Adwa_Menelik

ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ በ፲፱፻ ዓ/ም የዠመራቸው በሽታ እየጸና ሔዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎ፣ አንደበታቸው ተዘግቶ እንደቆየ በታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፮ ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የሸዋ ንጉሥ (፲፰፻፶፯-፲፰፻፹፩) በኋላም፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት (፲፰፻፹፪-፲፱፻፮) በነበሩበት ዘመን ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይሆን፣ ክፉውን በደግነት እየመለሱ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ አገር የሚሰፋበትን ልማት የሚዳብርበትን፣ ሕዝብ ዕረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን ከማሰብና ከመፈጸም አልተቆጠቡም። የአውሮፓን ኃያል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል።

የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ዜና ዕረፍት በወቅቱ ለመደበቅ ቢሞከርም ወሬው ካንዱ ወደሌላው እየተላለፈ ነገሩን የተረዳው ሁሉ፣ «እምዬ ጌታዬ፣ እምዬ አባቴ» እያለ በየቤቱ ያለቅስ ነበር። ከአልቃሾቹ አንዱ፣

ፈረስ በቅሎ ስጠኝ ብዬ አለምንህም
አምና ነበር እንጂ ዘንድሮ የለህም፤

አለ ይባላል። በንጉሠ ነገሥቱም ሞት ዋናዎቹ ሐዘንተኞች ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ፣ ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱና ብዙ መኳንንት አሉ። በልቅሶውም ጊዜ እቴጌ ጣይቱ፣

ነጋሪት ማስመታት፣ እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን፣
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን›› ብለው ገጠሙ ይባላል።

ከልጅ ኢያሱ ቀጥለው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለቱ ለምኒልክ ተብለው የነገሡት ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ የሚከተለውን ሙሾ አወረዱ።

እልፍ ነፍጥ በኋላው፣ እልፍ ነፍጥ በፊት፣ ባለወርቅ መጣብር አያሌው ፈረስ፣
ይመስለኝ ነበረ ይኼ የማይፈርስ።
ሠላሳ ሦስት ዘመን የበላንበቱ የጠጣንበቱ፣
የትሣሥ ባታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ።
ብትታመም ልጅህ እጅግ ጨነቀኝ፣ ብትሞትስ አልሞትም እኔ ብልጥ ነኝ።
ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድሁዎ፣ አንዠቴን ተብትበው ምነው መሔድዎ።
አሳዳጊ አላንተ አላውቅም እናት፣ ምነዋ ሞግዚቴ እንዲህ ያል ክዳት።
ቀድሞ የምናየው የለመድነው ቀርቶ፣ እንግዳ ሞት አየሁ ካባቴ ቤት ገብቶ።
እጅግ አዝኛለሁ አላቅሽኝ አገሬ፣ የሁሉ አባት ሞቶ ተጐዳችሁ ዛሬ።
ትንሽ ትልቅ አይል ለሁሉ መስጠት፣ ከጧት እስከ ማታ ያለመሰልቸት።
ድርቅ ሆኗል አሉ ዘንድሮ አገራችሁ፣ ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ።
አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ
መከራም እንደሰው ይለመዳል ወይ።

/አቶ ተክለጻድቅ መኩርያ፥ «ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት» ውክፔዲያ ላይ እንደተጠቀሰው።/

መጽሐፍት ሲያዞሩ…

n1704ፀሐፊውን… የቻሉትን አሰሩ፣ የቻሉትን አባረሩ፣ የቻሉትን ደግሞ ለማስፈራራት ላይ ታች አሉ። የቻሉትን የሚፈልጉትን እንዲጽፍ አድርገው እቅፍ ድግፍ አድርገው ያዙት።
 
የመጽሐፍትን መታተም ለማስታጎልና የፀሐፊዎችን ቅስም ለመስበር፥ የመጽሐፍት ህትመት ዋጋን በወረቀት እና በሰበብ አስባብኩ ከፍ አደረጉት።
 
ነባር መጽሐፍትን በጨረታ እስከመሸጥ ድረስ፥ የአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች መጽሐፍትን ድራሽ ለማጥፋት የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ። ከነሱ ሀሳብ የተለየው ላይ ሁሉ ጥርሳቸውን ነከሱበት።
 
“ለሽብር የሚያነሳሱ መጽሐፍት” ብለው በራሳቸው ጊዜ ተሸብረው፣ ሕብረተሰቡ እንዲሸበር እና ተሸማቆ እንዲኖር፣ ሲያነብም እንዲሳቀቅ አዋጅ አንጋጉ።
 
ይኸው ደግሞ፥ መጽሐፍ አዙረው እውቀትን በማስፋፋትና ራሳቸውን በመደጎም የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ምስኪን መጽሐፍት አዟሪዎችን ማሰር ጀመሩ።
 
የሪፖርተር ጋዜጣ ዜና እንዲህ ይነበባል….

አመፅ ቀስቃሽ ናቸው የተባሉ መጻሕፍት በመሸጥ የተጠረጠሩ አዟሪዎች ታሰሩ

ኅብረተሰቡን ለአመፅ የሚገፋፉና ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ መጻሕፍት በማዘዋወርና በመሸጥ የተጠረጠሩ መጽሐፍት አዟሪዎች፣ ከነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መታሰራቸው ታወቀ፡፡

ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ መጻሕፍት አዟሪዎች በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች መታሰራቸውንና በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ቤተሰቦቻቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አዟሪዎቹ የተጠረጠሩት ሕዝብ የሚያነሳሱና አመፅ የሚቀሰቅሱ መጣጥፎችን በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በማተም ክስ ተመሥርቶበት የሦስት ዓመታት ጽኑ እስራት የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ በቅርቡ ‹‹የፈራ ይመለስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹‹የኦሮሞና አማራ የዘር ግንድ›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍና ጋዜጠኛ ሙሉ ቀን ተስፋው ‹‹የዘመኑ ጥፋት›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ በማዞር ሲሸጡ ስለተገኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ቀደም ብሎ ክስ ተመሥርቶበትና ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ቅጣት የተጣለበትን መጣጥፍና በድጋሚ በመጽሐፍ መልክ ያሳተመውን መጽሐፍ ማሠራጨት ወንጀል መሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ማስረዳቱ ታውቋል፡፡ ሌሎቹም የተጠቀሱት መጻሕፍት አመፅ ቀስቃሽ መሆናቸውን በመግለጽ መሠራጨታቸው ተገቢ አለመሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቶ፣ መጻሕፍቱ ሲታተሙ ያተማቸው ማተሚያ ቤት በመጽሐፉ ላይ መግለጽ የነበረባቸው ቢሆንም ሳይገልጹ መቅረታቸውንም አክሏል፡፡ ይኼም ሆን ተብሎ መንግሥት ቁጥጥር እንዳያደርግ በድብቅ የሚሠራ ሕገወጥ ተግባር መሆኑን በማስረዳት፣ ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ተገልጿል፡፡

የተወሰኑ አዟሪዎች መጻሕፍቶች ተነጥቀው ሁለተኛ እንዳያዞሩ ፈርመው መለቀቃቸውንና ማተሚያ ቤቱን እንዲጠቁሙ ተገደው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መጻሕፍት አዟሪዎች ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በድጋሚ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

አሜሪካ ድምጽ ሬድዮም ቀድሞ እንዲህ ዘግቦት ነበር…

መጽሐፍ አዟሪዎቹ በተለይ የተመስገን ደሳለኝ፣ የሙሉጌታ ሉሌና የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ መሸጥ እንዳልቻሉ እነዚህን መጽሐፍትና ሌሎች የታሪክና የፖለቲካ መጽሐፍት ይዘው ሲገኙ እንደሚደበደቡ፣ እንደሚታሠሩና አንዳንዴም ለመለቀቅ ከደንብ አስከባሪዎች ጉቦ እንደሚጠየቁ ተናገሩ።

‘መጽሐፍቱን ማዞር ወንጀል ቢሆን’ እንኳን፥ በጎልማሶች ት/ት (መሰረተ ትምህርት adult education) ፕሮግራም እንኳን ማንበብና መጻፍ ያላስተማሩትን ዜጋ ምን ብለው “አመጽ ቀስቃሽ” መጽሐፍ ይዘህ ዞረኻል ብለው ያስሩታል? ያዋክቡታል? ይቀጡታል?
“አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” አሉ። ከቻሉ ሀሳብን ማሰሩን አይሞክሩትም ነበር?!