ፈርኦናዊነት

Hailemariam-Desalegnሰው ከመጽሐፍ ቢቀር ከእድሜው፣ ከእድሜው ቢቀር ከወዳጆቹ/ጎረቤቶቹ፣ ከነሱ ቢቀር አለትን ወደ አፈር በሚለውጠው ጊዜ፣ ከእርሱም ቢቀር ጨለማና ብርሃን ከሚፈራረቁበት የጠፈጥሮ ዑደት… እንዴት አይማርም?
 
በእኔ እምነት ይሄ ስርዓት እንኳን አሁንና ድሮም ያልፈረሰ፣ በከባድ ችግር ውስጥ እንኳን ገብቶ የማይፈርስ ስርዓት ነው። ስለዚህ በአለት ላይ የተመሰረተ ስርዓት አለን ብሎ ማመን ጠቃሚ ይሆናል። ….በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ያለምህረት ህግ የማስከበር ስራችንን ማከናወን የሚገባን ይሆናል። መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሁሉንም አቅሙን ይጠቀማል። በእኔ በኩል ይህ የህግ የበላይነት እንዲከበር ለማድረግ ሁሉም የጸጥታ አካሎቻችን ህግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ።
ብሏል (ጠ/ሚ?) ኃይለማርያም ደሳለኝ
እንግዲህ ትዕዛዝ ማንበብ ነበርና ስልጣኑ’አለሁ’ ለማለት ጊዜ ተራው ደርሶት መሆኑ ነው ሕዝብ ለመፍጀት ትዕዛዝ ያስተላለፈው፡፡ ይሄ መቼም የሚረሳ ጉዳይ አይደለም!
 
ቃል በቃል ገልብጬው ደጋግሜ አነበብኩት። ደጋግሜ ነፈርኩኝ። የሰው ልጅ አእምሮ እንዴት በዚህ ደረጃ ሊደነዝዝ ይችላል? መቼስ ያደገ አገር ሰዎች ብንሆን እንዲህ ያለውን ሰው ሰብስበው ጥናት መከናወኑ አይቀርም ነበር።
 
“ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” ነበር ተረቱ። “ፀጉራም ውሻ ሞቶም ሲታይ ጣረ ሞቱ ‘አለሁ’ ይላል” እንበለው ይሆን?!
.
.
ሰውዬው በሀይማኖተኛ ማሊያም እንደሚጫወት ትዝ ቢለን፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ የፈርኦንን ታሪክ እናስታውሳለን….
 
“እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ።” (ኦሪት ዘጸአት 7፥ 13-14) “ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ።” (ኦሪት ዘጸአት 14፥23)
 
“የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው። የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል።” (ትንቢተ ሕዝቅኤል 32፥2
 
“የመለስ መንፈስ ከኃይለማርያም ላይ ልቀቅ!” የምንልበት ጊዜ አልፏል። አሁን መንፈሱ ሙሉ ለሙሉ እንደተዋሃደው እያየን ነው። …እንግዲህ ሙሾ እያሞሸን ፍትህ ሲፈጸም የምናይበት ቀን ይመጣል! የሰው ልጅ ደም እንደው በከንቱ ፈሶ አይቀርም!
 
“ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና!” (መዝሙረ ዳዊት 136፥15)
 

ሀገሬን ከነኗሪዎቿ…

13925175_1450435844972892_1002811786806231956_nበስፖርቱም ሆነ በሌላው ጉዳይ አገሬን ከነኗሪዎቿ እንደ ሮቤል ኪሮስ ያስተዋወቀልኝ የለም። እንደሱ፥ በደልና ግፉን ሁሉ ባንድ ላይ ሸክፎ ለዓለም ያሳየልኝ የለም። ሙስናውን፣ ውጥንቅጡን፣ የወጣቱን ጉስቁልናና መገፋት፣ የስራ ማጣቱን፣ ሞያ ማቃለሉን፣ የሆድ ስፋቱን፣ የፖለቲካና የዘር መድልዎውን፣ የኑሮ ልዩነቱን (‘ሰላም ውሎ መግባት’ን ካለማወቅና ‘የጠሉትን የመቃወምን ዋጋ’ ካለመተመን፣ እስከ ‘የፈለጉትን ልዩ ነገር መሞከር’ መቻል ድረስ)… “መተዋወቅ” ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ መጭበርበር ደርሶባታል። ሀቀኛ ኗሪዎቿም ተበድለዋል።
 
ከትናንት በስቲያ ግን በሮቤል ቀፈት በኩል ሁሉም ነገር ታየ። በእርሱ ከአቅም በታች በሆነ ችሎታ ኦሎምፒክ ላይ መሳተፍ ሁሉም ነገር ፍጥጥ ብሎ ተነገረ። ሮቤልም አባቱም ያውቃሉ ብዙ ችሎታ እያላቸው ቤት የቀሩ ድንቅ ዋናተኞች እንዳሉ… ሌላ ሰው ተወክሎ ቢወዳደር የማሸነፍ እድል እንደነበረን… የሰውነት አቋሙን ዝርክርክነት (ፎቶው ላይ ወላ ተሰብስቦ ነው)… በምን መስፈርት እንደተመለመለና ባንዲራ ተሸካሚ እንደሆነ… እንዲህ ያሉ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ አገርን ለመወከል ቀርቶ ለተራ የቀበሌ ሥራ፣ ሚኒማውን ማሟላት ማለት ዝምድና ወይም የፖለቲካ ትስስር መፍጠር ማለት እንደሆነ… ሌሎችም ብዙ ባለጊዜያት ያውቃሉ። ግን በቃ ሮቤል መሞከር የሚፈልገውን ነገር እንዲሞክርና “ለየት” ማለት እንዲችል፥ የአገሪቷን መስፈርት ያሟላል። እንደአባትና ልጅ ሊያሳፍር የሚገባ ጉዳይ ሳይቀር፥ እንደባለጊዜ ሲታይ አእምሮን ይደፍንና ያኮራል።
 
ከነኅሊና ከሆኑ ምን እውቀትና ጉጉት ቢሰንቁ፣ ሰተት አድርጎ የማያስገባውን የሥራና የሞያ ዓለም አሳየልኝ። በየትኛውም ዘርፍ፣ ሰው ምን ያህል ያሸበረቀ ሲቪ ቢኖረው፥ በልኩ የተሰራ ስራ ላይ ተወዳድሮ አገሩን ማገልገል ቀላል እንደማይሆንለት… በአንጻሩ፥ የሚፈለገውን ሞያዊ አቋም ያላሟላ ቦርጫም፥ ላዩ ላይ ተጣብቆ በሚያስጨንቀውም ሆነ፣ ሰፍቶት በሚወላለቅበት፥ የስራ ዓለም ላይ ገብቶ አገሩ ላይ መገልገልና ሕዝቧን መበደል መቻሉን አሳየልኝ። የራበውና ቤተሰብ ማስተዳደር ያለበት ሰው ህሊናውን ሸጦ፣ የማያምንበትን ሀሳብ እያራመደ ዳቦ ይገዛ ዘንድ የሚያስገድደውን የተጨማለቀ ሲስተም ፍንትው አደረገልኝ።
 
የተማሩና አገር ውስጥ መስራት ያልቻሉ ብዙ ሰዎች ለስደት ወጥተው በየበረሀው ቀርተዋል። የቀናቸውም በየሰው አገሩ ተበትነዋል። እንኳን የማይችሉትን ልዩ ነገር ለመሞከር ቀርቶ፣ የሚችሉትን ልዩ ነገር መስራት እንዳይችሉ በሀሳብ ልዩነታቸውና በፖለቲካ ተሳትፎአቸው የተነሳ ከየእስር ቤቱ ፍርግርግ ጀርባ የተወረወሩም ሞልተዋል። መንግስትን የሚቃወም መፈክር ያዛችሁ ተብለው ከዩኒቨርስቲ ትምህርት ገበታቸው ሳይቀር ተፈናቅለው ጥቃት የተፈጸመባቸውም አሉ። በየጎዳናው ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው በግፍ ደማቸው የሚንዠቀዠቅ ወጣቶችም አይቆጠሩም። በአንጻሩ ደግሞ፥ የፖለቲካ ታማኝነትንና ዝምድናን ተገን አድርገው፥ ሳያንኳኩ፣ በተኙበት በሮች ተከፍተውላቸው ከቤት የሚጠሩ ቦርጫሞች አሉ። ይኼን ይኼን ሁሉ ሮቤል አሳየልኝ።
 
በአትሌቲክሱ እንኳን ብንመለከት፥ ብዙ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ለሌላ አገር ባንዲራ እየሮጡ ነው። ከአገር ቤት የሚገፉት፥ እንዲህ እንደሮቤልና አባቱ ያሉ የኅሊና ቦርጫሞች እየተመረጡባቸው ነው። ይህኔ፥ እሱ ቀፈቱን ለዓለም ባሳየበት ቅጽበት ቅስማቸው ተሰብሮ የስደት በርን ያማተሩ ብዙ ዋናተኞች ይኖራሉ። በሌላውም ዘርፍ እንዲሁ። ….እንጦጦ ሄደሽ ብትወድቂ ብትነሺ፣ አገር እቅፉን በሚደንቅ ብቃት ብትሮጪ፥ አትሌቲክስ ማኅበሩ ዙሪያ ዘመድ ከሌለሽ ማንም አያይሽም። ብለሽ ብለሽ ሲመርሽ፥ እዚያ ለሚሮጡት ጀላቲና ቀዝቃዛ ውሀ በመሸጥ ራስሽን ለማስተዳደር ትሞክሪ ይሆናል። …ይኼን ይኼን ሁሉ ብዙ ሳያወራ አሳየልኝ።
 
ሮቤል አገራችንን በዋና ለመወከል ወጥቶ፥ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ወክሎን ለዓለም አሳይቶልናል፣ እዚሁ እያለንም ለተጋረደብን ሰዎች ነገሮችን ገላልጦልናልና፥ ከእርሱ ይልቅ ፈልቅቆ ባሳየን አገር ላይ ዐይናችንን እንጣል።
 
የእርሱ ቦርጩን ማዝረክረክ የማሳፈሩን ያህል፣ የብዙ ቀልዶች መፈጠር ምክንያት ቢሆንም፥ እሱ እሱ እንዳያዘናጋንና መብታችንን ከመጠየቅ (ቢያንስ መበደላችንን በቅጡ ከመገንዘብ) እንዳያዘናጋን።
 
#Ethiopia #StopKillingCivilians