“ከቤተሰቤ መካከል አማርኛ የምችል እኔ ብቻ ነኝ።
ሌሎች 13 ወንድምና እህቶቼ አማርኛን እንዳይሰሙም
እንዳይናገሩም አድርገን በጥሩ ሁኔታ አሳድገናቸዋል።
አሁን ያለዉ የቁቤ ትዉልድም ከሞላ ጎደል አማርኛን
የማይናገር የማይሰማ ጀግና ትዉልድ ሆኗል።”
~ ፕ/ር ህዝቅኤል ጋቢሳ (በOMN)
“ቋንቋን በአግባቡ ያለመጠቀም የኦሮሞ ሕዝብ ተገቢ የመብት ጥያቄዎችን ለሌሎች እንዳያስረዳ እንቅፋት ከሆኑበት ነገሮች አንዱ ይመስለኛል፡፡ በ1983ቱ የሽግግር ጉባዔ ላይ እነ ኦቦ ሌንጮ ለታ ለየት ለማት በአስተርጓሚ ለመናገር ሲሞክሩ፣ አቶ መለስ በመንዝአማርኛ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲፈልጥና ቆርጦ ሲቀጥል ነበር፡፡ ፓለቲካ ለሚያውቅና ለገባው ሰው፣ ኦሮሚፋ አንድ ቀን እንኳ በአደባባይ ይሰማልን የሚባል የአናሳ ቡድን ቋንቋ ሳይሆን ትልቁ የኢትዮጵያ ብሄር የሚናገረው ቋንቋ ነው፡፡ ሙዚየም ውስጥ ይቀርብኛል ተብሎ የሚሰጋለት ቋንቋ አይደለም፡፡ የቋንቋ ፖለቲካ የማይናቅ ባይሆንም፣ በተገቢው ጊዜና ቦታ ካልተጠቀሙ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡”
~ ፕ/ር መረራ ጉዲና – “የኢትዮጵያ ፓለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዲግ” ገፅ 225
ቋንቋ
መግባቢያ ነው። ክህሎት እንጂ እውቀት አይደለምና ባይችሉ አያሳፍርም። መቻሉም ቢያስደንቅና ቢጠቅም እንጂ፥ የተለየ ሆኖ የሚያስኮፍስ ነገር አይደለም። ሰው እንደዋለበትና እንደፈለገው ልክ የትኛውንም ቋንቋ ማወቅና በአግባቡ የመጠቀም ክህሎቱን ማሻሻል ይችላል። ብዙ ቋንቋ ባወቀ ቁጥር ግን የተሻለ መግባባት እና መፍትሄ ማምጣት ይችላል።
በተለይ፥ ቋንቋውን ሆነ ብሎ ላለመማር መጣርም ጉልበትና ጥረት ይጠይቃልና ራሱን የቻለ ድካም አለው። ማለዳ ማለዳ ተነስቶ፥ ልጆችን ስለጥላቻ መስበክ፣ እሱን ቋንቋ እንዳትናገሩ ብሎ መጨቆን፣ ጓደኞቻቸውን መምረጥ፣ ውሏቸው ላይ ጣልቃ መግባት… ሁሉ የመብት ጥሰቶች ሆነው ያስወቅሳሉ እንጂ፥ እንደጥሩ ገሪነት የሚያስደንቁ አይደሉም። ወላጅ/አሳዳጊ ከዚህ በላይ ሊበድልም አይችልም!
እኔ ኦሮሚኛ ለመማር ከምደክመው በላይ (አዲስ ቃል ብሰማ እና አፌ ውስጥ ቢገባ ለመጠቀም እደጋግመዋለሁ እንጂ ስለመርሳት አልጨነቅም) እነ ፕሮፌር እዝቅሔል ቤተሰብ ልጆቻቸው አማርኛ እንዳያውቁ የደከሙት ሲታሰብ ያስቆጫል። ልጆች ከሰው ጋር ተግባብተው እንዳይኖሩ መፍረድ ኅሊና ላለው ሰው ግፍ ነው።
በክልልስ እሺ፥ መንግስትም ለይስሙላ ፌደራሊዝሙ ሲል “በአፍ መፍቻ ቋንቋ አስተምራለሁ” ይላልና በዚያ ያልፋሉ። 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሲመጡ መግባባት ከባድ ይሆናል። ዩኒቨርስቲ ሲገቡም እንዲሁ ሆኖ ሰው ባያገል እንኳን ራስን ማሸሽም ይከሰታል። ሕብረተሰብ ካልተግባባ ደግሞ ግፈኞች ጥሩ ምሽግ ያገኛሉ።
ስለታሪክስ ቢሆን በአንድ ቋንቋ እና ወገን ብቻ የተነገረውን፣ እንደዶግማ ከመጋት፣ ብዙ ማስረጃዎች (resources) ያሉበትን ቋንቋ፥ “ላስተምር” ብሎ መጣር ቢቀር፣ “እንዳይማሩ” ብሎ መነሳት ክፋት እንጂ ሌላ ምን ምክንያት አለው?
በአሜሪካ…
ፕሮፌሰሩ እዝቅሔል ገቢሳ፣ ካለክልሉ አስጠግታው፣ ቤት ንብረት አፍርቶ፣ “ሰዎችን ከክልላችን ውጡ” እያለ እንደልቡ እየተከፈተ በሚኖርባት እና በሚያስተምርባት አገረ አሜሪካ…
ሰሞኑን የሜሪላንድ የጤና መድኅን ዋስትና ማዕከል፣ ለደንበኞቹ የላከው ደብዳቤ ላይ ወደ 17 የሚጠጉ ቋንቋዎች (Bassa የሚባል ስሙን ሰምቼው የማላውቀው እና፣ ‘Khmer’ እና ‘Laotian’ የሚባሉ ቋንቋዎች፥ ፊደሎቻቸው እርስበርስ ተያይዘው ሸረሪት ቀለም ነክታ ወረቀቱ ላይ የሄደችበት መስለው የሚያስቁ ሳይቀሩ ተካተው) ተጠቅሞ ያስተላለፈውን መረጃ ተመልክቼ ነበር። ከቋንቋዎቹ ውስጥ፥ አማርኛ እና ኦሮሚኛም ተካተውበታል።
በአማርኛ የተጻፈው….
“ያለምንም ክፍያ በራስዎ ቋንቋ እገዛ የማግኘት መብት አለዎት። ስለማመልከቻዎ ወይም ከጤና ዋስትና ድርጅቱ ስለሚያገኙት ሽፋን ማንኛውም ጥያቄዎች ካሉዎት፣ ወይም ይህ ማሳወቂያ በግልፅ በተጠቀሰ ቀን ማድረግ ያለብዎ ነገር እንዳለ የሚያስገድድዎ ከሆነ፣ በተጠቀሰው የስልክ ቁጥር ለስትቴትዎ ወይም ለክልልዎ ደውለው ከአስተርጓሚ ጋር ይነጋገሩ።” ይላል።
አሜሪካ ውስጥ፣ ከቆሻሻ መጣያ ቅርጫቶች አንስቶ በተለያዩ ቦታዎች፥ የአማርኛንም ሆነ ሌሎች ቋንቋዎችን ተጠቅመው ለመግባባት ሲጥሩ ይታያል። በሂደቱ፥ የሚያስቁ አጠቃቀሞችም አይጠፉም።
ከገጠሙኝ መሀል፣ በ’ዋሽንግተን ኤቲካል ሶሳይቲ’ አዳራሽ መጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ “Do not put paper towels in the toilets.” የሚለውን መልእክት በ5 የተለያዩ ቋንቋዎች ለማስተላለፍ ሙከራ ተደርጓል። በአማርኛ የተጻፈውን ስመለከተው፥ “ዶ ኖት ፑት ፓፐር ቶወልስ እን ቶእለፅ!” ይላል። 🙂
ስንት አለ ቶእለፅ ራስ አቦ!? …ሳይሾም የነገሰ፣ “እሟገትልሃለሁ” የሚለውን ኅብረተሰብ ሳያውቅ የሚንቧቸር የእንግዴ ልጅ!