
It depends on what we want!

ማንነት የእምነትና የመቀበል ጉዳይ ነውና “ነህ” ተብለህ፤ ጉራጌ ነኝ ካልክ ትሆናለህ። አማራ ነኝ ካልክም ትሆናለህ። ኦሮሞ ነኝ ብትልም ትሆናለህ። ትግሬ፣ ወላይታ፣… ሌላም የመረጥከውን ዘር ጠቅሰህ “ነኝ” ብትልም ትሆናለህ። የሆነው ሆኖ በጉራጌነትህ፣ በአማራነትህ፣ በኦሮሞነትህ፣ በትግሬነትህ… ለምትኖርባት ምድር፣ ምን የሚጠቅም ነገር ሰርተሀል? ያው ዘር ቆጥሮ ቂም በቀል መቆለል ነው?
ደግሞ ልቁጠር ልሰንጥቅ ካልክ፥ አማራንም ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ መንዝ ብለህ ልትከፋፍለው ትችላለህ። ጉራጌም ሶዶ፣ ሰባት ቤት፣ ሊባል ይችላል። ሰባት ቤቱም፥ ኧዣ፣ እነሞር…ሶዶውም ዶቢ፣ መስቃን፣ ክስታኔ… እየተባለ መውረድ ይችላል። ኦሮሞም ብትል፥ የወለጋ፣ የሸዋ እያልክ ልትዘረዝር ትችላለህ። ሌላውም ዘር እንዲሁ መተንተንና ለሽኩቻ መዋል ይችላል። መቅጠን ቀላል ነው። መጥበብ የመፈለግ ውጤት ነው። ግን ምን ስናስብ ነው ያንን የምናደርገው? ለምን እንፈልጋለን?
እቧደነዋለው፣ እዛመደዋለሁ የሚለውን ዘር ቆጥሮ ሌላውን ዘር ሲያንኳስስና ደረጃ ሲደለድል የሚውል ሰው ሌላ ትልቅ ቁም ነገር ቢቀር፥ እዛመወደዋለሁ፣ እቧደነዋለሁ ካለው መሬት ክልል ላይ አንዲት ችግኝ ተክሎ ያውቃል? እዚያ ሲደርስ፥ እጁ የያዘውን ቆሻሻ (የአፉን መርዝ ችላ ብንለው እንኳን) ሳይጥል ተመልሷል? ለአካባቢው ኅብረተሰባዊ መስተጋብር ተጨንቆ ሰዎች በሰላም እንዲኖሩና እርስ በርስ ከመነዛነዝ ይልቅ የተሻሉ ሀሳቦች ላይ እንዲያተኩሩ አግዟል?
በእርግጥ ዝምድና ያለና የሚኖር ነው። በአግባቡ ተቆጥሮ ሲውልም ቅመም ነው እንጂ መጥፎ ነገር የለውም። ሰው ቤተሰቡ እንደሚያኮራውና ስለቤተሰቡ እንደሚያወራው፣ ዘሩን ጠቅሶ፥ እኔ እንዲህ ነኝ ቢል ክፋት ላይኖረው ይችላል። የራስን ማውራት ግን የሌላውን ማንኳሰስን አይጠይቅም። በሌላው ዘር መንኳሰስ የሚጎላና ከፍ ከፍ የሚል ማንነት አለኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ግን ራሱን ቢፈትሽ የተሻለ ከፍ ከፍ ማለት የሚችል ይመስለኛል። በዚያ ላይ፥ የትና የት ጅምላ የጋራ ችግሮች ባሉን ሁኔታ ላይ በዘር መቸራቸር ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም።
ዘሮች ይለምልሙ!
ዘረኝነት ይድረቅ!