበቃም አታጣም። ሰብአዊ ተቆርቋሪ ነን ባይ ኗሪዎችም ድርጊቱን በጓሮ መንገድ አዙረው ከሰራተኛ አያያዝና ከአሰሪዎች በደል ጋር አያይዘውት፥ ትንታኔ ሰጥተውበት ቢያንስ ለኗሪ ህሊና የወንጀለኛውን አጢሀት ሊያቀሉ ይሞክሩ ይሆናል። ወይ ደግሞ የወንጀለኛዋን የትምህርት ደረጃና የማሰላሰል ሁኔታ ተንትነው፣ ቢያንስ ልባቸውን አሳምነው በልባቸው ምህረት ያደርጉላትም ይሆናል። (ለነገሩ ይሄ በፍርድ ቤትም ቢሆን ዓይነተኛ የፍርድ ማቅለያ መሆኑን በተለያየ ጊዜ ታዝበናል።)

ከዚህ የሚተርፈው አብዛኛው የማህበረሰብ  ክፍል ግን እንዲህ ያለው ነገር ሲከብደው “ምን ሰይጣን አስቶት/ቷት ነው?” በሚል ቆራጣ አረፍተ ነገር ጠቅልሎት፥ አጢሀቱን ሁሉ ሰይጣን ላይ ነው የሚያላክከው። ይሄ ነቢይ መሆን ወይም ጥናት አያሻውም። ይልቅስ ያለፉ የወንጀል ታሪኮችንና ህብረተሰባዊ ትንታኔዎቻቸውን ማስታወስ በቂ ነው። ሰይጣን ግን ፈረደበት። የምር አንጀቴን ነው የሚበላኝ።

እዚህ ጋር ከዚህ በፊት የሰማሁትን ተረት (አፈታሪክ) ላንሳ…

የሆነ ገዳም ውስጥ ነው። የፆም ወቅት ላይ አንድ መነኩሴ እንቁላል ጥብስ ክፉኛ ያምራቸዋል። ሊያረሳሱት ቢሞክሩም ጭራሽ የሚባረር ዓይነት አምሮት አልሆነባቸውም። ከዚያም ዘየዱ። ሰብረው ቢጠብሱት አንድም እሳት የላቸውም ሌላም ደግሞ ሽታው በገዳሙ ቅፅር ውስጥ ተሰምቶ የሚያስቀጣቸው ይሆናልና እንቁላሉን ሳይሰብሩት ቅርፊቱን በጧፍ ለብልበው መጥበስ አሰቡ። ከዚያም ጧፉን ለኩሰው መጥበስ ጀመሩ። በመሀል ከየት መጡ ሳይባል የገዳሙ አበምኔት ወደመነኩሴው ማደሪያ ዘው ብለው ሲገቡ ድርጊቱን ተመልክተው ደነገጡ። ገሰፅዋቸውም። መነኩሴውም ጥፋታቸውን አጠር ባለች ማብራሪያ ይቅርታ ለመኑ። “ይቅር በሉኝ አባቴ። ሰይጣን አሳስቶኝ ነው።” ለካስ ቀድሞም አምሮቱን ሊያሳድርባቸው ቤት መጥቶ ኖሮ “ኧረ አባቴ ይህን ዘዴ፥ እኔም ካለዛሬም አላየሁት” ብሎ ሰይጣን ራሱ መልስ ሰጠ። ይባላል።

እንግዲህ ይሄ የሚያሳየን ነገሮችን በሰይጣን ላይ የማላከክ አባዜያችንን ጥልቀት ነው። ጥቅም የለውም እንጂ ብዙዎቻችን ሰይጣንን እንበልጠዋለን።

እናቱምገበያየሄደችበትእኩልየሚያለቅስበት’ –  የእኛ ፍርድ ቤት

በተለያዩ ጊዜያት፥ በዝርዝር የማላስታውሳቸውን ወንጀሎች፣ ጭራሽ ከማይመጣጠኑ ቅጣቶቻቸው ጋር ሰምቼ አንገቴን፥ ወንጀሉን በፈፀሙት ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ህጋችንና በፍርድ ቤታችን ላይ ደፍቼያለሁ። ፊቴ ከማይጠፉት እንደምሳሌም፡-  ባንድ ጎን፥ የሚስቱን እጆች በመጥረቢያ የቆረጠው 19 ዓመት ተፈረደበት፡፡ ሲባል እንሰማና፤ በሌላ ደግሞ፥ የ6 ልጆቹን እናት (ሚስቱን) አንዱን ልጅ ከኔ እንዳልወለድሽው በራእይ ታይቶኛል ብሎ የገደላት 6ዓመት ተፈረደበት ሲባል እንሰማለን።

ይህ ገርሞን ሳያባራ፣ ሚስቱ ላይ ግልፅ የሆነ ጥቃት አድርሶ ልጆቹ እንዳይመሰክሩበት አባትነቱ አራራቸው የተባለለት አባወራ ደግሞ፣ በነፃ ተለቀቀ እንባላለን። ሁሉንም የሚያደርሱን ቴሌቪዥንና ሬዲዮዎቻችን ናቸው፡፡ እንግዲህ ይህ ነው የኛ ፍርድ ቤት። አመክሮው፣ ጉቦውና ዝምድናው ተደማምረው የፍርዱን መጠን የት ሊያደርሱት እንደሚችሉም መገመት ልብ ላላ ሰው ቀላል ሂሳብ ነው። ታዲያ የኛን ፍርድ ቤት፣ “እናቱም ገበያ የሄደችበት እኩል የሚያለቅስበት” ብለው አሳነስኩት እንጂ አበዛሁት ይባል ይሆን?

ከዚህ በላይ ሽብር ከወዴት ይገኛል?

ያም ሆነ ይህ ግን ወንጀሎች በብዛትና በዓይነት እየተፈፀሙ ዘወትርጆሮአችንን ይደርሳሉ። ሰጋት ላይም ይጥሉናል። ከትንንሽ የቀበሌ ትኩረት ከተነፈጋቸው ጥቃቶች እስከ ትልልቅ አገራዊ ሽፋን እስከሚሰጣቸው ጥቃቶች ድረስ ብዙ እንሰማለን። በሞባይል ቀፎ ቅሚያና ኪስ በማውለቅ ሳቢያ በየቅያሱ የሚነሱ አምባጓሮዎችና በሰላማዊ ኗሪዎች ላይ የሚደርሱ አሰቃቂ ጥቃቶች ብዙ ናቸው። ‘በሩ ላይ ተወጋ። በሩ ላይ ተዘረፈ። በሌሊት የቤተሰብ ቤት ተሰብሮ ተሰረቀ።…’ የሚሉ ወሬዎች በተለይ በአሁኑ ወቅት በየቀበሌው ገነዋል። ‘ሌባና ዱርዬም በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቷል እንዴ?’ እስኪያስብል ድረስ። (ቢያንስ በእኛ ቀበሌ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ ተበራክተውና ተጠናክረው እየተፈፀሙ ነው።)

ይህንንም ሽሽት ሰዉ ወደቤቱ ለመግባት የሚጣደፈው ገና ጀምበር ስታዘቀዝቅ ነው። የቤቱን አጥር ቢጠነክርልኝ ብሎ አጥር የሚያስቀይረውም ብዙ ነው። ሲሆን የስልክ ቀፎም ይቀየራል እንጂ፣ በወርቅማ ማን ያጌጣል? ዱላው ይቀራል እንጂ ዝርፊያና ንጥቂያው በጠራራ ፀሀይ፣ በፖሊሶች ምስክርነት ሳይቀር ይፈፀማል። በየታክሲ ቦታው፣ በየመንገዱ፣ በየካፌው፣ በየጎዳናው፣ በየጥጋጥቁ…. አሸባሪው ብዙ ነው። ሰዉም ጥላውን ሳይቀር ይጠራጠራል።

‘የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም’ና የሰማውን አስታውሶ ራሱን ለመጠበቅ ይጨነቃል። በለመደውና ይሆናል ብሎ ባሰበው ሲጨነቅና ራሱን ለመጠበቅ ሲሞክር፥ ጭራሽ ያልሰማው ዓይነት ንጥቂያ ይገጥመዋል። ያልገመተው ዓይነት ጥቃት ይደርስበታል። ታስረው ሳይቆይ ስለሚፈቱ የከፋ ጥቃት ያደርሱብኛል ብሎ ስለሚፈራ ማንም ማንም ላይ መጠቆም አይፈልግም። ይፈራል። እንግዲህ ከዚህ በላይ ሽብር ከወዴት ይመጣል? (ለስንቱስ ነገር ይሆን ይሄን ሀረግ የምንመዘው?)

እንግዲህ በማንም ልገደል የምችልበት ሁኔታ እንዳለ ነው እና እየተማርኩ ያለሁት ከእንግዲህ አልፈራም። (ለነገሩ ድሮም አልፈራም ነበር።) እናም እላለሁ። የእኛ ፍርድ ቤት ነገሩን እንዴት ይመለከተው ይሆን? ‘አሸባሪ’ በሚል ታርጋ ቃሊቲ የታጎሩትና በስደት ያሉት የሚያማምሩ አዕምሮዎች በቴሌቪዥን፣ (ለዚያውም ክሱ ተጠናቅቆ ፍርዳቸው ሲነገር – በዜና ወይ በዶክመንተሪ) አደረጉ ተብሎ ከምንሰማው ነገር ባለፈ ምንም ሲያደርስብን አላየንም።

ማወቅ፣ መጠየቅ፣ መፃፍና ማንበብ በሚያሸብሩበት አገር እንደምን እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ችላ ተባሉ? ነው ወይስ ወንበር እንዳይነቀንቁ አያሰጉምና?! ባትሰማንም ቅሉ እንላለን – ቃሊቲ ሆይ በርሽን ከፍተሽ ውስጥ ያሉትን ሰላማዊ ዜጎች አስወጪና የሚያሸብሩንን አስገቢልን።

ወይ ጂጂ…! (2)

ዛሬ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ስለ አባይ የተጫወተችውን ሙዚቃ አዳምጬ እንደ አዲስ ብገረምና የምለው ግራ ቢገባኝ…. ከዚህ በፊት በ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አብርሀምና ሰርፀፍሬ ያዘጋጁት የነበረው የጣእም ልኬትፕሮግራም ላይ የሰጡት ትንታኔ ትዝ አለኝ፡፡ ከዚያም ቅጂው ያለበትን ፋይል ከማህደሬ በርብሬ አግኝቼ ወደ ፅሁፍ ገለበጥኩት፡፡ ያኔ በጣእም ልኬት ፕሮግራም መቋረጥ የተነሳ ከሸገር ሬድዮ ጋር የነበረኝን ቂም መርሳቴ ትዝ ቢለኝ ደግሞ፣ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ባለፈው ክረምት በደል ሳይቆጠር በደመቀ ሁኔታ የተፈፀመ የሆነ አገራዊ ክስተት ቢገርመኝ የጫርኳት ግጥም መሳይ ነገር እንዲህ ትዝ አለችኝ…

ሆደ ሻሽ ሀገሬ ቂም አለመያዙን ዛሬ ባየ ኖሮ፣
ያንገራገጨውን፣ የገላመጠውን የናቀውን ቆጥሮ፣
ከልቡ ባዘነ፣ ይቅር በሉኝ ባለ፣ በደሉን ዘርዝሮ፡፡

ሆ…. ‘ምን አገናኛቸው?!’ ኸረ ምንም! ግን እንደው ነገሩ ትንሽ ቢነካካ ለሸገርም ይሆን ነበር በማለት እንጂ፡፡ የምር ግን ሸገሮች ከልባቸው ተፀፅተውና በደላቸውን ዘርዝረው ይቅር ሊሉን በተገባ ነበር፡፡ ባወቁ…

ለማንቻውም እነሆ የጣእም ልኬት ትንታኔ በአባይ የዘፈን ግጥም ላይ….

ይህ ግጥም የአገራችንን ታላቅ ወንዝ አባይን በርዕሰ ጉዳይነት የሚያነሳ የዘፈን ግጥም ነው፡፡ ይህ የዘፈን ግጥም በእኔ እምነት እስከዛሬ ስለ አባይ ከተቀነቀኑት ዘፈኖች ሁሉ እጅግ የተለይ፣ ጥልቅና ምጡቅ ስራ ነው፡፡ አንዳንዶች በጓን ለማድነቅ ፍየሏን ማረድ አያስፈልግም ይላሉ፡፡ ይህ አባባል እውነትነት ያለው ነው፡፡ አተረጓጎም ላይ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር፡፡

አንዱን ለማድነቅ ሌላውን ማብጠልጠል መዝለፍና አንዱን ለሌላው ክብር መስዋዕት ማድረግ ፈፅሞ ያልተገባ ነገር እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አንዱ ከሌላው በሆነ ጉዳይ መሻሉን፣ በሌላ ነገር ደግሞ መድከሙን መግለፅ አያስፈልግም ማለት ከሆነ እጅግ አደገኛ አነጋገር ይሆናል፡፡

በህይወት እጅግ በርካታ ነገሮች አንፃራዊ ከመሆናቸውም በላይ በበጎ እይታ የአንዱን ከአንዱ መሻል ማውሳት ለጥበቡ በእድገትና በመሻል ጎዳና በርትቶ መግፋት እጅግ ረብ ያለው ግብአት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ አባይ የተሰኘው የእጅጋየው ሽባባው ግጥም ከእስከዛሬዎቹ አባይ ነክ ግጥሞች ሁሉ የረቀቀ ነው ስንል እንናገራለን፡፡ የስራዋን ግሩምነት ማስተጋባት ከገጣሚዋ ዋና አምሀዎች አንዱም ጭምር ነውና፡፡ ይህንን ለማለት ያስቻሉንን ምክንያቶች እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡

ግጥሙ ሲጀምር የሚያነሳው ስለ አባይ አፈጣጠርና አመጣጥ በመተረክ ነው፡፡ እናም የራሱን ምናባዊ ብየና ይሰጣል፡፡ ወደሚቀጥሉት የሀሳብ ድሮቿ ከመሸጋገሯ በፊት ገጣሚዋ መሰረቷን አጥብቃና አፅንታ ለመሄድ በመሻት ስለአባይ የመነሻ ቦታ አመጣጡን እና አፈጣጠሩን የምናብ ነፃነቷን ተጠቅማ ትበይናለች፡፡ ትተርካለችም፡፡ ስለታላቁ ወንዝ ስታወጋን ስለአመጣጡ ማውሳቷን እፁብ የሚያደርጉት አንዳንድ ምክንያቶች አሉ፡፡

አንደኛ የምታጫውተን ስለወንዝ ከወንዝም ከዓለም ረጅም ስለሆነው ስለአባይ ነውና፤ ወንዝን አንስቶ፣ ወራጅ ውሀን ጠቅሶ ስለመነሻና መድረሻ አለመናገር ግጥሙን ስነኩል ያደርገው ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ድንቅ ብየና ለግጥሙ ፅኑ መንደርደሪያና ልዩ ምልአት ሰጥቶታል፡፡ ሁለተኛ የገጣሚዋ ብየና የወንዙ መነሻ ያደረገው አንዱን ክፍለ አገር፣ አህጉር ወይም ግዛት በመጥራት አይደለም፡፡ የትኛውም ቀበሌና ጎጥም አልተጠቀሰም፡፡ ይልቅስ…

የሀሳብ አድማሷ ወዲያ ተመንጥቆ፣ ምድርን ተሸግሮ፣ ዓለምን ዘቅዝቆ እያየ….አባይ ህይወት እንድትቀጥል ለምድር ከገነት የተቸራት ቅዱስ የጠበል ውሀ መሆኑን ታበስረናለች፡፡ ባናውቅበት ነው እንጂ…የምትልም ይመስላል፡፡ እነኚህን ሀሳቦች ሁሉ የምናገኘው እንግዲህ በዘፈኑ የመጀመሪያ ክፍል ማለትም አዝማች ላይ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህንን ሁሉ ግዙፍ ፍልስፍና፣ እነኚህን ሁሉ አበይት ሀሳቦች የተሸከመ የስንኞች ህብር ሌሎች ተከታይ ስንኞችን ለማዝመት ብቁ በመሆኑና መንደርደሪያነቱም የጎላ በመሆኑ አዝማች የሚለው ስም ያንስበት ይሆናል እንጂ አይበዛበትም፡፡ አባይ ከ እንጂ እስከ እንደሌለው አበክረው ይሰብካሉ….

የማያረጅ ውበት…. የማያልቅ ቁንጅና…፣
የማይደርቅ፣ የማይነጥፍ፣ ለዘመን የፀና፣
ከጥንት ከፅንሰ አዳም….
ገና ከፍጥረት…
የፈሰሰ ውሀ… ፈልቆ ከገነት፡፡
ግርማ ሞገስ፣
የአገር ፀጋ፣ የአገር ልብስ…
ግርማ ሞገስ…አባይ፣
ግርማ ሞገስ፣
የአገር ፀጋ፣ የአገር ልብስ…
ግርማ ሞገስ….አባይ….
የበረሀው ሲሳይ፣ (4X)

ብነካው ተነኩ!…. አንቀጠቀጣቸው፣
መሆንህን ሳላውቅ፣ ስጋና ደማቸው፣
የሚበሉት ውሀ፣ የሚጠጡት ውሀ፣
አባይ ለጋሲ ነው… በዚያ በበረሀ…
አባይ… አባይ… አባይ… አባይ…
አባይ ወንዛወንዙ፣
ብዙ ነው መዘዙ…
አባይ… አባይ… አባይ… አባይ…
አባይ ወንዛወንዙ፣
ብዙ ነው መዘዙ…

አዝማች፡-

አባይ የወንዝ ውሀ፣ አትሆን እንደሰው!
‘ተራብን፣ ተጠማን…’ ተቸገርን ብለው፣
አንተን ወራጅ ውሀ….ቢጠሩህ አትሰማ፣
ምን አስቀምጠሀል ከግብፆች ከተማ?
አባይ…አባይ…አባይ…አባይ…
አባይ ወንዛወንዙ፣
ብዙ ነው መዘዙ…
የበረሀው ሲሳይ፣ (3X)

Oh, Gigi…!!

ወይ ጂጂ…! (1)

To my everyday surprise, and every spot astonishment, the way she expresses things is the way I want them be expressed!…and mostly, she makes things way far from my imaginations (and even from their nature), before she shows me nailing them down.

Her exceptional ability of playing with words (specially as a music lyrics) is something I would die craving for more!, &would dare to try one:) …aww, she put everything a scale up, so that no one dare to try. She knows how to mesmerize and quench a thirsty and a demanding soul effortlessly.

Most importantly, she understands the music; knows what to work, whom to work with, and for whom she is working it; upgrade her knowledge in many regards! Though I didn’t get chance to see any of her paintings, I’ve heard that they are amazingly professional; even herself tell that she is more sure about her artistic qualities in the painting than the music. (Sheger FM 102.1, interview with Meaza Biru)

I push she should sing more! I push she should paint more! I push she should write more! I even push she write a book…just she trigger her mom’s spiral. YeY, her mom is publishing a historical novel, which Gigi has rated as wonderful. I can’t wait…

The track, my player is playing now is….

ምን ትጠብቃለህ?…አቦ ሽማኔ፣ አቦ…
እንዲያ ወዲያ ወዲህ ትንቆራጠጣለህ፣
በሰፋው ደረትህ…ባማረው ባትህ…
እስኪ ተለመነኝ፣ ባይን በጥርስህ
የሰው ስጋ እርም ነው፣ ይቅር መብላትህ
አቦ ሸማኔ…

አደራ ብሰጠው፣ አደራ ልቤን
በልቶት ተገኝ አሉ፣ በጣጥሶ አንጀቴን
የደከመን ገድሎ፣ ፉከራው ምንድን ነው፣
ቀን የጣለው ለታ እርሱም እንደ እኔ ነው፡፡
እርም የእናቴን ስጋ፣ እምልልሀለሁ
ፍቅርን ካልሰጠኸኝ እሞትብሀለሁ፡፡
ያን እምቢ ያን እምቢ…ስለመን ከርሜ፣
ይኸው ተጃጃልኩኝ ደግሜ! ደግሜ! ደግሜ…

ባቱ፣ ተረከዙ፣ ሲጋው ተነባብሮ፣
ወገቡስ የሱ አይደል አይበላም ወይ አብሮ
ልጁ የወይን ሀረግ፣ ጠይም ዓሳ መሳይ
እኔ እናቱን ብሆን፣ ለሰውም አላሳይ፡፡

አንተ ልጅ አንተ ልጅ ያሙሀል
ልብ ይበላል እንጂ አይሰጥም ይሉሀል፣
በዚህች በማተቤ እምልልሃለሁ፣
ፍቅርን ካልሰጠኸኝ እሞትብሀለሁ፡

አሻፈረኝ እምቢ አትናገሩኝ፣
ወስዳችሁ ቅበሩኝ የሰው ነው አትበሉኝ፡
እኔስ ያንን ጀግና፣ ተኝቼ አላልፈውም፣
አገር ጉድ ይበለኝ፣ የኔ ነው…የኔ ነው….የኔ ነው….

የኔ ናት…የኔ ናት…. የኔ ናት… የኔ ናት…. ))

I love Gigi ( Ejigayehu Shibabaw ) so much!!