ለሰው ልጆች ሁሉ!

477907-hand-1355208385-980-640x480.jpgእኛ አገር “መቻል” ቀላል ስብከት ነው። ብዙ ጊዜ እንዲችሉ የሚጠበቅባቸው አቅመ ቢሶች እና ተጠቂዎች ናቸው እንጂ፥ አጥቂዎችና ባለጊዜ ጉልበተኞች አይደሉም። (የማጥቃትና ጉልበታቸውን የማሳየት ፍላጎታቸውን እንዲችሉትና፣ ስሜታቸውን እንዲገዙት።)

ከተረትም ሳይቀር፥ “አህያን ውጭ አስረው ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ።” እንላለን። ለአህያ በጅብ መበላት ማስተባበያዊ ትንታኔያችን ‘ውጭ መታሰሯ’ ነው እንጂ የጅቡ አውሬነት አይደለም። የጅብ ጉልበተኛነት ተለይቶ ታውቋልና እውቅና ተሰጥቶታል። አህያ ግን ከጌቶች አንስቶ ሲረገጥ ችሎ ስለሚኖር፥ መቻል ግብሩ እንደሆነ ተቆጥሮም፣ ውጭ ስለመታሰሩ ጌታዋ ይወቀሳል።

ሰፈር ውስጥ የታወቀ ጉልቤ፥ ልጅ ፈንክቶ ወደ ወላጆቹ አቤቱታ ሲቀርብ፥ “አህያን ውጭ አስረው ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ።… እሱ እንደው ለእኛም እንዳስቸገረ ታውቃላችሁ። እሱስ ይሄን እያወቀ ለምን ከሱ ጋር ይጣላል?” ይባላል።

“ሴት ተደፈረች፣ ተደበደበች” ሲባል፥ “አህያን ውጭ አስረው ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ።… ማን አጭር ቀሚስ ልበሽ አላት? ማን አምሽተሽ ግቢ አላት? ዝም ብሎማ እንዲህ አያደርጋትም።” ይባላል።

“ኧከሌ የተባለ ጋዜጠኛ/ፖለቲከኛ ታሰረ” ሲባል፥ “አህያን ውጭ አስረው ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ።… አርፎ አይቀመጥም ነበር? …ጀብደኛ መሆኑ ነው? …የሆነ ነገርማ ሳያደርግ እንዲሁ አይሆንም።” ይባላል።

“ተማሪዎች በፖሊስ ሀይል ተገደሉ” ሲባል፥ “አህያን ውጭ አስረው ጅብን ነገረኛ ያደርጋሉ።… ማን ውጡ አላቸው? አርፈው አይማሩም ነበር? እስካፍንጫው የታጠቀ ወታደር ፊት ምን ያንጎማልላቸው ኖሮ?”

“ቻሉት… መቼስ እስኪያልፍ” ብለን ከንፈር የምንመጠውም ለተጠቂው ነው እንጂ ላጥቂዎቹ አይደለም። እነሱንማ እውቅና ሰጥተናቸው ማን ጣልቃ ሊገባ?

የሰው ልጆች ጥቃት መቆም ያለበት፥ ባጋጣሚ በሚገኝ እድልና በተጠቂው ሰው ሽሽት ሳይሆን በተስተካከለ ለውጥና ቀጥ ባለ ስልጡን ስርዓት አማካኝነት ነው። ስለዚህ ሁሉም ራሱን ይፈትሽ። ለመብቶቻችንና ለነጻነቶቻችን በጋራ እንቁም። ጥቃቶችን እናውግዝ!

ዛሬ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን (የ16ኛው የጾታዊ ጥቃትን የማውገዝ ወንድ-መር ዘመቻ ማብቂያ) ተከብሮ ሲውል ከብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶቻችን ጋር ሆነን እንደሆነ የታወቀ ነው። ብዙ ብዙ ችግሮች አሉብን።

ብዙዎች በጣም ቅርብ በሆነ የቤተሰብ አባላት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ብዙዎች ‘ህግን ያስከብርልኛል፣ ሰላም ወጥቼ እንድገባ ዘቤ ነው’ ብለው ለደመወዙም እንዲሆን ግብር በሚከፍሉለት የፖሊስ አካል ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች ከቤት ተገፍተው በየሰው ሀገር ተበትነው ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች ከፍለው በሚያሰሯቸው አሰሪዎቻቸው ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች በአደራ በተረከቧቸው የቤተሰብ አባሎቻቸው ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች በመርማሪዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች በቆዳ ቀለማቸው የተነሳ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች በዘራቸው የተነሳ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙ ህጻናት ማስረዳት በማይችሉበት ሁኔታ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ቢዘረዘር አያልቅም። ጥቃት በየፈርጁ፣ የትየለሌ ነው።

ምናልባት መጠኑና ዓይነቱ በጆሮና በዐይን የሚሰጠው ግምት ከፍ ዝቅ ይል ይሆናል እንጂ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ትልቅና ትንሽ የለውም። “በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” ማለት ለሰብአዊ መብቶችም ይሰራል። መንገድ ላይ ሲለክፍና እጅ ጠምዝዞ ሲለቅ ዝም የተባለ ሰው ራሱን ወደ ላቀ አጥቂነት ሊያሸጋግር ይችላል። በዱላ ቸብ አድርጎ የተኛም ነፍሰ ገዳይ ሆኖ ከእንቅልፉ ሊነቃ ይችላል።

ስለዚህ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሆን፥ ሁሉም እንደ ችሎታው መጠን፣ እንደመረዳቱ ልክ፣ እና እንደ አቅሙ ሁኔታ ሊያወግዝና የኅሊናውን ሰላም ሊጠብቅ ይገባዋል። የሰብአዊ መብት ጥሰት ትንሽና ትልቅ እንደሌለው ሁሉ፥ እርሱን የማውገዝ፣ የማጋለጥ እና የመከላከል ሂደቱም ትንሽና ትልቅ የለውምና ሁላችንም በዙሪያችን ዐይናችንን እንግለጥ።

ለሰው ልጆች ሰላም!!

የታላቁ ሩጫ እለት የተሰማኝ የመጠቃት ስሜት…

ከጓደኞቼ ጋር ነበር የሮጥነው። በርግጥ “የሮጥነው” ማለት ይከብዳል፤ የእርምጃ ያህል ነበር። ትንሽ ዱብ ዱብ እንልና ብዙ ሰከም ሰከም እንላለን። ሲለን በቡናና በቢራም በቀላሉ የማይረጥብና የማይወራረድ ርዕስ አንስተን እናላምጠዋለን። ከፌስቡክ ስታተስ እስከ መፅሐፍት አንስተን እንጥላለን። ሸጋ ጊዜ ነበር…

ስንሮጥ ስንሮጥ….

ከሰዓታት ባንዱ ቅፅበት፥ ተግተልትለን መጨረሻ ገባን። መግባታችንን ተከትሎ፥ “እንኳን ደስ አላችሁ።” አለ የመድረኩ አጋፋሪ። ወዲያውም፥ “የመጨረሻዎቹ ተሳታፊዎች ገብተዋል…” ብሎ የመዝጊያ የሚመስል ነገር አወራ። ባልሰማውም ፊቱን ወደ እኛና ቀድመው ወደገቡት ሰዎች መለስ ቀለስ እያደረገው የሚያስበሽቀን ይመስላል። የመጨረሻ በመሆናችን የዛለ ሳቅ ተቀባብለን ከማረፋችን፥ ሰዓቱ በመርፈዱ ግቢው ውስጥ የነበሩ ፖሊሶች እንድንወጣ ያዋክቡን ጀመር። እኛም ብድግ ብድግ ብለን ወደ መውጫው ሄድን።

ፊትና ኋላ ሆነን ከግቢው ወጥተን እየተጠባበቅን፣ ሁለት ተራምደን አንዱ ውኅ ሊገዛ ሲቆም፥ ስንቆም፤ ትንሽ ቆመን ሁሉም ሲሰበሰብ፥ ስንሄድ… ከፊት ለፊታችን ፒካፕ መኪና አየን። የሩጫውን ቲሸርት የለበሱ ጎረምሶች እየተፈናጠሩ ሲሰፍሩበት ስናይ፥ የወዳጄ እብደት ታክሎበት “ጆዬ ፒካፕ… እንጫን።” አለችኝ። መልሴን በድርጊት ስሰጣት፣ ወደኋላ ዞሬ ሌሎቹን እየፈለግኩ ወደመኪናው አመራሁ። የተጫኑት ሰዎች ጋቢና በነበረ የይሁንታ የእጅ ምልክት መሆኑን ስላስተዋልኩ፥ እንደማንከለከል በማመን ነበር። ግን የመኪናውን ጫፍ ስይዘው “አይቻልም” አለ አንደኛው።

የሰፈር ድግስ ቤት ቀድሞ ገብቶ የሰፈር ልጆች ላይ ሃርደኛ እንደሚሆን ከልካይ መስሎኝ፥
“ለምን? አንተ ተሰቅለህ የለ?” አልኩት፤ በዚያ ድካም ላይ ሊኖረኝ በሚችል ትህትና።
(ለራሱ ሊፍት ለምኖ ሌላውን ይከላከላል? ትልቅ አይደለ? በሰው ንብረት አዛዥ መሆን ደርሶ)

“አይቻልም። ውሻ” አለኝ። አይቻልምን ደጋግሞ ብሎኝ አልሰማ እንዳልኩት ሁሉ ስቦት።

ሊፍት (ለያውም ፒካፕ ጀርባ) ለመሳፈር በማሰቤ ብቻ “ውሻ” ስባል፣ ከባለጌ አፍ ብቆጥርበትም… የሆነ ዓይነት መጠቃት ተሰማኝ።

መሳደቡ ባለመኪናውን እንደሚያውቀውና እንደ ልጅ ‘የእኛ መኪና ነው’ ማለቱ ገባኝ። በጣም ስለደከመኝ የመጣያ ጉልበት አልነበረኝም እንጂ ስድቡ አብሽቆኛል።

“እና ምን ያሳድብሃል? በስርዓት አትናገርም?” አልኩት የሞትሞቴን፣ በደከመ ንቀት እያየሁት።

ወዲያውም፥ “ነይ ባክሽ እንሂድ” ብያት መሄድ ጀመርን።
(በከመሬት ተነስቶ ተሳዳቢነቱ ንቄው ከርሱ ጋር ላለመሳፈር ብዬ ተውኩት እንጂ፥ ራሱ ሊፍት ጠይቆ መሆኑን እርግጠኛ ስለነበርኩ፥ ዝም ብዬው ለመሰቀል እሞክር ነበር።)

እሷም “ጆዬ ና በቃ። ይቅርብን።” አለች።

“ሰዉ ግን ምን ሆኖ ነው? አይሆንም አይልም? ይሳደባል እንዴ?” ብያት እሷን አስከትዬ መሄድ ቀጠልኩ።

“ና ና…” የሚል ድምፅ ተከተለኝ።
(አስፓልቱ ሙሉ ሰው በመሆኑ እኔን አልመሰለኝም ነበር።)

ተደገመና እኔን መሆኑ ገባኝ።
(ሰውዬው ጤና የለውም? ወይስ ለነገር ነው የሮጠው?)

“አንተን እኮ ነው። ና…”

ዝም ብዬ እሄዳለሁ።

(ቆይ እርሱን ና ብለው ይመጣልኛል?)

“ቁም! አንተን እኮ ነው…”

ዝም ብዬ እሄዳለሁ።

(ቁም ብለው ይቆምልኛል? ምኔ ነው እሱ? ጓደኛዬ ነው ወይስ አባቴ ነው? አጎቴ ነው? ወይስ የአባቴ ጓደኛ ነው?…ጮሆ ቁም የሚለኝ?)

በጣም ስለደከመኝ መመላለሱን አልፈለግኹም። ብፈልግም ጉልበት የለኝም ነበር። ሌላ ጊዜ ቢሆን ይሄ ከማላልፋቸው ጥቃቶች አንዱ ነው። ያን ቀን ግን ዞርም ሳልል በቸልታ መሄዴን ቀጠልሁ። (በምን አቅሜ?)

ወዲያው ጠንካራ እጅ ከትከሻዬ ጠፍንጎ እንደ ሳጥን አዞረኝ። ሌላ ፊት ነበር። ጋቢና የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም።

“እየተጠራህ አይደል? ንቀት ነው?” አለ ብዙም ሳይቆጣ፤

(ያመዋል እንዴ ሰውዬው? እርሱን ጠርቼው ዝም ቢለኝ ‘ንቀት ነው?’ እለዋለሁ? መጥራቱስ ንቀት ካልሆነ ክብር ነው?)

“ልሰቀል አልኩት ለራሱ ሊፍት ጠይቆ ከለከለኝ። በቃ ለምን ይጨቃጨቃል?” አልኩ ዐይኔን በብስጭት አጉረጥርጬ። (ጉርጥ)

“ሲጠራህ እኮ መቆም አለብህ።” አለ በማግባባት ዓይነት።

“ጥጋበኛ።” እያለ ሌላው ሊጎትተኝ እጁን ይሰዳል። በዚህ ቅፅበት፥ የመኪናዋ ታርጋ “ፖሊስ” ማለቷን አስተዋልኩ።
(የፖሊስ መኪና የሚገዛው እኛው በምንከፍለው ግብር አይደል? ደሞዛቸውስ? ታዲያ ምናለ ቢያንስ በትህትና ቢናገር?)

ምናልባት ስራ ላይ ነበሩ። ወይ እንደእኔው ከጓደኞቻቸው ጋር ሊሮጡ ነበር የመጡት። …ግን መጠቃቴ ጎልቶ ተሰማኝ። ሆድ ባሰኝ። መጀመሪያ “ስንት ዓይነት ሰው አለ?” ብዬ ያለፍኩት መጠነኛ ጥቃት፣ ህመም ሆነብኝ። ሲሆንስ፥ ወጉ ጉልበተኞች እንዲህ ሲያበሻቅጡን ፖሊስን ማመንና ተገን ማድረግ ነበር። እልሄ ቢገነፍልም፥ ምንም እንደማላመጣ ሳውቅ ዋጥኩት። ዝም ማለት እንደሚሻል ወሰንኩ። የያዘኝ ሰው ነገሩን ማብረድ ይፈልጋል። የገባው ነገር ነው።

“ሲጠራህ አትመጣም? አታከብርም? ፖሊስ ሲጠራህ…” አለኝ ተለሳልሶ።
(ጠንቋይ እቀልባለሁ? ብቀልብስ ፖሊስ ስለጠራኝ ብቻ ማሸርገድ አለብኝ?)

“ለጠራኝ ሁሉ እሄዳለሁ? እርሱስ ሰው አያከብርም? ዩኒፎርሙን ለብሶ ቢጠራኝ በግዴ እሄድለት ይሆናል። እንደ እኔ ቲሸርት ለብሶ ሲጠራኝ ግን ማን ነው ብዬ ነው የምሄደው?” አልኩት ሳላስጨርሰው።

አንድ አራት ወጠምሻዎች ከመኪናው ላይ እንጣጥ እንጣጥ እያሉ ከበቡኝ። አወራረዳቸው የፊልም ቀረፃ ይመስላል። ሁሉም ቲሸርት ስለሆነ ያደረጉት ፖሊስ መሆናቸውን ማወቅ ይከብዳል።

“ጥፍራም! አምጣው ጫነው።”
“ሌባ….”
“ጣቢያ….”
“ልክ ይገባል አምጣው።”
“አትለምነው…”
ሌላም ሌላም…ዛቻዎች ከአፎቻቸው እየተነባበሩ ሾለኩ። አንደኛው ሊጎትተኝ ሲሰነዝር፥

“ልቀቀኝ። በቃ እኮ እንደ እኔው ሯጭ መሰለኝ ሲጠራኝ አልሄድኩም። ፖሊስነቱን እንዳውቅለት ነው ደግሞ ከላይ ለመጫን ስል የሚሳደበው? ዝም ብሎ የፖሊስ መኪና ነው አይለኝም?” አልኩኝ።
(የፖሊስ መኪና መሆኑን ቀድሜ ባውቅ እንዴትም ቢደክመኝ ለመጫን አልጋበዝም ነበር።)

ምንም እንደማላመጣ አውቃለሁ። የብሶቴን ነው እንደምንም የተናገርኩት። ይህም ሆኖ ላለመናገር የዋጥኩትና ከጓደኞቼ ጋር የተበሳጨንበት ይበዛል። ሰዉም ለመናቸው… የጭንቀቱን አስረዳቸውና ለቀቁኝ።

የመጠቃት ስሜቱ ግን አብሮኝ ከረመ። ለብዙኛ ጊዜ አቅመ ቢስነቴን አየሁ። እፅፈዋለሁ አላልኩም ነበር…
————————-
ታዲያ አሁን በምን ትዝ አለኝ?

እስኪ እኔን — ሴት፥ ፖሊሶቹን — ወንድ አድርገን ስለን በሁለት ፆታ እንየው….

“ነይ” ስንላት
“ሲጠራሽ አትመጪም ንቀት ነው?” ስንላት
“ሲጠራሽ አትሄጂለትም? አታከብሪም ወንድ ሲጠራሽ?” ስንላት…
ለጠራት ሁሉ ባለመቆምና ባለመዞር መብቷ ስትሄድ፥ ስትሰደብ….

አይከብድም?

ቢደረግብን የማንወደውንና እኛ ዘለን ሌሎች ላይ የማናደርገውን ነገር ሰዎች እኛ ላይ ሲያደርጉት ስናይ አይከብድም? ከዚያ በላይስ የመጠቃት ስሜት (sense of helplessness) ከወዴት ይሰማል?

ሰው በሰውነቱ ይከበር! የሰው ልጆች ጥቃት ይቁም! የሴቶች ጥቃት ይቁም!