ሴት ነሽና

ሴት ነሽና፥
ሰውነቱን፣ ክብሩን ትቶ፣
ቀሚስሽን ወንድ ይለካል
ደግሞ ሲለው ተንጠራርቶ
ተጠራርቶ… ደፍሮ ይነካል፤
 
ሴት ነሽና፥
“ተው” ብትዪው፥ እንደመብቱ
“ዝም በይ” ይላል በአንደበቱ፤
ማንም የለም “ተው” የሚለው፣
ሁሉም አጋዥ አበርቺው ነው፤
 
ሴት ነሽና፥
የሀሳብሽን ቁመት ልቀት
የህልምሽን ስፋት ርቀት
ወንድ ሰፍሮ ይመዝናል፣
በእርሱ ገበያ ይተምናል፤
 
ሴት ነሽና፥
በአውሬነቱ እርቃን ቀርቶ፣
ሀፍረት ጥሎ፣ ሱሪ ፈትቶ፣
ሰው ገላ ላይ ይፈነጫል፣
“አሳስታኝ ነው” ብሎ ይጮሃል፤
 
ሴት ነሽና፥
ለእርሱ ስሜት ለአውሬነቱ
ጥጋት ሆኖ ለነውሩ፣ ለሴሰኛ ሟችነቱ
አንቺን ያማል ሁሉም ወጥቶ ከየቤቱ፤
 
ሴት ነሽና፥
እሱ ሰፍሮ አጥሯል ብሎ
የደፈረሽን ተንጠላጥሎ፣
ሁሉም ወጥቶ ያጸድቅለታል
“ማን ተራቆች” አላት ብሎ፤
 
ሴት ነሽና፥
ሰዓት እላፊሽ በሰፈሩ ይተመናል
መውጫ መግቢያሽ በጎረምሳ ይሰፈራል
 
በየት ገባሽ?
በየት ወጣሽ?
ከማን ታየሽ?
ማንን አየሽ?
ሁሉም ጣቱን ይቀስራል፤
 
ሴት ነሽና፥
አትስሚያቸው!
እኔ እኔ ነኝ በይ ንገሪ፣
ብርቱነትሽን ለዓለም አውሪ፤
ለጉልበታም ጉልበትሽን
ለብልሁም ብልሃትሽን
አሳያቸው፣ እንዳጸሚ!
አንቺ ላንቺ፣ በርቺ ቁሚ
 
ቆሞ ሄደሽ ስትልቂ፣
ያኔ ይመጣል ማሪኝ ብሎ
ሂስ ቅጣቱን ተቀብሎ፣
የሰው ሁሉ ቁም ነገሩ፥
ሴት ነሽና!
ሴት ሴታታ…
ምታበሪ በቀን ማታ!
 
/ዮሐንስ ሞላ/
ሴትን አንኳስሶ የሚናገር ከራሱ ነው ክህደት የሚፈፅመው። ያ ባይሆን ደግሞ፥ አለማወቁን ነው የሚገልጠው። ይገልጠው አለማወቅ ባይኖረው፥ አውቆ ቸል ማለቱን ያሳያል። ወይም፥ ከእውቀቶቹ ሁሉ “ሴት”ን በአግባቡ ማወቅ ጎድሎት ሳይሆን አይቀርም። ወይ ደግሞ፥ ያልተጣራ የውስጥ ችግር ይኖራል። – እንጂማ፥ “ካላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም” እንዲሉ፥ ማንም ስለፆታው ያደረገው አስተዋፅኦ በሌለበት ሁኔታ፥ ፆታው ከርሱ የተለየውን ዝም ብሎ አይፈርጅም።
 
ሴት የሚለው ቃል እንደ ቅፅል፥ ፆተኝነትን አቀንቃኝ ያልተገባ ልማዳዊ አጠቃቀም እንዳለው ቢታወቅም፥ እንደ ስም፥ የወል መጠሪያ ነው። …እንደ ወል ስም፥ ሴት: ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከመሀይም እስከ ምዑር፣ ከቤት እመቤት እስከ ድርጅት እመቤት፣ ከምንዝር እስከ አለቃ፣ ከወላድ እስከ መሀን፣ ከወታደር እስከ ጦር መሪ፣ ከአገልጋይ እስከ እመ ምኔት፣ ከፀሐፊ እስከ አንባቢ… ሌላም ከ—እስከ ተብሎ ተዘርዝሮ የማያልቅ የተለያዩ የኑሮ እርከኖች ላይ የሚገኙ፣ በተፈጥሮአዊ ባህርያቸው እንስት የሆኑ ሰዎች ተለይተው ይታወቁበታል።
 
“ሴት” ብሎ በጅምላ የሚዘልፍ፣ የሚሰድብና ደምሳሳ ድምዳሜ (hasty generalization) የሚያደርግ ፆተኛ፥ የስኬት መሰረት የሆኑ የታፈሩና የተከበሩ ሴቶችን ታሪክ አያውቅም። ወይም እያወቀ እንዳላወቀ ሆኗል። …እያወቁ እንዳላወቁ መሆን ደግሞ ካለማወቆች ሁሉ የከፋና በራስ ጥመት የሚመጣ በመሆኑ፥ ይበልጥ የማህበረሰብ እና የጋራ ግንዛቤዎች ጠንቅ ይመስለኛል።