Tag: 16DaysofActivism
የታላቁ ሩጫ እለት የተሰማኝ የመጠቃት ስሜት…
ከጓደኞቼ ጋር ነበር የሮጥነው። በርግጥ “የሮጥነው” ማለት ይከብዳል፤ የእርምጃ ያህል ነበር። ትንሽ ዱብ ዱብ እንልና ብዙ ሰከም ሰከም እንላለን። ሲለን በቡናና በቢራም በቀላሉ የማይረጥብና የማይወራረድ ርዕስ አንስተን እናላምጠዋለን። ከፌስቡክ ስታተስ እስከ መፅሐፍት አንስተን እንጥላለን። ሸጋ ጊዜ ነበር…
ስንሮጥ ስንሮጥ….
ከሰዓታት ባንዱ ቅፅበት፥ ተግተልትለን መጨረሻ ገባን። መግባታችንን ተከትሎ፥ “እንኳን ደስ አላችሁ።” አለ የመድረኩ አጋፋሪ። ወዲያውም፥ “የመጨረሻዎቹ ተሳታፊዎች ገብተዋል…” ብሎ የመዝጊያ የሚመስል ነገር አወራ። ባልሰማውም ፊቱን ወደ እኛና ቀድመው ወደገቡት ሰዎች መለስ ቀለስ እያደረገው የሚያስበሽቀን ይመስላል። የመጨረሻ በመሆናችን የዛለ ሳቅ ተቀባብለን ከማረፋችን፥ ሰዓቱ በመርፈዱ ግቢው ውስጥ የነበሩ ፖሊሶች እንድንወጣ ያዋክቡን ጀመር። እኛም ብድግ ብድግ ብለን ወደ መውጫው ሄድን።
ፊትና ኋላ ሆነን ከግቢው ወጥተን እየተጠባበቅን፣ ሁለት ተራምደን አንዱ ውኅ ሊገዛ ሲቆም፥ ስንቆም፤ ትንሽ ቆመን ሁሉም ሲሰበሰብ፥ ስንሄድ… ከፊት ለፊታችን ፒካፕ መኪና አየን። የሩጫውን ቲሸርት የለበሱ ጎረምሶች እየተፈናጠሩ ሲሰፍሩበት ስናይ፥ የወዳጄ እብደት ታክሎበት “ጆዬ ፒካፕ… እንጫን።” አለችኝ። መልሴን በድርጊት ስሰጣት፣ ወደኋላ ዞሬ ሌሎቹን እየፈለግኩ ወደመኪናው አመራሁ። የተጫኑት ሰዎች ጋቢና በነበረ የይሁንታ የእጅ ምልክት መሆኑን ስላስተዋልኩ፥ እንደማንከለከል በማመን ነበር። ግን የመኪናውን ጫፍ ስይዘው “አይቻልም” አለ አንደኛው።
የሰፈር ድግስ ቤት ቀድሞ ገብቶ የሰፈር ልጆች ላይ ሃርደኛ እንደሚሆን ከልካይ መስሎኝ፥
“ለምን? አንተ ተሰቅለህ የለ?” አልኩት፤ በዚያ ድካም ላይ ሊኖረኝ በሚችል ትህትና።
(ለራሱ ሊፍት ለምኖ ሌላውን ይከላከላል? ትልቅ አይደለ? በሰው ንብረት አዛዥ መሆን ደርሶ)
“አይቻልም። ውሻ” አለኝ። አይቻልምን ደጋግሞ ብሎኝ አልሰማ እንዳልኩት ሁሉ ስቦት።
ሊፍት (ለያውም ፒካፕ ጀርባ) ለመሳፈር በማሰቤ ብቻ “ውሻ” ስባል፣ ከባለጌ አፍ ብቆጥርበትም… የሆነ ዓይነት መጠቃት ተሰማኝ።
መሳደቡ ባለመኪናውን እንደሚያውቀውና እንደ ልጅ ‘የእኛ መኪና ነው’ ማለቱ ገባኝ። በጣም ስለደከመኝ የመጣያ ጉልበት አልነበረኝም እንጂ ስድቡ አብሽቆኛል።
“እና ምን ያሳድብሃል? በስርዓት አትናገርም?” አልኩት የሞትሞቴን፣ በደከመ ንቀት እያየሁት።
ወዲያውም፥ “ነይ ባክሽ እንሂድ” ብያት መሄድ ጀመርን።
(በከመሬት ተነስቶ ተሳዳቢነቱ ንቄው ከርሱ ጋር ላለመሳፈር ብዬ ተውኩት እንጂ፥ ራሱ ሊፍት ጠይቆ መሆኑን እርግጠኛ ስለነበርኩ፥ ዝም ብዬው ለመሰቀል እሞክር ነበር።)
እሷም “ጆዬ ና በቃ። ይቅርብን።” አለች።
“ሰዉ ግን ምን ሆኖ ነው? አይሆንም አይልም? ይሳደባል እንዴ?” ብያት እሷን አስከትዬ መሄድ ቀጠልኩ።
“ና ና…” የሚል ድምፅ ተከተለኝ።
(አስፓልቱ ሙሉ ሰው በመሆኑ እኔን አልመሰለኝም ነበር።)
ተደገመና እኔን መሆኑ ገባኝ።
(ሰውዬው ጤና የለውም? ወይስ ለነገር ነው የሮጠው?)
“አንተን እኮ ነው። ና…”
ዝም ብዬ እሄዳለሁ።
(ቆይ እርሱን ና ብለው ይመጣልኛል?)
“ቁም! አንተን እኮ ነው…”
ዝም ብዬ እሄዳለሁ።
(ቁም ብለው ይቆምልኛል? ምኔ ነው እሱ? ጓደኛዬ ነው ወይስ አባቴ ነው? አጎቴ ነው? ወይስ የአባቴ ጓደኛ ነው?…ጮሆ ቁም የሚለኝ?)
በጣም ስለደከመኝ መመላለሱን አልፈለግኹም። ብፈልግም ጉልበት የለኝም ነበር። ሌላ ጊዜ ቢሆን ይሄ ከማላልፋቸው ጥቃቶች አንዱ ነው። ያን ቀን ግን ዞርም ሳልል በቸልታ መሄዴን ቀጠልሁ። (በምን አቅሜ?)
ወዲያው ጠንካራ እጅ ከትከሻዬ ጠፍንጎ እንደ ሳጥን አዞረኝ። ሌላ ፊት ነበር። ጋቢና የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም።
“እየተጠራህ አይደል? ንቀት ነው?” አለ ብዙም ሳይቆጣ፤
(ያመዋል እንዴ ሰውዬው? እርሱን ጠርቼው ዝም ቢለኝ ‘ንቀት ነው?’ እለዋለሁ? መጥራቱስ ንቀት ካልሆነ ክብር ነው?)
“ልሰቀል አልኩት ለራሱ ሊፍት ጠይቆ ከለከለኝ። በቃ ለምን ይጨቃጨቃል?” አልኩ ዐይኔን በብስጭት አጉረጥርጬ። (ጉርጥ)
“ሲጠራህ እኮ መቆም አለብህ።” አለ በማግባባት ዓይነት።
“ጥጋበኛ።” እያለ ሌላው ሊጎትተኝ እጁን ይሰዳል። በዚህ ቅፅበት፥ የመኪናዋ ታርጋ “ፖሊስ” ማለቷን አስተዋልኩ።
(የፖሊስ መኪና የሚገዛው እኛው በምንከፍለው ግብር አይደል? ደሞዛቸውስ? ታዲያ ምናለ ቢያንስ በትህትና ቢናገር?)
ምናልባት ስራ ላይ ነበሩ። ወይ እንደእኔው ከጓደኞቻቸው ጋር ሊሮጡ ነበር የመጡት። …ግን መጠቃቴ ጎልቶ ተሰማኝ። ሆድ ባሰኝ። መጀመሪያ “ስንት ዓይነት ሰው አለ?” ብዬ ያለፍኩት መጠነኛ ጥቃት፣ ህመም ሆነብኝ። ሲሆንስ፥ ወጉ ጉልበተኞች እንዲህ ሲያበሻቅጡን ፖሊስን ማመንና ተገን ማድረግ ነበር። እልሄ ቢገነፍልም፥ ምንም እንደማላመጣ ሳውቅ ዋጥኩት። ዝም ማለት እንደሚሻል ወሰንኩ። የያዘኝ ሰው ነገሩን ማብረድ ይፈልጋል። የገባው ነገር ነው።
“ሲጠራህ አትመጣም? አታከብርም? ፖሊስ ሲጠራህ…” አለኝ ተለሳልሶ።
(ጠንቋይ እቀልባለሁ? ብቀልብስ ፖሊስ ስለጠራኝ ብቻ ማሸርገድ አለብኝ?)
“ለጠራኝ ሁሉ እሄዳለሁ? እርሱስ ሰው አያከብርም? ዩኒፎርሙን ለብሶ ቢጠራኝ በግዴ እሄድለት ይሆናል። እንደ እኔ ቲሸርት ለብሶ ሲጠራኝ ግን ማን ነው ብዬ ነው የምሄደው?” አልኩት ሳላስጨርሰው።
አንድ አራት ወጠምሻዎች ከመኪናው ላይ እንጣጥ እንጣጥ እያሉ ከበቡኝ። አወራረዳቸው የፊልም ቀረፃ ይመስላል። ሁሉም ቲሸርት ስለሆነ ያደረጉት ፖሊስ መሆናቸውን ማወቅ ይከብዳል።
“ጥፍራም! አምጣው ጫነው።”
“ሌባ….”
“ጣቢያ….”
“ልክ ይገባል አምጣው።”
“አትለምነው…”
ሌላም ሌላም…ዛቻዎች ከአፎቻቸው እየተነባበሩ ሾለኩ። አንደኛው ሊጎትተኝ ሲሰነዝር፥
“ልቀቀኝ። በቃ እኮ እንደ እኔው ሯጭ መሰለኝ ሲጠራኝ አልሄድኩም። ፖሊስነቱን እንዳውቅለት ነው ደግሞ ከላይ ለመጫን ስል የሚሳደበው? ዝም ብሎ የፖሊስ መኪና ነው አይለኝም?” አልኩኝ።
(የፖሊስ መኪና መሆኑን ቀድሜ ባውቅ እንዴትም ቢደክመኝ ለመጫን አልጋበዝም ነበር።)
ምንም እንደማላመጣ አውቃለሁ። የብሶቴን ነው እንደምንም የተናገርኩት። ይህም ሆኖ ላለመናገር የዋጥኩትና ከጓደኞቼ ጋር የተበሳጨንበት ይበዛል። ሰዉም ለመናቸው… የጭንቀቱን አስረዳቸውና ለቀቁኝ።
የመጠቃት ስሜቱ ግን አብሮኝ ከረመ። ለብዙኛ ጊዜ አቅመ ቢስነቴን አየሁ። እፅፈዋለሁ አላልኩም ነበር…
————————-
ታዲያ አሁን በምን ትዝ አለኝ?
እስኪ እኔን — ሴት፥ ፖሊሶቹን — ወንድ አድርገን ስለን በሁለት ፆታ እንየው….
“ነይ” ስንላት
“ሲጠራሽ አትመጪም ንቀት ነው?” ስንላት
“ሲጠራሽ አትሄጂለትም? አታከብሪም ወንድ ሲጠራሽ?” ስንላት…
ለጠራት ሁሉ ባለመቆምና ባለመዞር መብቷ ስትሄድ፥ ስትሰደብ….
አይከብድም?
ቢደረግብን የማንወደውንና እኛ ዘለን ሌሎች ላይ የማናደርገውን ነገር ሰዎች እኛ ላይ ሲያደርጉት ስናይ አይከብድም? ከዚያ በላይስ የመጠቃት ስሜት (sense of helplessness) ከወዴት ይሰማል?
ሰው በሰውነቱ ይከበር! የሰው ልጆች ጥቃት ይቁም! የሴቶች ጥቃት ይቁም!