አሻም እቴ…!

የጊዜን ቡቱቶ አሳር፣ የዘመንን ውድቅዳቂ፣

የኑሮን ስንክሳር መዝዞ፣ የህይወትን ብጭቅጫቂ፣

ከ’ነ ዝብዝቡ ጎትቶ፣ ከ’ነ ኮተቱ ጎልጉሎ፣

ከ’ነ ተሳቢው ስቦ፣ ከ’ነ ጓዙ ካንቺ ጥሎ፣

እድል ስቃይ አሸክሞሽ፣

ህመምን ዱሎ ከአምሮሽ፣

ነጋ ጠባ ሲያስጨንቅሽ፣ ነጋ ጠባ ስትማቅቂ፣

በነገር ብዛት ስትዝዪ፣ በሀሳብ ብዛት ስትደቅቂ፤

ኦ ያ’ንቺስ….

ዘንበል ካረገሽ ችጋር፣ ማንም ላይረዳሽ ችሎ፣

የተጫነሽን መከራ፣ ማንም ላይጥለው ነቅሎ፣

ሁሉን በራስሽ ችለሽው፣ ለሌላ ሰው ላታስነኪ፣

ሁሉን በልብሽ ይዘሽው፣ ተስፋን በኑሮሽ ስትሰብኪ፣

ስኬትን – በልጆች ደስታ፣ በጥጋባቸው ስትለኪ፣

እርካታን – በውጣ ውረድ፣ ሥራን – በጥረት ስትሰፍሪ፣

የኑሮን ግለት ለማብረድ፣ ባ’ሳብ ላይ ታች ስትቧትሪ፣

ሀዘንን በልብሽ ይዘሽ፣ ተስፋን በፊትሽ ስትዘሪ፣

ልጅ ብቻ ጉልበት ሆኖልሽ፣ በእናትነት ስትዳክሪ፤

ኦ አንቺስ….

ወገብሽን እያለፋሽ፥ እለት በመሸ በነጋ፣

መባተል ሆኖብሽ እዳ፣ ሸክም ሆኖልሽ ጸጋ፥

ከቀን ትብስ ስትታገይ፥ የቀን ትሻልን ፍለጋ፥

መቼ ተስፋ ልትቆርጪ? መቼ እምነትሽ ሊናጋ?

ዙሪያ ገባው ሲያደናግዝ፣ ‘ሚያዝ ‘ሚጨበት ሲጠፋ፣

ህይወት ጣእሯ ጠንክሮ፣ ነገር ዓለሙ ሲከፋ፣

በሸክም ቤትሽን ልትጠግኝ፣ የኑሮን ቁስል ልታክሚ፣

ማልደሽ ከጫካ ገብተሽ፤ ጭራሮ፣ ቅጠል ልትለቅሚ፥

ስቃይሽን ታሰፊያለሽ፥ የኑሮን ክፍተት ልትደፍኚ፤

አካልሽን ትሰብሪያለሽ፥ ስብራትሽን ልትጠግኚ።

ኦ አንቺስ!

ልጅ – ዓለም ብለሽ ወስነሽ፣ ቤትን በልጅ ስትገድሚ፣

ለምሰሶው ፀንቶ መቆም፣ ለዓለምሽ ውበት ስትደክሚ፣

የሴት ወግ፥ የጓዳ ሥራ፣ የማጀቱ ጉድጉድሽ፣

ባልን ለመርዳት ከጓሮ፣ በእርሻ ሥራ መጠመድሽ፣

ሳይበቃሽ፣ አርፈሽ ሳታውቂ፤

ለአፍታ እንኳ’ አምረሽ፣ ሳትደምቂ፣

የመከራን ጥምር ሸክም፥ ከጫንቃሽ ላይ ልትንጂ፣

ለልጆችሽ ቀንቶ መቆም፣ ዘመንሽን ልትማግጂ፣

ራስሽን ታጎብጫለሽ – ካለቦታሽ በቦታቸው፤

ሰውነትሽን ታለፊያለሽ – ካለእረፍት ለ’ረፍታቸው፤

ኦ አንቺስ!

ማድያት ፊትሽን ወርሶት፣ ፀአዳው ገፅሽ ወይቦ፣

በጢስ፣ በጥላሸቱ፥ ገላሽ እንደጨርቅ ነትቦ፣

ቅጠልሽን ተሸክመሽ፥ ከመዝለቅሽ ከመንደሩ፣

እንስራ አዝለሽ ትርቂያለሽ፥ ውሀ ለመቅዳት ከጥሩ፤

ረፍዶ ልጅ ለማባበል፥ ባ’ንቀልባ አዝሎ ‘እሽሩሩ’፣

ቀን መሽቶ የባልን ዱላ፣ ከጀርባሸ ፥ ጦም ከማደሩ፣

ደግሞ በገበያም ቀን ሸክም፣ ሸጦ ለመግዛት መጣሩ፣

ልጅ አድጎ ተነሳ ሲባል፣ በቦታው ሌላ ሊመጣ፣

አንቀልባው ከመታጠፉ፣ ‘ሳጥን ሳይገባ ሊወጣ፤

አቤት ያንቺስ አበሳ፣ እግዚኦ የጀርባሽ ጣጣ።

ጭነትሽን ላያግዙሽ፣ ልጆችሽ ላያቀሉልሽ፣

በመሳሳትሽ ተገፍተው፣ በመጫን ማውረድ ላይረዱሽ፣

ወልደሽ – የወላድ መሀን፣ አፍርተሽ – አልቦ ፍሬ ዘር፣

ሰጥተሽ አዱኛ ብላሽ፣ ወርቅ ሰጥቶ፥ ወሳጅ ጠጠር፤

ዘርሽ የትም ተበትኖ፣ በየወደቀበት ባክኖ፣

ለስንት ብቅል ሲጠበቅ፥ በየደረሰበት መክኖ፣

ያልመከነውም ተለቅሞ፣ በወፎች መንጋ ተወስዶ፣

ከአድማስ ወደዚያ ተሻግሮ፣ ከባህር ወዲያ ተሰድዶ፣

ኦ ያ’ንቺስ!

ከቶ ምን ልበልሽ እቴ፣ ‘አሻም!’ ነው እንጂ ስትመጪ፣

የኑሮን ሸክም ልትንጂ፣ ሸክም ሸክፈሽ ስትወጪ፣

የኑሮን ሸክም ልታቀይ፣ ሸክም ጠፍረሽ ስትወርጂ፣

በህይወት ያ’ሳብ መንገድ ላይ፥ ከ’ነ ጭነትሽ ስትነጉጂ፣

ገና ከሩቁ ሳይሽ፥ ከ’ነ ጭንቀትሽ ስትደርሺ፣

___ሌላማ ምኑን ችዬበት? ‘አሻም!’ ልበልሽ እንጂ፤

አሻም እቴት! አሻም፣ አሻም፣ አሻም እ’ቴ!

የት አውቄበት ልረዳሽ? የት ችሎት ሸክሙን ጉልበቴ?

ላበርታሽ በቃል፣ በሃሳቤ፤ እስኪ ልርዳሽ ባንደበቴ፤

አሻም! አሻም! አሻም እቴ!

ግን ተስፋ አለኝ…

ከያሉበት ተጠራርተው፣ ልጆችሽ ሲሰባሰቡ፣

ተንጠራርተው ሲደርሱበሽ፣ ትጋት ልፋትሽን ሲያስቡ፣

‘ሆ. . .’ብለው ደጅሽ ሲመጡ፣ ማጀት ጓዳሽን ሲከ’ቡ፣

ተስፋ አለኝ እቴት፣ . . . ይህም ያልፋል፤

ጀርባሽም ከሸክም ያርፋል፡፡

/ዮሐንስ ሞላ/

(ማስታወሻ: ይህ ግጥም ከዚህ በፊት በተደረገ የ”በጥበብ እንኑር” የስነ-ፅሁፍ ውድድር ላይ ተሳትፎ በ3ኛ ደረጃ ተሸላሚ ነበር።)

ወይ ትምህርት…

‘የብቁ ባለሞያ ያለ’ vs ‘የስራ ያለ’…

የአገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብዙ የተባለለትና፣ እንደማስቲካ ዘወትር በየሰዉ አፍ የሚላመጥ ነገር ነው። – ላይዋጥ፣ ላይተፋ በአፍ የሚንከባለል። የሚያሳሳ። ተሰልችቶ የሚያስጠላ። ጣእሙን ይቀይር ዘንድ ተአምር የሚናፍቁለት። እንደነገሩ ችግሩ በየጊዜው እየተነሳ ቢደከምለትም እስከዛሬ ይህ ነው የሚባል ጉልህ ለውጥ አላሳየም። እንዲያውም አንዳንዴ ለመፍትሄ የታሰበው ጥረት ዘርፉን ለሌላ ድካም አቀብሎት ያልፋል።….ምናልባትም ትግበራ ላይ ያለ የለውጥ ዘዴ (strategy) መጨረሻው ሳይታይ በአናቱ ሌላ እያስነደፈ።

የጥራት ማነሱን ጉዳይ ባለማመን ፀንቶ (አንዳንድ ጊዜም በስሱ እያመነና ከትናንት የተሻለ መሆኑን ለማስረዳት ላይ ታች እያለ) የሚታገለው መንግስትም ጥራቱን ለማሻሻል (ወይም ለመሸፋፈን) በተለያዩ  ጊዜያት የተለያዩ  እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። “የአንዳንድ ፀረ – ልማት ሀይሎች…” ወሬ ነው፥ ብሎ የሚፈርጀውና “የለም” ብሎ የሚከራከርለት የትምህርት ጥራት ማነስ ጉዳይ… በአሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን በመከላከልና (defence) ለመለወጥ (ለመሸፋፈን) ሰርክ መኳተኑን በመመልከት መረዳት ቀላል ነው። – ከራሱ ውጪ ሌላ አስረጂ ሳያሻ!

በተለያዩ  ጊዜያትም የትምህርት ፖሊሲውን በማደስ፣ የትምህርት አሰጣጥና የተማሪዎች የምዘና መንገዶችን በመከለስ፣ የመማሪያ መፃህፍትን በመቀየር፣ ለግል ተቋማት የማስተማር እውቅናና ፈቃድ በመስጠት፣ አንዳንዴም ባልታሰበ ሁኔታ የሰጠውን ፈቃድ በመንጠቅ፣ አዳዲስ ተቋማትን በመክፈት፣ የተቋማቱን የአገልግሎት መዋቅር በመለወጥ፣ ለመምህራን ስልጠናዎችንና ስብሰባዎችን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም በሌሎች በብዙ መንገዶች ቢሞክረውም ውጤቱ እንኳን ለጥጋብ፥ ለአቅመ ረሀብ ማስታገስም አልደረሰም። ዛሬም ሞያዎች ‘የብቁ ባለሞያ ያለ’ ብለው ይጮሃሉ። በአንፃሩም ብቁ ተብለው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁትም ‘የሥራ ያለ’ እያሉ ይባክናሉ።…ያላሰቡትንና ሰዎች የማይመርጡላቸውን ስራ እየሰሩ።

የተውኩትን ነገር ተመክሬ… (ኮብልስቶን እንደምሳሌ….)

የስራ ትንሽ የለውም። አርቀን ሳናስበው እንኳን ማንኛውም ዓይነት ስራ የሆድን ገመና ሸፍኖ  ቀጥ አርጎ ከሰው እኩል ያውላል።  ብዙ ነገር ሳንጎትት በዚህ ብቻ ስራ ክቡር መሆኑን አምነን እንናገራለን። አግባብ የሆነ የስራ ክፍፍል (rational division of labor) መኖሩም ለእድገትና ለስራው ጥራት የሚኖረው አስተዋፅኦም ጉልህ መሆኑን እናውቃለን። ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን ማንኛውም ስራ ለደረጃው በሚመጥን ባለሞያ ካልተሰራ፥ ስራው በሌላ ተሰርቶበታልና የሚመጥነው ባለሞያው ስራ ከመፍታቱ ባሻገር ትልቅ የሰው ሀብት ብክነትም ያስከትላል።

ለዚህም ነው ከላይ ‘ያላሰቡትንና ሰዎች የማይመርጡላቸውን ስራ እየሰሩ’ ያልኩት። እንደ ምሳሌ እንደ ትልቅ የገቢ ማስገኛ ተቆጥረው ዝናቸው በአገሩ ከናኘ ስራዎች መሀል ኮብልስቶን አንዱ ነው። በእርግጥ ወጣቶችን አሰባስቦ፣ ስራን ያለመናቅ ስነልቦናን ገንብቶ ማሰራትና፣ ራሳቸውን እንዲረዱ ማድረግ ጠቃሚነቱ አያጠያይቅምና በራሱ ትልቅ ስኬት ነው። ለሰራተኞቹ የገቢ ምንጭ፣ ለከተማዎቹም ውበት ነውና፥ በአገሪቱ ላይ የኮብልስቶን ንጣፍ ስራ በሰፊው መሰራቱ ማንንም አይሳዝንም። አያበሳጭም።

በድንጋይ ማንጠፍ ስራው ላይ የተሰማሩ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን መኖራቸውን መስማት (ለዚያውም በመንግስት የመገናኛ አውታሮች በኩል) ግን ያማል። ሲሆን ሲሆን በዚህ የስራ ዘርፍ ላይ መሰማራት የነበረባቸው ትምህርታቸውን ከተለያዩ  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጨረሱት ወጣቶች ሳይሆኑ ሌሎች (እነሱ ትምህርታቸው ላይ ውጤት ለማምጣት ደፋ ቀና ሲሉ ስራ ፈት የነበሩ አሊያም በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን መቀጠል ያልቻሉ) ወጣቶች ነበሩ።

እንዲያም ሳይሆን ቀርቶ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ስራውን እየሰሩ ቢገኙ (መርጠውትም ሆነ ምርጫ አጥተው) ኑሮአቸውን ለማሻሻል ክብሬን፣ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ፣ ስራ ሳይንቁ ተገኝተዋልና በማህበረሰብ ደረጃ አድናቆት ይቸራቸው ይሆናል። ከዚያ ባለፈ ግን እንደ ጥሩ ነገር ታይቶ ለመንግስት የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሲውሉ መመልከት ትዝብት ነው ትርፉ። – አንድም ላስተማራቸው ዜጋዎቹ የሚመጥን የስራ ዘርፍ ቀድሞ አላመቻቸምና፤ ሌላም በድንጋይ ንጣፍ ስራ ላይ መሰማራት የሚችሉ ወጣቶችን በቅናሽ ወጪ ማምረት ሲችል ያን አላደረገምና እንደ ኪሳራ እንጂ እንደ ትልቅ ስኬት ሊወሰድ አይችልም።

በወቅቱ የነበረው የሰዉም አፀፋ ይህን ድርጊቱን የሚያወግዝ እንደነበር ለብዙዎቻችን ትኩስ ትዝታ ነው።  ዛሬም ድረስ እየገረብን የምንታዘበው። በዚህም “ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” ይሉት ተረት ለመንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተተርቷል። ምናልባት ትርፍና ኪሳራውን ቀድሞ ሳያሰላ አምልጦት ያደረገው ነገር ነበር፤ ብንል እንኳን የትምህርት ጥራቱን በተመለከተ ማጣፊያው እንዳጠረው የኮብልስቶን ስራ በግልፅ የሚያሳየን አንድ የአደባባይ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። (ትምህርታቸውን ጨርሰው በበሬ አረሱ ስለተባሉ ወጣቶችም ትዝብቱ ከዚህ አይለይም።)

‘ቄሱም ዝም! መፅሀፉም ዝም!’

ዛሬም በዘርፉ የሚያጠኑ ምሁራን ስለ ትምህርት ጥራቱ አሳሳቢነት ይጮሃሉ። ችግሮቹን መዝዘው ስለመፍትሄው ይባክናሉ። ከወረቀት በዘለለ መፍትሄ ሲሆኑ ግን አንመለከትም። እንደ ምድረበዳ ጩኧቶች ናቸው። ጯሂውና አድማጩ በአንድ ዓይነት መስመር ውስጥ አይደሉምና ትርፉ ከግለሰብ እርካታ ባለፈ ስምና ድካም ነው። መንግስትም ቢሆን በአንድ ጎን የችግሩን መኖር ላለመቀበል እየተከላከለ፣ በሌላው ደግሞ ነገሩን ለማሻሻል (ወይም ገፅታውን ለመቀየር) ይረዳል ያለውን መንገድ ሁሉ ይሞክራል።

ከነዚህ መሀል ግን ተማሪዎችን በፓርቲ አባልነት መመልመልና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሰበሰቡ ማመቻቸት፣ ተማሪዎቹን የገመናው ተካፋይ ቤተሰቦች በማድረግ ጥረታቸውን ሁሉ የራስን ገመና በመደበቅ ትርምስ ውስጥ ጥሎት፣ ነገሩን በማይደፈር ማእቀፍ ውስጥ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ተማሪዎችም ስለጥራቱ እና ችግሮቹ ከማሰብና ከመጠየቅ ይልቅ ገፅታውን በመሸፈን ስራ ላይ ተጠምደው ስለነገ የፓርቲያቸው ህልውና ይብሰከሰካሉ። – ገፁ ገፃቸው መሆኑን አምነው ተቀብለዋልና።

ባለፈው ወዳጃችን ማህሌት ፋንታሁን  “የፍርሀት ዘመን” በሚል ርእስ እንዳስነበበችን የዘመናችን የፍርሀት ዛር በከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ላይ ልዩ መልክና ገፅ ይዞ፣ እንዲሁም በነገ ጥቅም (job security) ሰበብ ዳብሮ የተንሰራፋ ነው። ተማሪዎች በችሎታቸውና በራሳቸው ጥረት ካለመተማመናቸው ወይም ደግሞ የስራ ዓለሙን አሰራር ቀድመው በማወቃቸው የተነሳ የነገ እንጀራቸውን ለማብሰል ይረዳቸው ዘንድ ማገዶአቸውን የሚያቀራርቡት ገና ስራቸው ሳይጠነክር ከመነሻው ነው። – በፓርቲ አባልነት! ከቀናቸው እና የነቁ ታላላቆች ካላቸው ደግሞ ከበሶ ጋር አደራ ተቋጥሮላቸው። – ‘Green ካርዷን…!’ በምትል ለዛ ባላት ቀጭን ሀረግ።

ይሄም በተማሪዎች ዘንድ የሚኖረውን የፉክክርና የመበላለጥ ስሜት ያቀጭጨዋል። በከንቱ የራስ መተማመን (ጉራ) እና ትእቢት እንዲታነፁም ያደርጋል። ልቡን በትዕቢት ቀድሞ የሞላ ተማሪ ደግሞ ትምህርት የመቀበል ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ አናሳ ነው የሚሆነው። በዚያም እንደነገሩ ካለምንም ማማረርና ማንጎራጎር ቆይተው ወደየመጡበት ይመለሳሉ። – ተመርቀው።

ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ

ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከዚህ በፊት ሆሳህና ዩኒቨርስቲ ተብሎ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎለት አዲስ የተገነባ (በግንባታ ላይ ያለ) ዩኒቨርስቲ ነው። አዲሱ ስያሜ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ አልተወደደም የሚል ነገርም ከተለያዩ  ምንጮች ሰምቼአለሁ። አሁን ግን ዋቸሞ ዩኒቨርስቲን ላስተዋውቅ አይደለምና ስለስሙ ለውጥ አግባብነትና ኢ-አግባብነት አልጫወትም። ግን እንዲያው ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ይሄ ዩኒቨርስቲ ነውና ከርሱ ጋር የተያያዘውን ላጫውታችሁ።

ባለፈው ረቡእ (ጥቅምት 20) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ እግር ጥሎኝ (ጉዳይ ገጥሞኝ) ተገኝቼ ነበር። የሄድኩበት ጉዳይ ፈፃሚዎች ስብሰባ ላይ ነበሩና እስኪወጡ ድረስ ዐይኔን ግድግዳ ለግድግዳ እያንከራተትኩ ያገኘሁትን ሳነብ ቆየሁ። በመሀል….

እኔ ኧከሌ…በህክምና ትምህርት ዘርፍ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የተመደብኩ ሲሆን፣ ወደ ጥቁር አንበሳ የሚቀይረኝ ሰው ካለ ወሮታውን እከፍላለሁ።

ስልክ…..

ምናምን የሚል የተማሪ የቅያሪ ማስታወቂያ አንብቤ በጣም ተገረምኩኝ። በርግጥ ስሙን ከዚህ በፊት አዲስ ከተገነቡ ዩኒቨርስቲዎች ዝርዝር ውስጥ አይቼዋለሁ። የሆሳህና ዩኒቨርስቲ አዲስ ስም መሆኑንን ግን እስኪነገረኝ ድረስ አላውቅም ነበር። ለአቅመ ህክምና ትምህርት ማስተማር መድረሱንማ ጠርጥሬም አላውቅ። እርሱም ነበር አግራሞቱን የጫረብኝ። (ምናልባት ማስታወቂያው በተማሪዎች ለፌዝ የተለጠፈ እንደሆነ እንጃ….ተገንብቶ ያላለቀው ድህረ-ገፁ ላይ ግን ህክምናን ትምህርት የለም።)

እስከጊዜው ድረስ… – ‘ለምን?’!

በእለቱ ቤቴ ስመለስ፥ ነገሬን ቅደም ተከተል አስይዤ ጨዋታውን ለማዋዛት በማሰብ፥ በመፅሀፈ ፊት (facebook) ግድግዳዬ ላይ

ኢትዮጵያ ‘ወቻሞ’ (or something like that) የሚባል ዩኒቨርስቲ እንደተሰራላት ሰምቶ የሚያውቅ እጁን ያውጣ!!! :)) የምር…

ብዬ ለጠፍኩኝ። ብዙ ጊዜ FB ላይ የሆነ ነገር ስፅፍ በጨዋታ ደንብ ነው። ያኔም ነገሩን ሳነሳው ከጨዋታ ባለፈ ቁም ነገር… ምን ያህሉ ሰው ዩኒቨርስቲውን ያውቀው ይሆን? ከሚል ሀሳብ በቀር ሌላ ምንም ዓይነት ፍላጎት ኖሮኝ አልነበረም።

ከአስተያየቶቹ መሀል ግን አንድ ወዳጅ ነገሩን ከፌዝ (በቃሉ ላይ ከማላገጥና ቃሉ የሚመለከተው ብሄርን ከመናቅ) ወስዶት ተበሳጨ። እኔም ነገሬን ለማስረዳት ላይ ታች አልኩኝ። – ከነ ስሜቴና ብስጭቴ! ግን መግባባት አልቻልንም። ሀሳቤን በመጠየቅ ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ ቃሉ ላይ እንደተሳለቅሁኝ ደግሞ ደጋግሞ ነገረኝ። እኔን መኮነኑ ውሀ ያነሳለት ዘንድም የጠቀሰው “ዋቸሞ” በማለት ፈንታ “ወቻሞ” ብዬ መፃፌን ነቅሶ በማውጣት ነበር።

በእርግጥ ስሙን ስፅፈው ተሳስቼያለሁ። እንዲህ ያለ የቃል አፃፃፍ ስህተት ግን እኔም ስሰራው ወዳጄም ሲታዘበው የመጀመሪያችን ሊሆን አይችልምና ነገሩ ከማስተካከያ ባለፈ ለዘለፋ አያበቃም ነበር ባይ ነኝ። በቅንፍ ውስጥ (or something like that) ስል… ስሙን በትክክል መጥራቴን ከመጠራጠሬ የመጣ መሆኑን በግልፅ አስቀምጦ ለሚፈጠረውም ማንኛውም ዓይነት ስህተት እንደ ቅድመ-ይቅርታ ያገለግለኛል ብዬ አስቤም ነበር። ይሄንንም አብራርቼም መግባባት ሊታሰብ አልቻለም። እንግዲህ ይሄ ንትርክም የትምህርታችን አንድ ውጤት ሊሆን ይችላል። ላይሆንም ይችላል።

ያም ሆነ ይህ ግን የማይጠይቅ ዜጋን ማፍራት ተጠያቂነትን ከማጥፋቱ ባሻገር የሚጠይቁ ዜጎችን ለማሸማቀቅና ለመዝለፍ ዓይነተኛ መንገድ ነው። ሀሳቡን በነፃነት መግለፅ የማይችልም ሀሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሚጥሩ ምስኪን ነፍሶችን በሀሳባቸው ለመናቅ ሲጥር ይስተዋላል። “ለምን?” ተብሎ ሳይጠየቅ ያደገ ሰው “ለምን?” ብሎ ይጠይቅ ዘንድ አይማርም። “ለምን?” ብሎ የማይጠይቅ ሰውም ለሰዎች ምክንያታዊነትና ማብራሪያ ቦታ የለውም። ይህም ጉዳቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአገር እና ለኗሪዎቿ ነው። ለመጪው ትውልድ የሚያስተርፈው ርዝራዥም ብዙ ነው።

ጨዋታዬን ስጠቀልለውም ትምህርትን የትም እና ከማንም ይማሩታልና የትምህርት ጥራታችን እንዲጠበቅልን እየተማፀንንና እየፀለይን እስከ ጊዜው ድረስ ከአገኘነው ነገር ሁሉ እንማር። በፍርሀት እና በራስ ከመተማመን ማነስ የተነሳ፥ የጎደሉንን እውቀቶችም በመጠየቅና በንባብ እንሙላ። ታናናሾቻችን “ለምን?” ብለን እየጠየቅናቸው “ለምን?” ብለው የሚጠይቁ ተቆርቋሪ ዜጎች እንዲሆኑ እናግዛቸው።

Serious love with passengers? Eh…

It is common to see while people look for related anecdotes to the ideas they want to articulate at different points of their life. Here I am triggering a related spiral, in order to underscore life in its social aspects; just as my knowledge has allowed me, as my experiences have thought me, jus in my current opinion, at this time &place settings — I am saying “LIFE IS A TAXI”. Here we go… 😀

Life is a taxi, we’re drivers of our own taxis; through modes of communications, adaptations, or other kinds of social affections. Depending on the social status of the drivers, &the qualities of the highways, the taxis size may vary and it may have more than a single doorman (co-driver, literally families and familial friends) throughout the voyage on the road of life;… whatsoever, life is a taxi.

When some doormen get off their duty for reasons, they may deteriorate the drivers’ attendance too…simply the drivers too may be off till they get back their colleagues, or acclimatize themselves with new doormen-incase of entire loss, and vice versa. But the taxi won’t stop before the driver!: it is a taxi after all, life has to be continued, and the taxi should support the owner’s daily subsistence 🙂

Taxis are here and there, passengers (literally friends) are so; both running for an equilibrium, and keeping the engine in motion throughout. Passengers could take the taxis at any time and place, and could leave them at any whereabouts; and in the later case, the taxis door should be open to let them go, though. In the interim of the voyages, it is common and possible that the drivers and doormen may have a real sweet time with their passengers…that sweetness may happen among the passengers too; and possibly everyone in the taxi might have enjoyed that test…but they’ve to go, if they have decided already.

All passengers could not stay in the taxi throughout, and doormen and drivers could say ‘please, don’t go’ for no avail…if they say let’s go, they’ve to go…it is a taxi after all; they may need to go to other activities, or change another taxi. As well, there are also annoying passengers, drivers, and doormen; and they may get kicked even before they reach to their destinations…whatsoever, both parties are on their ever lesson taking activities. Moreover, taxis could face techincal or mechanical problems in the middle of the roads; and passengers may cooperate with the drivers and doormen to repaire, or leave them with the defects.

To this end…. I wonder, how many doormen I have, where my late passengers are now, to what destination I will drive with my current passengers, which taxis I am a door man in, which taxis I am a passenger in, which taxis I served either as a passenger or a doorman…I just wonder:) All in all, ‘never fall in real love with passengers, unless you are sure you can keep them as your doormen!’….is my opinion 😉

Let’s check our seat belts, and let’s go…!! Life is a taxi after all!!! 😉

P.S. This was originally posted on FB, on February 17, 2011