‘ከስሜት ባሻገር’

ቅዱስ ላሊበላ፥ ከአንድ ወጥ ድንጋይ፣ መሰረቱ ከጣራው የተጣለ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በሚያስደንቅና የሰው ልጅ ሊያስበው በማይችለው ጥበብ አንጾ አበረከተልን። ዓለም ዛሬም ድረስ በኪነ ህንጻው ይደመማል። ያየው ሰው ሁሉ ይደነቃል። “ላሊበላና ሞት ሁልጊዜ አዲስ ነው” እስኪባል ድረስ በታየ ቁጥር አዲስ ነው።

ምን ያህል የተጻፈ ቢነበብ፣ የተቀረጸ ቪዲዮ ቢታይ፣ ነገር አዋቂ ሰው ሲተርክ ቢሰማ፥ ደርሰው ሲያዩት ስሜቱ ከቃላት በላይ ነው። ልክ ልጅ መውለድን በሉት። (በዚሁ አጋጣሚ ያላያችሁት እዩት።) የራስን ልጅ ወልደው እስኪያቅፉ ድረስ፥ ምን ለልጅ ቢንሰፈሰፉ፣ የስሜቱን ከፍታ ያውቁት ዘንድ ከባድ ይመስለኛል። እንዲህ ያለውን ድንቅ ነገር ላሊበላ አበረከተልን።

እኛ ደግሞ፥ ለላሊበላ አድናቆት ይሁን ተብሎ፣ እጅግ በረቀቀ ቋንቋና ምስክርነት ከተጻፈ ወስዋሽና ቀስቃሽ ውዳሴ ጽሁፍ ውስጥ “አዳራሽ” የሚል ቃል መዘን፥ የነገርንና የክርክርን ድንጋይ ስንፈለፍልና፣ ጥላቻንና ፍረጃን ስናንጽ እንውላለን። ውዳሴ አጻጻፉ ላይ ስህተት ቢኖር እንኳን፥ ስለብዙው ጥሩ ነገር አድንቀን መጀመር እንችል ነበር። (በጣም የደነቀኝ ደግሞ፥ ላሊበላን አይቶት የማያውቅ ሰው ሁሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጥ ነበር።)

ላሊበላ አካባቢ የነበሩት ድንጋያት ወደ ድንቅ አብያተ ክርስቲያናት ሲፈለፈሉ፥ በሌላ ቦታ ድንጋይ አልነበረም ማለት አይደለም። ቅዱስ ላሊበላ ድንጋያቱን ለህንጻ ቤተክርስቲያን አልሞ፣ ጥበብን ከፈጣሪ ጠይቆ ሲያገኝና ሀሳቡን ሲያሳካ፣ ሌሎች ድንጋያት ግን ለሌሎች ተግባራት ውለው ነው። ልክ እንደዚሁ፥ ነገርን ሁሉ በበጎም በጠማማም መልኩ መመልከት ሊፈጠር ይችላል።

ፋሲካን ለመብላት ቦታ እንዲያሰናዱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሲልካቸው “ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ?” ሲሉት፥ “እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ።” እንዳላቸው በመጽሐፍ ተነግሮናል። (የሉቃስ ወንጌል 22: 1-12; የማርቆስ ወንጌል 14:1-15) በመዝሙረ ዳዊት 47: 12 -13ም “ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፣ በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ አዳራሽዋን አስቡ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ።” ተብሎ ተጽፏል።

ከዚህ የምንረዳው፥ “አዳራሽ” የሚለው ቃል፣ ሆን ተብሎ የተጣመመ አገባብ እንደሌለው ነው። መዝገበ ቃላት ብናገላብጥም፥ “አዳራሽ ማለት ታላቅ ቤት፣ ብዙ ሰው የሚያገባ፣ ይኸውም ክብ፣ ሰቀልኛ ነው።” ወይም “ወደ ታሰበበት ነገርና፣ ጉዳይ የሚያደርስና የሚያገናኝ አድራሽ፣ አቃራቢ።” ተብሎ ይተረጎማል። ለእኛ ግን፥ ለላሊበላ አድናቆት “ኢአማኒ ነኝ” ባለ ሰው በተጻፈ ጽሁፍ የተነሳ ቃል መዘን ለክርክር እናውለዋለን።

ቁጣ፣ ክርክር፣ ተሳዳቢነት፣ ዛቻና ፌዘኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱም ጋር በአዎንታዊ መልኩ አልተጻፈም። እንዲህም አልተማርንም። ሆኖም ግን፥ የምናምነው አምላክ የማይወደውን ነገር ተጠቅመን፥ በሀይልና በማንኳሰስ፣ በትምክህትና በመመጻደቅ የእርሱን ቤት እንዳስከበርን እናስባለን። ነገር ግን “ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።” (የሉቃስ ወንጌል 5፥32) ተብሎ ተነግሮናልና እግዚአብሔር ማንን መቼ፣ እንዴት እንደሚጠራ ስለማናውቅ፥ “ኢአማኒ ነኝ” ላለ ሰው የማርያም መንገድ በሚከለክል መልኩ ሆ ብለን እንነሳለን። ከዚህም ባሻገር “እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።” (የሉቃስ ወንጌል 15፥7) ተብሎም ተነግሮናልና ኢአማኒ ሰው ንስሐ ሊገቡ ከሚችሉ ሰዎች መደብ ነውና፥ ከጻድቃን ይልቅ በእርሱ መጠራት በሰማይ ደስታ ይሆናል።

የሆነው ሆኖ፥ ይሄ ሁሉ ሲሆንስ ምን ላይ ቆመን ነው ሌላውን ሰው የምንዘልፈው? እኛ “አማኝ” መስለንና በስሙ ክርስቲያን ተብለን በጓዳም ባደባባይም ስንት ዓይነት ጽድቅ ሰርተን ጣታችንን ለመጠቆምና ድንጋይ ለማንሳት እንረባረባለን?

“ነኝ እንዳልል፥

የት ቆሜ መሆኔን አየሁ” እንዳለው ነው ጋሽ ሰለሞን ደሬሳ።

“አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” (1ኛ ቆሮንቶስ 10:12) ተብሎም ተነግረናልና ሁሉም ነገር እንደ እኛ ሳይሆን እንደቸርነቱ ይፈጸምልን ዘንድ እንማጸናለን።

————

ትናንት በዕውቀቱ ስዩም ላንዲት ሴትዮ አስተያየት ለጥፎ የነበረው ምላሽ ላይ “Don’t waste your time with explanations: people only hear what they want to hear.” የሚለውን የPaulo Coelho ንግግር አስተያየት መስጫው ላይ አስፍሬ ነበር። (አስተያየታቸውንም አንብቤው፥ ቁጣውና ተግሳጹ እንዲሁም ነገር ፈልፋይነቱንና የማጋጨት ፍላጎታቸውን ብቻ ነበር ለማየት የታደልኩት።) በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እርስ በርስ ማብራሪያ መሰጣጠትና መማማር እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ነው ይህን ሁሉ መዘብዘቤ።

የሆነው ሆኖ ሰው መርጦ ማንበብና መርጦ መረዳት ይችላል። መፍረድና መወገን ግን በፍላጎት እና በስሜት ብቻ የሚወሰን አይመስለኝም።

ሰላም!

 

አሜንታ! – ለ“ከአሜን ባሻገር”

12509614_10153897229492065_997488513348132261_n“ያንዘፈዝፈኛል፥ ብርቱ ዛር አለብኝ!”

በከፋ የዘረኝነት ብርድ ልብስ ተጀቡነን፤ ሰዎችን በመጨቆን ጋቢ ተሸፋፍነን፤ ቅጥ ባጣ ንፍገት እና ስስት ተጋርደን፣ ሆነ ብሎ ተንኮልን በመሸረብ፣ ሴራ በመጎንጎን እና እውነትን በማጣመም አባዜ ውስጥ መሽገን፤ በወሰን የለሽ ስግብግብነት እና ጥቅመኝነት ታዛ ውስጥ ተሸሽገን፤ ኅብረተሰብን በማጫረስ ኩታ ተከናንበን የምናነበው ከሆነ፥ እርግጥ ነው፥ “ከአሜን ባሻገር” ክፉኛ ብርድ ያስመታናል። በመጽሐፍ አምሳል ተጠግቶን ከቀሰፈን፥ ከእውነት ጋር አላታሚ፣ ከ’አይነኬ’ ርዕሶች ጋር ተፋላሚ፣ እና አፍራሽና አቆርቋዥ ሀሳቦችን ቆልማሚ፥ ብርድ ለማገገም እና ወደ ዘላቂ ሙቀት ለመሸጋገርም የራሳችን ቅንነት እና ፍላጎት ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ምናልባት “አውቃለሁ” ብለው (አዋቂ መስለው) ከተደላደሉበት ቦታ ሁነው ሲመለከቱትና ራስን ሲያዩበት “የምታውቁት ልክ አይደለም።”፣ “ተጨናብራችሁ ስታጨናብሩ ነበር” አልያም “አታውቁም” መባልን መቀበል ከባድ ቢሆንም፥ “አለማወቁን ማወቅም” ለእውቀት ያበጃጃልና፥ ካወቁበት የአዋቂነት ማማው ይሆናል። ከጥፋት ጋር አብረው፣ እውነትን በማድበስበስ፣ በፍረጃ እና በዘረኝነት መንፈስ አድፍጠው ‘ሲሸቅቡ እና ሲቀረቅቡ’ ላሉ ሰዎችም ድንጋጤው ቢያስለፈልፍ፥ ሰውኛ ነው። የተበረዙትን መጽሐፍት በማጣቀሻነት ተጠቅመው መጽሐፍ እያሰናዱ ላሉ ሰዎች እና፣ የብሔር እና የጥላቻ ፖለቲካ በማቀንቀን (እና ለማቀንቀን ወጥነው) ፕሮጀክቶች እየነደፉና፣ ለማስፈጸም እየለፉ ላሉ ሰዎች፥ ከአሜን ባሻገር ‘things fall apart’ የሚያሰኝ ዱብ እዳ ቢሆንም አያስደንቅም።

(ቅቤ ከሙዝ ደባልቆ የሚሸጥ ሰው ሸፍጡ ሲታወቅበት እንደ ሀቀኛ ሁሉ ለማሳመን ላይ ታች ማለቱ አይቀርም። ከሳሾቹ በሸር እና በተንኮል ተነሳስተው ያደረጉት እንደሆነ ይተነትናል። – መተዳደሪያው ነውና፥ ይጠበቃል። እስኪጋለጥ ድረስ የተጋረደበት መጋረጃ መተርተሩ ነውና፥ ሀፍረቱን ለመከለል ቢፍጨረጨርም እንግዳ ነገር አይሆንም። …ልክ እንደዚያው ሁሉ፥ ከሙዝ ጋር የተደባለቀውን ቅቤ አምኖ ገዝቶ፣ ቀምሞ እያነጠረ ሲያጣጥም የነበረ ሰው እውነቱን ሲረዳ ቢደነግጥም፥ በደንበኝነት ዘመኑ በሆዱ ውስጥ ስላስተላለፈው ባዕድ ነገር ድብልቅ ቅቤ ሲል፥ ሊሟገት ይችላል። – ርካሽ መብላቱ አማራጭ ማጣቱን አልያም ድህነቱን ያሳብቁበታልና፥ ለጊዜው ቢሟገት አይፈረድበትም። እውነቱን ስለሸሸው የቀረለት ቢመስለውም፥ መጽናኛው ነው።)

Don’t waste your time with explanations:
people only hear what they want to hear
– Paulo Coelho

መጽሐፉ የቆምንበትን መሰረት እንድንፈትሽና እውቀቶቻችንን እንድንመዝን መንገድ ከማመላከት፣ የዘመን ቁስላችንን ከመመዝመዝና ጥቀርሻዎቻችን እንድንፈቀፍቅ ከመጠቆም፣ እንዲሁም ወደ ንጽህና ለማቀራረብ መንገድ ከመጥረግ ባለፈ አዋራ የሚያስጨስ ይዘት የለውም። ካስጨሰም፥ ወይ አዋራውን እያወቁ ሲቆልሉ በኖሩት፣ አልያም የአዋራው ቁልል ስር ምሽግ ሰርተው የምቾት ቀጠናቸውን በዘረጉ ተጠቂዎች (victims) ዘንድ ነው።

ሲጀመር “ከአሜን ባሻገር” በወገንተኝነት አልተጻፈም። “በወገንተኝነት ነው የተጻፈው” ቢባል፥ ውገናው ከእውነት እና ከእውቀት ጋር መሆኑን ለመገንዘብ መጽሐፉን በንጹህ ልቡና መጀመር በቂ ነው። …በእርግጥ ይከብዳል፥ ከከተሙበት ብርድ ልብስ ውስጥ እንደ ዋዛ ሲነካኩ እና፥ አዋራ ሲጠጣ የኖረ ታሪክ ተቆስቁሶ “ይጽዳ” ሲባል። ያም ይመስለኛል ብዙዎችን ጭራሽ ስላላነበቡት (ወይም በቅንነት ስላላነበቡት) መጽሐፍ በተቃዋሚነት እያስሟገታቸው ያለው። “አንብበውት ነው” ቢባል ደግሞ፥ መጽሐፉ ላይ ለተጻፉ ሀሳቦች ደጋፊነት ጥሩ ምስክር ሆነው መቅረብ የሚችሉ ናቸው።

ፀሐፊው ማስረጃዎችን እያጣቀሰ ሲያስረዳ ካልተዋጠልን ችግሩ ከጉሮሮ ወይም ከትምክህት ነው። አሁን መጽሐፉን አንብበው ፀሐፊውን ‘ጠላት’ ብለው ለመፈረጅ የሚሯሯጡ ሰዎች፥ ቀድሞም ቢሆን አውቀው ሸሽተውት እና ለማጥፋት ደክመው እንጂ፥ እውነቱን ያውቁት ነበር ማለት ነው። – ይሄ ይበልጥ ያስተዛዝባል! ሰው እውነትን ማወቅ ካልፈለገ የተጻፈውን አያናበውም። ቢያነበውም እንዳልተጻፈው አድርጎ ነው የሚረዳውና የሚያስረዳው። (ከሩሲያዊው አሌክሳንደር ቡላቶቪች ፅሁፍ ‘annihilation’ ተብሎ የተተረጎመውን፥ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ ‘massacre’ ብለው እንደጻፉት መገለጡን ያስታውሷል።)

ባለማወቅ፣ በለብለብ እውቀት በመቀባባት፣ በጥራዝ ነጠቃ በመነከር፣ ባለመፈለግ እና ወገን ላይ ተንኮል በመሸረብ፥ ተጠምደን ስንዳክር ለኖርን፣ እና በቅንነትም ይሁን በጥቅም ኀሳሽነት፥ በግልም ይሁን በቡድን፥ ለአገራዊ ለውጦች አራማጅነት (activism) እና የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪነት፥ ላይ ተሰማርተናል ብለን ለምናስብ ሰዎች “ከአሜን ባሻገር” መንገዳችንን በመጥረግ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

በእውቀቱ ሀሳቡን ሲያሰናስል፣ ማንሳት ወደፈለጋቸው ጉዳዮች ነገሩን ሲያቀናብር፣ ሀሳቡን ሲያንሸራሽር እና ተረኩን ሲያደራጅ፥ እንደነ ተስፋዬ ገብረአብ በገጸባህርያት ልሳን ተቀንብቦ፣ አልያም እንደአንዳንድ የታሪክ ፀሐፊያን ትርጉም እያፋለሰ፣ ባድርባይነት መረጃን እየሸሸገ፣ እና “እንደተባለው ሳይሆን እንደፈለገው” እየተረዳና እየገለበጠ ሳይሆን መጽሐፍትን በማገላበጥ፣ ዶሴዎችን በመመርመር፣ ሰነድ በማመሳከር እና መረጃዎችን በማጠናቀር ነው። በዚህ ሂደቱ ንባብ እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽኦ ለማድረግ ከመርዳቱም ባሻገር፥ ሰው “ሆዴን ሆዴን” እና “ልታይ ልታይ” በሚልበት ጊዜ፣ ከእውነት ጋር ወገን በመሆን የኅሊና ልዕልናውን የሚያሳይ ነገር ነው።

የእውነት እና የእውቀት ቀበኝነት?

በእውቀቱ እንዲህ ተጨንቆ መጽሐፍ ሲያሰናዳ፥ ከሰው ጋር የመቀራረቢያው አቋራጩ መንገድ ጠፍቶትም አይሆንም። ድፍን ሀበሻ እንዲወደው ቢፈልግ እንዴት ማድረግ እንዳለበት የሚጠፋው ዓይነት ሰው አይደለም። “አይ ተወዳጅነቴ ዓለማቀፍ ይሁንልኝ” ብሎ ቢነሳም በውጭ ቋንቋ ሊራቀቅም ይችል ነበር። ሲሻው በግጥም ሲሻው በስድ ጽሁፍ የሚቀኝ የዘመን እንቁነቱን በአንድ ድምጽ የምንመሰክርለት የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።

ሆኖም መቀራረብ ያሳሰበው ከእውነት እና ከሰው ልጆች ጋር ነው። ያ ዋጋ ያስከፍላል። ሀቅ ለተናጋሪው ዋጋ የማስከፈሉን ያህል ለአድማጩም የሚያንቅ ነገር አያጣውም። ቢያንስ ከመንግስት ጋር ያላትማል። ይህንን ሀሳቡን ሲያጠናክርም “የግለሰቦች የወሲብ ገመና ብቸኛው ለእስር የማይዳርግ ርዕሰ ጉዳይ ነው።” ይለናል። ከእውነትና ከእውቀት ጋር የሚፋጠጥ ሰው በመንግስት ባይታሰር በጥቃቅን መንግስታዊ ባህርይ ባላቸው ሰዎች መታሰሩ አይቀርምና በየቦታው የምንሰማቸው የተቃውሞ ድምጾች የባለድምጾቹን ነውር የሚያጋልጥ ነው እንጂ እውነት ተናጋሪውን አይጎዳውም።

በተለይ፥ ታሪክን ከመሀል ለምንጀምር እና በአጤሬራ በተሟሸች እውቀታችን “ፖለቲካን ቋጥረን እንፈታለን፣ ታሪክን እንተነትናለን፣ ትልልቅ ሀሳቦችን እናወራርዳለን” ብለን ከነግትርነታችን አደባባይ ለምንወጣ እና “ካለእኔ ማን አለ” ለምንል ነውረኞች፥ “ከአሜን ባሻገር” ጥሩ መጽሐፍ ነው። አንድም “ነገርን ከስሩ፣ ውሀን ከጥሩ” እንዲሉ፥ ትልልቅ ጉዳዮችን እንዴት መያዝ እንደሚገባን ያስተምረናል። ሆነ ብለው ሲያለባብሱና ሲያሽሞነሙኑ፣ የሰዎችን ሰላም ለማደፍረስ ለሚባክኑ ሰዎችም ትምህርት አጭቋል። ቢያጡ ቢያጡ፥ የወጣቱን ጸሐፊ ብርታት እና ብሩህነት ያደንቃሉ።

“ወንጀል ቢጠፋ ፖሊስን ያሳስበዋል” የሚል ፍተላ ስንሰማ አድገናል። ሀኪምም እንዲሁ “የበሽታ መኖር የስራ ህልውናው ነው” ይባላል። ልክ እንደዛው ላንዳንድ ፀሐፊዎች እና ፖለቲከኞች፥ የዘር ጉዳይ እና የፍረጃ መኖር ጥሩ ግብአት ሆኗቸው የሚያኖራቸው ነውና የተሸሸጉበት ቀፎ ሲነካ አይወዱም። ከዚህ ባሻገር፥ እንደ ኅብረተሰብ ስንመዘን፣ መላመድ እና መመቻቸት የእውቀት እና የእውነት ቀበኛ እንዳደረገን ከምንረዳባቸው ጥሩ አጋጣሚዎች አንዱ የ”ከአሜን ባሻገር” መታተም ሆኗል። ዙሪያችንን እንድናበጥር፣ መጽሐፍትን እንድንመረምር፣ እና ውሏችንን እንድናድስ ጥሩ ዓይነት መስታወት ሆኖናል።

ለምን እውቀት እንደሚያስፈራን አይገባኝም። መሀይምነት የጨለማ ጉዞ ነው የሚል ጽሁፍ ባለበት የፊደል ገበታ ተምረን አልፈን ማንበብን ብናውቅም፣ ጥቅማችን እንዳይጎድል፣ ልማድ ሆኖብን ይሁን ብርሃኑን ፍርሃት እንጃ፥ በጨለማው ውስጥ መኖርን ሞያ አድርገን የያዝን እና የምንሰብክ እንበዛለን።

“ከአሜን ባሻገር” (በቅንነት ሲነበብ)

መሰረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው ቦታዎች ውስጥ በሚሊዮኖች ወጥቶ ስለሚገነቡ ሀውልቶች ፋይዳ እና መሰረት ይጠይቃል። በእነ “የቡርቃ ዝምታ” ንድፍነት (blue print) የተገነባውን የአኖሌ ሃውልት ያነቃንቃል። (በቅንነት የምር ቢወሰድ ሀውልት የማስፈረስም አቅም ያለው ነው።) ሐረር ከጨለንቆ ብዙ የሚርቅ ሆኖ ሳለ፥ ጨለንቆ ውስጥ መቆም ይገባው የነበረው “የጨለንቆ መታሰቢያ” ለምን በወረራው ወደ መስጊድ የተቀየረ የተባለው ቤተክስያን ደጃፍ ቆመ ብሎ በመጠየቅ፥ ምናልባት ለህብረተሰቡ የተዘጋጀ ወጥመድ ሊሆን እንደሚችል ስጋቱን ይገልጻል። ለጥቅምም ሆነ እውነቱን ባለማወቅ ጥላሸት ሊቀቡ የተደከመባቸውን ግለሰቦች እና መዋቅሮች በማስረጃ ታግዞ ሞግቷል።

የሃሳብ ነጻነት አፈናውን ፈርጀ ብዙነት፣ የአምባገነኑን ብዛት፣ የከያንያንን ወረተኛነትና ለማድነቅ ባህር ተሻጋሪነት አባዜ፣ የሃገርን ውበት፣ ስነ-ፆታ (gender)ን፣ ‘የጋዜጠኞችን’ ገመና ፈልፋይ ሆኖ መጠመድ፣ ህገ መንግስቱን እና ጸረ ሽብር ህጉን፣ የከሳሾችን ክፋት እና የንፍገት ልክ፣… መግቢያና መውጫው ላይ ደግሞ፥ ብዙዎች “ይሆናል” ብለው አስበውት የነበረው ሳቅ አጫሪ ሽሙጦችን እና የጉዞ እና የንባብ ትሩፋቶቹን ከመግቢያውና ከመውጫው አጭቋልና፥ ሁሉም የልክ የልኩን ይቆነጥር ዘንድ ማዕዱ ሰፊ ነው። ስለ እርቅ እና ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ላይ እንድናተኩር የሚያሳስብ መጽሐፍ ነው። በጅምላ እንደምንፈልገው ሳይሆን እንደሚያስፈልገን (በዋናነት መሆንም እንዳለበት፥ ራሱ እንደሚፈልገው) ሳይጽፍልን አልቀረም።

ኢአማኒነቱን አስረግጦ በተናገረበት ሁኔታ እንኳን፥ ከመጠየቅ እና ሲያመቸው ከመቀለድ ባለፈ፣ እንደብዙ ኢአማኒ (atheist) ነን ባዮች የሰውን እምነት አያጣጥልም። እንደውም በኢአማኒነቱ ውስጥም፥ “የእምነት ምልክት በሌለበት ቦታ መኖር ይሰለቻል” ይለናል። ስለእምነት እና ቤተ እምነቶች ትስስር ሲናገርና ቤተእመነቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ/ያደረሱ ሰዎችን ሲኮንን፥ “ቤተክርስቲያን ወይም መስጊድ ሲቃጠል የሚጎዳው እምነቱን አይደለም። እምነቱማ በምእመናን ልብ ውስጥ በእልክ ይበልጥ እየተንቀለቀለ ይኖራል። የእምነት ስርአቱ ጠላት ባልደረሰበት ሀገር ውስጥ በሚገኝ ቤተ-አምልኮ ውስጥ ይቀጥላል።” ይለናል። ታሪክን መሰረት አድርጎ ሲተነትንም፥ መሟገት ባለበት ቦታ የእምነት ተቋማትን ወግኗል። (እንደምሳሌ ለማንሳት፥ የአፈወርቅ ገብረየሱስን ታሪክ አውስቶ፥ “ቤትክስያንን ደግሞ የቀጣፊዎች ዋሻ ሆና እንድትታይ አድርጓታል።” በማለት ፀሐፊውን ይወቅሳል።)

“ከአሜን ባሻገር”፥ በአሜንታ የተቀበልናቸውና ተደጋግመው ስንሰማቸው እውነት የመሰሉንን ነገሮች በመወልወል ትክክለኛ ምስላቸውን ወደመከሰቱ ያቀራርበናል። እውነት የተጋረደችበትን መጋረጃ ይሰነጥቃል፣ ታሪክ አጣማሚነት የሰፈረበትን ምሽግ ይንዳል። ፀሐፊው “ዘመነ ዳፍንት” ላለው ዘመናችን እንደጥሩ ካሮት ነውና በቅንነት ከተቀሰመ ዐይንን አጠራርቶ ከእውነት ጋር ያፋጥጣል። መዋጥ ቢከብደንም ቅሉ፥ እውነት ቅርጿን ትለውጥ ዘንድ ከማባበል ይልቅ፣ ትምክህታችንን ስለመስበር እና ጉሮሯችንን ስለማስፋት ብናስብ እናተርፋለን።

ስንጠቀልለው

በዕውቀቱ ለስንፍናችን ቅጣት ነው። ለለብለብ እውቀታችንና ለ“አጤሬራ” ተመርኳዥ ሊቅነታችን ጥሩ ማገዶ ነው። የታሪክ ት/ት ክፍሎች፣ መጻህፍት እና የታሪክ ዳናዎች እየተፈቀፈቁ ባሉበት ሀገር ላይ፥ እንደበእውቀቱ ዓይነት ሰዎች ሊደነቁ የሚገባቸው፣ ወደ ሙላት የሚያቀራርቡን ሀብቶች ናቸው።

ለቧልት የጭን ገረድ፣
ላውቆ ድንቁር ገልቱ፥
ለዘረኞች ፈውስ ብርቱ መድኃኒቱ፥
ቁም ነገርን ያስስ፥ ይኑር በእውቀቱ!

እያልን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። 🙂

አሜን ብለናል በእውቄ!

እንወድሃለን!