የገና በዓል ልዩ ዝግጅት | Ethio Teyim | Episode 45

የገና በዓል ልዩ ዝግጅት! “ያረፈደ ልደት”፣ “እሱ”፣ ገና በጉራጌ፣ በዓል እና ናፍቆት | Gena | Ethio Teyim | Episode 10

ካለ ሰው…

DS1j6ZEX0AAcrwwከነድህነቱ ወዘናው ፊቱ ላይ ጨፍ ያለ ምስኪን፤ ዘሩ ምን ሆነ ምን፥ ፈገግታው ከልቡ ፈልቆ ፊቱ ላይ፣ ጥርሱ ላይ፣ ዐይኑ ላይ፣ ግንባሩ ላይ ሁሉ የሚከለበስ ድሃ። ቂጡ ሁላ የሚስቅለት ዕድለኛ፥ ምንም የሌለው፣ ሁሉም ያለው። የአዲስ አባ ሰው፣ የአገር ሰው!
 
ገመድ እና አንድ ሁለት የተሳሉ ማረጃ ቢላዋዎችን ይዞ አሳራጅ የሚቃርም በሬ አራጅ። የበግ ቆዳ ያሌው። በአዲስ ልብስ ያሸበረቁ፣ በአዲስ ልብስ እና በጸዴ ምግብ ተስፋ በቀብድ የሚቦርቁ ሕጻናት።
 
እዚህ እና እዚያ በወዳደቀ ቀጤማ፣ መንገዱም የበዓል ይመስላል። የሚነሳለት ቆሻሻ ባይኖርም፣ ሁሉም የበዓል መልኩን ይይዛል። በፍቅር ዐይን እንደሚያዩት ሁሉ፣ ያምራል! በዋዜማ እና በእለቱ ፀሐዩዋም ትለያለች። የቅዳሜ ፀሐይ ተሞሽራ ተኳኩላ ማለት ነው!
 
ከየቤቱ፣ ከየግሮሰሪው፣ ከየሱቁ፣ ከየመደብሩ የሚወጣው የ”ስንት ገባ ዶሮ” …”ቅቤ እና ሽንኩርቱ እንዴት ነው?” …”ሰንጋው ስንት ተገዛ?” …”ቅርጫ ተሟላችሁ?”… ጥያቄው፥
 
“እኔማ ቀን አቁላላቼ ጣጣዬን ጨርሻለሁ” …”ጠላው አልፈላ አለኝ” …”ሸቀበኝ። ቀላጭ ዱቄት ሆነብኝና ዳቦው ማስቲካ ሆኗል።” …”ትንሽ ቂጡ አረረብኝ ባክሽ” …”ኤጭ! መብራቱን አስሬ ሲያበሩ ሲያጠፉት ዳቦውን አበላሹብኝ” …”ሊጥ ታቅፌ ቀረሁ። መብራቱ ሚመጣም አልመሰለኝ። ማዕድቤት ገብቼ ልጋግር እንጂ” የሚሉ የሚራገሙ፣ የሞኮሩ ድምጾች፥
 
እና፣ ሙዚቃ… የበዓሉን ጠረን ይዞ በየመንገዱ ላይ፣ በየቅያሱ ላይ ይደፋዋል። ሁሉም የራሱን ቅባት ከሌላው ቅባት እየቀየጠ ፊቱን ይደባበሰዋል። በጠረኑ ጦዞ ከፍ ይላል። በዓል አልወድም የሚል ዘበናይ እንኳን ከሁሉም አይጎልም። የግዱን እንኳን አደረሰህ/ሽ ተባብሎ ይተቃቀፋል።
 
ሻኛቸው ብቻውን፣ ከእሱ በቀር ያለው ሰውነታቸው ብቻውን የሚንጎማለሉ የእርድ ከብቶች፣ ከዚህም ከዚያም ድምጻቸው የሚሰማ በግና ዶሮዎች እንደ ቅርብ ዘመድ ትዝ ይላሉ።
 
የላቱ ሙቀት በህጻናት የተለካ፣ ቆለጥ እና ፊኛው በቁም እያለ ህጻናቱ የእኔ ነው የእኔ ብለው እጣ የተጣጣሉበት፣ ደግሞ ከታረደ በኋላ ሰባ አልሰባ የሚባልለት፣ ከታረደ በኋላ የተመገበው ሳር ዓይነት እና የመጣበት ቦታ ሳይቀር እየተጣጣመ የሚተረክለት፣ በግ። ቀዥቃዣ ባህርይው ከእድገቱ ጋ ተዳምሮ የሚወሳለት ፍየል።
 
በየቅያሱ የተገዛላቸውን አልባሳት በኩራት እያወሩ በደስታ አፕዴት የሚደራረጉ፣ ኮሜንት የሚሰጣጡ፣ ላይክ የሚገጫጩ ህጻናት (አንዳንዶቹም ለናሙና ለብሰው የሚወጡ)፣ ያገኙትን በጊጩ እና ወጋሁ አጀባ ሼር የሚደራረቁ ንጽሀን፥ ለዓመት በዓል ብቻ ከፊት የሚጸዳ ንፍጥ ያለባቸው ህጻናት፣ ፊታቸው እንደ እርጥብ መሬት ሙትክ ሙትክ የሚል እንኳን ንፍጥ ሊታይባቸው ሲያስብ ተሯሩጦ አናፋጭ ያላቸው ብርቱካን መሳይ ፊቶች፥ ግን ደግሞ ዝርክርኩም ንጽሁሁም እኩል የሚያምሩ ህጻናት፥ ሁሉም የሚያወጡት ልዩ የበዓል መልክ አለ።
 
የበዓሉን ዋና ቀንበር የሚሸከሙት፣ እረፍት የሚናፍቃቸው፣ ኋላ እግሩን ዘርግቶ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሚቀያይር ወጠምሻ “አሳረርሽው” “ቅባት ሞጀርሽበት” “ጨው አሳነስሽው” “አላበሰልሽው” የሚል ወቀሳ ሁሉ ሊደርሳቸው የሚችል፣ ቤቱ ሙሉ መሆኑን የሚያረጋግጡት ሴቶች።
 
በዓል ደርሶባቸው ልጆቻቸው ከሰው እንዳያንሱ የሚሳቀቁ ወላጆች ከርታታ ዐይን፥ ቢያምም የራሱ መልክ አለው። ለበዓል በተለየ መልኩ የተፈታ፥ ሀምሳ ሳንቲም ከመስጠት አስር ብር ወደ መስጠት የተሸጋገረ ለጋስ እጅ። ያለውን ቤት ያፈራውን አጥፎ ለጎረቤቱ የሚያቃምስ ደግ። የለው እንዳይባል ለዓመል ሰርቶ፣ አለው እንዳይባልና በደግነት እንዳይሰጥ ያለውም አንስቶበት በፀፀት አንጀቱን የሚበላው ምስኪን።
 
ጥርስ ውስጥ ስጋ ገብታ ሰላም ነስታ ስታስጨንቅ ጊዜ ከመሬት አንስተዋት ሰላም ያገኙባት የስንደዶ ስንጣሪ እንኳን እንደ ትልቅ ቁም ነገር ከነመልኳ እና ሁኔታዋ በዐይን ትዞራለች።
 
ሁሉም ይናፍቃል።
 
የትም ቢሄዱ፣ እንዴትም ባለ ስሜት ውስጥ ቢሆኑ፥ በዓል ጠረኑን አያጣም።
 
የመርካቶን ደጃፍ ካልረገጡ ግን አይሞላም!
 
በሽንኩርት ተራ ተሽሎክሉከው፣ ሳህን ተራ ጎራ ብለው ዱኙን፣ ቀበሪቾውን፣ ሀደሱን፣ ቀስሉን፣ እጣኑን፣ ከርቤውን፣ ጭሳጭሱን በያይነቱ ዘረጋግተው የሚሸጡት እናቶች ጠረን ካልታከለበት ይጎላል።
 
በበርበሬ በረንዳ በኩል አልፈው አንድ ሁለቴ ካላነጠሱ ምኑን በዓል ሆነ? ሰባተኛ ወርደው ቀጤማውን፣ ጠጅሳሩን፣ አሪቲውን እጅ ካልነሱ ምኑን ደመቀ?
 
ክንዴ ቡቲክ፣ እልል በል ሀበሻ፣ አላየሁም አልሰማሁም እንዳትል፥ ለየት ያለ የበዓል ቅላጼውን ካልለቀቀ ምኑን ዋዜማ ሆነ?
 
ታታሪው በያይነቱ፣ ፌሽታው በየቤቱ ነው። ሁሉም በያይነቱ ይሸጣል። መርካቶ የሰው ሰፈር!
 
ግን የባሰም አለ።
 
የሰው አገር በዓል፥ ሁሉም ያለው፣ ሁሉም የጎደለው።
 
ቀጤማው ባይጎዘጎዝም፣ ጠጅ ሳር እና ሀደስ ባይሸቱም፣ ከሴው ከአየሩ ጋ በድሪያ ስሜት መጥቀው እኛንም ባያሳብዱን የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል አይቋረጥም።
 
የአዲስ አባ ውሃ ያልነካው ከሰው ያልጠጡት ቡና ቡና ባይሆንም፣ እንዳቅሙ ኤክስፖርት ስታንዳርዱ ተመርጦ ፣ እንደነገሩ እጣኑም አብሮት ቢነግስም፣ ተቆልቶ በአፍንጫ ተምጎ፣ ይፈላል።
 
በጉ ደጃፍ ታስሮ ለሁለት ለሶስት ቀን ድምጹን እያሰማ፣ ሲወጡ ሲገቡ በዐይን እየቃኙት፣ ሳር ውሃውን ባይቀርቡለትም፥ ከቦታው ታርዶ ተበልቶ ይመጣል።
 
ቅርጫ ገብተው፣ ከብት አማርጠው አራጅ ጠርተው ከነሙሉ ክብሩ እና ማዕረጉ ባይከፋፈሉትም ስጋውም ከኪሎ እስከንቅል አለ።
 
አተላው ይደፋ፣ አምቡላው ይጣል ባይባልም፥ ጠጁም ጠላውም እንዳቂሚቲ አይጠፉም።
 
ካቴም በያይነቱ ተሞሽራ አለች።
 
ግን መንፈስ እና ጠረን ይርቁታል። ውሃ ውሃ ይላል።
 
ሞቅታውም በለሆሳስ ነው። እቃ እንደረሳ ሰው፣ በአሁን እነሳለሁ ዓይነት ዱቅ ብለው፣ በዜና እየበረዙ፣ በአገር ቤት ወቅታዊ ወሬ እያዋዙ ስለሚጠጡት አንጎል ጋ ሳይደርስ፣ ሆድ ሳያጠረቃ ይተናል።
 
እናት እናት የሚል ሽታ፣ አባት አባት የሚል ጠረን የለም። ዶሮ ዶሮ፣ ጓሮ ጓሮ የሚሰማ ቅያስ የለም። ሰክሮ የሚወላገድ የለም። ለድጋፍም ለበረከትም እጅ የሚዘረጉለት ምስኪን የለም።
አንዱም የሌለው፣ ምናልባት ስጋውን በፈረንጂ ካቴ የሚያወራርድ የባሰበትም ብዙ ነው።
 
ግን ምኑም ካለ ብዙ ሰው አይጣፍጥምና፣ የትም ሆኖ ሰው ያለው፣ ሁሉም ቦታ አለ!
ያለንን የምናካፍልበት፣ ከእኛ የባሱትን የምናስብበት በዓል ያድርግልን! ጌታችን መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ተወልዶ መከራውን ሁሉ እንደተቀበለ፣ እኛም እንዲሁ ሰውነትን አስቀድመን ወንድሜ እህቴ በመባባል ያኑረን!
 
መልካም በዓል ይሁንልን!

ናፈቀኝ… (ጂጂ)

“ናፈቀኝ… ደገኛው ቄስ ሞገስ፥ በፈረስ፣ በበቅሎ ተጉዞ ሲመጣ፥ 28574-2
ለዓመት በዓል ጨዋታ፥ ሰው እልል እያለ ሲቀበል በእምቢልታ፤
አንተዬ… በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፤ ያገሩ ገነኛ ሆ እያለ ሲመጣ፣
አባዬ ናፈቀኝ የከብቶቹ ጌታ፥ ሲባርክ ሲመርቅ የቤቱን ጨዋታ፤
እምዬ እናታለም….
ጉልበትሽ ችሎታሽ ይበልጣል ከሺህ ሰው፥
__ ይኸው ሰውን ሁሉ እጅሽ አጠገበው፤
ናፈቀኝ… ያያ ታዴ ሆዴ…
“የሽመል አጓራ አይችልም ገላዬ
የኔ ሆድ አሌዋ ና ቁም ከኋላዬ፤
አያና ድማሙ አያና ድማሙ
አያና ድማሙ አያና ድማሙ፤
ዓባይ ወዲያ ማዶ ትንሽ ግራር በቅላ
ልቤን ወሰደችው ከነሥሩ ነቅላ።”
እያለ ሲዘፍን ትዝታው ገደለኝ
ዛሬ በሰው ሀገር የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ
ወኻ ጃሪ ወኻ ኮሎ ሲሉ
ያባቴን በሬዎች የእናቴን መሰሉኝ፤”
~ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ❤
ውስጧ ሆኜ፥ ሀገሬን ከሩቅ ከማይባቸው ምርጥ ሙዚቃዎች አንዱ! …እንግዲህ ከሀገር የራቃችሁ ወዳጆች፥ ይህንን ሙዚቃ መዝዤ ናፍቆት ሳጋግልባችሁ፥ ጉዳችሁ 🙂
መልካም የገና በዓል!